የቅዳሜ ማስታወሻ
ሰሞኑን “አይጋ” የተባለ የወያኔ ድረገፅ ግብረአበሮች ያላቸውን ሶስት ጋዜጠኞች በተከታታይ ፅሁፍ ሲደበድብ ሰንብቶአል። እነዚህ ሶስቱ ጣምራ ጠላቶች፣ አቤ ቶክቻው፣ ተመስገን ደሳለኝ እና እኔ ነበርን። ፀሃፊው እንቅልፍ በተጫጫናቸውና ውሃ በጠማቸው ቃላት ረጅም ሃተታ ፅፎአል። የአቤ፣ የተመስገን እና የኔ ስሞች ያለበትን እየመረጥኩ እየዘለልኩ ነው ያነበብኩት። ምክር ነክ ሃተታዎችን ዘለልኳቸው።
ከሶስቱ ተከታታይ ፅሁፍ ቀልቤን የሳበችው፣ አቤ ቶኪቻውን ፀረ -ኢትዮጵያ ብለው መፈረጃቸው ነው። እኔን ቢሉኝ ያምርባቸዋል። “የቡርቃ ዝምታ”ን በማንሳት ወይም “ኤርትራዊ ነው” የሚለውን በማደማመቅ ለማሳመን አይከብድም ይሆናል። አቤን ፀረ - ኢትዮጵያ ለማለት እንዴት እንደደፈሩ ግን አልገባኝም። ነፍሱን ይማረውና መለስ በህይወት ቢኖር ኖሮ፣ እርግጠኛ ነኝ ይህን ፅሁፍ የፃፈውን ካድሬ እስርቤት ይልከው ነበር።
አልተረዱትም እንጂ አበበ ቶላ የሃገር ቅርስ ነበር። የህዝብ ስሜቶችን እና ብሶቶችን ጎልጉሎ እያወጣ በሚያስቅ መንገድ እውነትን ለተደራሲው ማቅረብ የቻለ የብእር ጀግና ነው - አቤ። ኢህአዴግ ብልህ ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አቤ ያሉ ብእረኞች በነፃነት እንዲፅፉ ማመቻቸት ነበረበት። መስታወት ይሆኑት ነበር። ስህተቶችን ለማረም ያግዙት ነበር። አቤን በፀረ - ኢትዮጵያነት የሚፈርጅ ምን አይነት ጭንቅላት ይሆን? ይህች ኢትዮጵያ የተባለች ሃገር እንደው ምን ይሻላታል? እውነተኛ ልጆችዋን ቀረጣጥፋ እየበላች የምትኖረው እስከመቼ ይሆን? የጠላቶችዋ መፈንጫ መሆኗ ከቶ መቼ ያበቃል?
ከመለስ መሞት ወዲህ አቤ በፃፋቸው መጣጥፎች፣ ብዙ ጊዜ ጧ! ብዬ ስቄያለሁ። ሁለቱ ግን አይረሱኝም። መለስ በመሞቱ ሃዘናቸውን ገለፁ ስለተባሉት የጎዳና ተዳዳሪዎች ምን ነበር የፃፈው? ቃል በቃል ትዝ አይለኝም፣ አሳቡ ግን እንዲህ ነበር፣
“እኛ ጎዳና ተዳዳሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ተማምነን ነበር ወደ ጎዳና የወጣነው። እሳቸው ከሞቱ ምን እንሆናለን? እንግዲህ ምን እናደርጋለን። ያለን ምርጫ ያው ወደ ቤታችን መመለስ ነው…”
ሌላዋ ደግሞ እንዲህ ትነበባለች፣
“…እኔ የምለው ዘንድሮ ባለ ስልጣኖቻችንን እየታዘባችሁ ነው? ኩብለላን እኮ የስራቸው አካል አደረጉት። እኛ አቀርቅረን ኮብል ስቶናችንን ስንጠርብ፣ እነርሱ ደግሞ ኮብልል “ስቶን” እያሉ እየነኩት ነውኮ!”
No comments:
Post a Comment