ኢሳት ዜና:-የህወሀት ም/ል ሊቀመንበር በመሆን በቅርቡ የተመረጡት የየኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ይህንን የተናገሩት ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር ባደረጉት ውይይት ነው። ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የአክራሪነትና የሽብርተኝነት አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ አገሪቱን ሊበታትናት መቃረቡን ገልጠዋል። ” በሀይማኖት ሽፋን ኢትዮጵያን ለመበታተን ና ለማተራመስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ዝም ብለን መመልከት የለብንም፤ አሁን የሚታየው አክራሪነት በማንኛውም መልኩ መገታት አለበት ሲሉ” የመንግስትን አቋም ግልጽ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የትምህርት ጥራትን ለማረጋጋጥ ተብሎ በተጠራ ስብሰባ ላይ ነው። ቀደም ብሎ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራንን በአንድነት በመጥራት ለማወያየት እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ምክንያቱ በግልጽ ሳይነገር እንዲሰረዝ መደረጉ ይታወሳል። መንግስት የዩኒቨርስቲ መምህራንን በየፋኩልቲያቸው በተናጠል ለማናገር መወሰኑም ታውቋል።
ዶ/ር ደብረጺዮን ” አክራሪነትን ከእንግዲህ አንታገስም” በማለት መናገራቸው ምናልባትም መንግስት ላለፈው አንድ አመት በአወልያ ተጀምሮ መላውን ኢትዮጵያን ያዳረሰውን የሙስሊሞች የመብት ይከበርልን ጥያቄ በሀይል ለመጨፍለቅ ማሰቡን የሚያሳይ ነው በማለት አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ሰው ለኢሳት ተናግረዋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ አንዳንድ መምህራን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የኑሮ ውድነት በማንሳት የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ለሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል። ሚኒስትሩ ግን በዚህ አመት መምህራን የደሞዝ ጭማሪ እንዳይጠብቁ ነግረዋቸዋል። አሁን ባለው የደሞዝ አከፋፈልና በየጊዜው በሚታየው የዋጋ ንረት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እንደማይቻል መምህራኑ ገልጠዋል።
No comments:
Post a Comment