Translate

Wednesday, October 10, 2012

ያልተመጣጠነ ግጥሚያ


fight
ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ታመዋልም ሞተዋልም በሚማልበት ሰአት  ሎጋው ሽቦ ተዘፈነ …
የርዕሰ ብሄር መለስ ዜናዊ ሞት ይፋ በሆነበት ሰአት ደግሞ ብር አንባ ሰበርልዎ ተብሎ ሲዘፈን በሰፊው ተሰማ…
ኃይለማርያም ደስ አለኝ ቦታው ተፈቅዶላቸው ሀገር ወከሉ ተብሎ ሲታወጅ አስገራሚው ዘፈን አላቆመም የቤተ  ዘመዱ ይታያል ጉዱ ይባል ተገባ…
*****************************************************************************************************

አጋጣሚ የፈጠረውን ፖለቲካዊ ግርግር በጥበብ ተጠቅሞ በፖለቲካው እንቅስቃሴ ውስጥ የመደራደሪያ አቅም በማበጀት ወይም አቅም በመገንባት አማራጭ ሀይል መሆንን ከማሳየት ፋንታ በቀረርቶና በሽለላ የጨዋታውን ህግ ለመቀየር መመኘት የምኞት ሁሉ መናኛ ቢባል ያስነውር ይሆን?
በትግል አጋሮቻቸው ከአንድ ነፍስ በላይ እንዳላቸው የተስተናገዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጨረሻ ጊዜ የስጋቸውን ነፍስ ተሰናብተው በአጥንታቸው ላይ በቀረው ነፍስ ተንገዳግደው ደቡብ አሜሪካና ሜክሲኮ ብቅ ብለው ነበረ።
ታዲያ ከወዳጃቸው ከቻይናው መሪ ጋር ተጨባብጠው እስከ ወዲያኛው በተሰነባበቱበት ወቅት አጥንታቸው ከስጋቸው መለያየቱን ያላስተዋለ የኮምፒውተር ቆዛሚ አለ ብየ አላምንም።
በዚያን ወቅት በውጭ የሚገኙት የፖለቲካ ጥበብ ያልዞረባቸው ተቃዋሚዎች መንግስት የተገለበጠ መስሏቸው ተዋግቶ ነፃ መሬት እንደያዘ የደፈጣ ተዋጊ ዘራፍ በማለት የተለመደው ምስቅልቅል የፖለቲካ አመራር ከየአቅጣጫው ይጎርፍ ጀመረ።
ሰውየውም ያላቸውን ነፍስ በሙሉ አሟጠው ካመለጡም በኋላ ይህንን ማመን የከበዳቸው ጓዶቻቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሬሳ አልሞትክም ብለው ሲክዱ፥ ህዝቡን ደግሞ መሪያችን አልሞቱም በማለት ገገሙ።
ይህም ሆኖ መሪያችው የሚሞት ስጋ ለባሽ መሆናቸውን መቀበል ያቃታቸው እስከሚመስል ድረስ ተደናግጠው በነበረበት ወቅት የመሪያቸውን ሞት በመካድ የመረጋጊያ ግዜ ገዝተው የተቃዋሚዎቻቸውን እንቅስቃሴ በትጋት መከታተል ጀመሩ።
ፖለቲካ የፉክክር ጨዋታ መሆኑን እንጂ የመጫወቱ ተሰጥኦ እምብዛም ያልተካኑት ከሀገር ውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ታዲያ የተሸበረው መንግስት ጊዜን ለመግዛት በመረጠው ሜዳ ሲያሰልፋቸው በተርታ ተኰልኩለው የመለስ ዜናዊን ዜና እርፍት ለነበረከት ስምኦን ለማሳመን ያላሉትና ያልሰማነው ትንታኔ የለም እንግዲህ ይህንን ስንል ፉከራውንና ሽለላውን ትተነው ነው።
በመጨርሻም በረከት፤ ሳሞራና፤ ብርሀኔ ገብረክርስቶስ፤ የሞት ትርጉሙ ገብቷቸው የመሪያቸውን ሞት ይፋ አደረጉ።
በዚህን ጊዜ ደግሞ ከሜዳ ውጭ ሆኖ የሚጫወተው ተቃዋሚ ቡድን በጎዶሎ ተጫዋች ከሚጫወተው የገዢው ፓርቲ ላይ ግብ ለማግባት የጫዋታ ስልት ቀይሮ ዋና ሜዳ ውስጥ ለመግባት መሞከሩን ዘንግቶ ድል በድል እያሉ በመዘመር ለመለስ ከሚያለቅሰው ወይም ከሚያስለቅሰው ቲፎዞ ጋር ግብግብ ገጥመው ጨዋታውን በፎርፌ አስረከቡ።
በፖለቲካ ጨዋታ እንደሚታወቀው ዳኛ የሚሆነው ምንግዜም አሸናፊው ነው።
በመሆኑም በተቆጣጠሩት ሜዳና ባላቸው የዳኝነት ስልጣን ተጋጣሚውን ቡድን ከለቀስተኛው ጋር አተካራ ተያይዞ ከሜዳው መራቁን ካረጋገጡ በኋላ የጎደለባቸውን ተጫዋች (ጠቅላይ ሚኒስትሩን) ለመተካት እርስ በርስ ተሳልጠው፥ ተዋቅጠው፥ ተዳጉሰው፥ ተሰልቀው፥ በመጨረሻም ለኃይለማርያም ደሳልኝ የሟቹን የማእረግ ስምና መቀመጫ ሸልመው አሁንም ጨዋታውን በበላይነት መምራት ይዘዋል።
ታዲያ እንዳያችሁት በፎርፌ የተዘረረው የጨዋታው ህግም ይሁን ጥበብ ያልገባው የውጪው ተቃዋሚ ቡድን በሚያስገርም አይነት የምኞት ፈረስ ላይ ቂጥጥ ብሎ በጎደለው ተጫዋች የተተካውን ኃይለማርያም ደሳለኝን በራሱ ቡድን ላይ ጎል እንዲያገባ የቤተዘመዱ ይታያል ጉዱ እያሉ በመዝፈን የምኞት ሁሉ መናኛ የሆነውን ምኞት ተመኙ።
ባልተመጣጠነ ጉልበት፥ ውል በሌለው አመራር፥ ጥበብ ባልዞረበት ስሌት፥ በተለይ ደግሞ፥ በተመሰቀቃቀሉ ድርጅቶች፥ የሚመራው ከሀገር ውጭ የሚደረገው ትግል፤ ጉልበቱን ያፈረጠመን መንግስትና፥ ሁኔታዎችን የመጠቀም የረቀቀ ዘዴ የተለማመደን ግዙፍ ድርጅት፥ እንዲሁም ስልጣን ማለት አስፈላጊ የሆነ የሰይጣን ስራ (power is the necessary evil) መሆኑን ተረደቶ በጭካኔ ለሚወሰድ እርምጃ ቀላል ምክንያት ሰጥቶ ከሚያስፈፅም ቡድን ጋር ሲጋጠም የራስ አቅምንናና የባላንጣን ጉልበት ማወቅ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ወሳኝም ነው።
መሪውና ተመሪው ተደባልቆ፥ ሽለላና ፉከራ በመሰቃቀሉት፥ በእውቀት ሳይሆን በስሜት በሚንቀሳቀስ በብዙ መሪዎች የሚመራው እንቅስቃሴ የመሸነፍን ልምድ ለሀያ አመት ደግሞ ደጋግሞ ተጎናፅፏል፤ ይህንን ለመቀየር ይህችኑ እውነት ከልብ ማመን የመጀመሪያው እርምጃ ይሆናል።
በተለይ ካገር ውጭ ሆኖ አብሮ ከማይኖረው ህዝብ ላይ የመሪነትን መንፈስ ማዳበር በተግባር ሊተረጎም የማይችል ግብ አልባ ጨዋታ ነው።
የሰማኒያ ሚሊዮን ህዝብ ጉዳይ የኔ ነው ብሎ እራሱን ወክሎ የሚንቀሳቀስ ቡድን መደገፍ እንዳለበት ሁሉ ሀላፊነትን በሚገባ ካልተወጣና መወጣት ካቃተው እንዲስተካከል መጠረብ ይገባዋል።
ስለዚህም በውጭ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሰቃቀለውን የተቃዋሚ ድምፅ መግራትም ሆነ ማጎለበት ካልቻሉ መገሰፅና መወረፍ አግባብ ነው።
ብዕሬ በተቃዋሚዎች ላይ እንዲህ መሳለቁ ገዢዎቹን ደግፌ ወይንም ፈርቼ አይደለም።
ይህንን ብሶቴን በማስተዋል ያነበበና እንደኔ በውጭ በሚገኘው ተቃዋሚው ተስፋ የቆረጠ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይገነዘባል ብዬ አምናለሁ።
የመብት ረጋጮቹና የጉልበት አምላኪዎቹ ገዥዎቻችንን ፅናትንና ያላሰለሰን ዘዴ ባደንቅም ለሰማኒያ ሚልዮን ህዝብ ተጠሪ ለመሆን የሚያበቃ የሞራልም ሆነ የሀገር ፍቅር ስሜት የሌላቸው መሆናቸውን መናገር አስፈላጊ ይመስለኛል።
በፖለቲከኞች መሳለቅ መቀለድ ከዛም ሲያልፍ መፀየፍ ግፍና አድሎ ያንገበገብው ብዕር መሄጃ ሲያጣ የሚያነባው እንባ በመሆኑ እንደተለመደው በአንድ አይነት አስተሳሰብ ዙሪያ ብቻ ያልተፃፈን አስተያየት ከተቆጣጠራችሁት መድረክ የምታገሉት ከሆነ ከገዢዎቻችን መንፈስ ያልተለያችሁ ስለሆነ አንድ አርጌያችሁ እንድታገላችሁ እገደዳለሁ ማለት ነው።
በመጨረሻም የፖለቲካ መሪዎችና ፓርቲዎች የመምራት ሀላፊነት ስላለባችሁ በድረገፅ አርበኞች፤ በሬድዮ ፕሮግራም ፊት አውራሪዎች፤ በአጠቃላይ በብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች መመራታችሁን አቁሙና እንደ ፖለቲካ መሪ አላማችሁን ፕሮግራማችሁን ፍልስፍናችሁን አጥምቁንና ምሩን።
የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ወይም የድረገፅ፥ ሬድዮንና፥ ፓልቶክ፥ ጋሻ ጃግሬዎች በምታደርጉት ተሳትፎ መብታችሁን እየተለማመዳችሁ መሆኑን ጥያቄ ውስጥ ባላስገባውም ቢይንስ ብያንስ ከሙያ አንፃር በመመልከት ለዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት የሚደርገው ትግል እንዳይጓተት ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንቅፋት አትሁኑ። ማለትም በሙያችሁ እንደጋዜጠኛ አገልግሉን፤ አለበለዚያም ለአንዱ ፓርቲ አድራችሁ እንደ መሪ ምሩን፤ ተመሰቃቅላችሁ አትመሰቃቅሉን።
እስካሁን ግን ሳታውቁት ጠላታችሁን እያገለገላችሁ ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይታደጋታል!!
ከዘመድ አገኘሁ
ጸሐፊዉን ለማግኘት ከፈለጉ at: zamedaganiahu@gmail.com

No comments:

Post a Comment