ከዶ/ ር ዘላለም ተክሉ
10/18/ 2012
በቅርቡ የቻይና ቲቪ ኒውስ1(China CCTV News) ኢትዮጵያን “የአፍሪካ ኢኮኖሚ ፓወር ሀውስ” ሆናለች ብሎ ሲያሞካሽ “ሊበሉዋት ያሰቧትን ጅግራ ቆቅ ነሽ ብለው ይሏታል” ዓይነት ፉገራ መስሎኝ ችላ ብዬ ተቀምጬ ነበር:: ነገር ግን “የመለስን ራዕይና ተክለ ሰውነት ወራሹ” አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሰሞኑን ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ተመሳሳይ ፉከራ ማድረጋቸውን ስሰማ በዝምታ የሚታለፍ ጉዳይ እንዳልሆነ ተረዳሁኝ:: በሳቸው አባባል ኢትዮጵያ በቴሌኮምና በኢንተርኔት ዝርጋታ ዘርፍ ባለፈው አመት ባደረገችው ልማት ከደቡብ አፍሪካና ግብጽ ቀጥሎ በሶስተኝነት ደረጃ እንድትሰለፍ ማድረጋቸውን አረጋግጠውልናል2::
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ አደገ፣ ድህነት በከፍተኛ ደረጃ ቀነሰ፣ አገሪቷ በፎቅና በመንገድ ተጥለቅልቃለች የሚሉት ዜናዎች ለደሀውና ለተራበው ህዝባችን ቅንጣት ታክል ፋይዳ የማይሰጥ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ በተደጋጋሚ የተረጋገጠ እውነታ መሆኑ ይታወቃል:: ነገር ግን ያ ሽለላ አልበቃ ብሎ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ ከያዙት አገሮች ደረጃ ደርሳለች እያሉ መፎከር ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ማሳወቁ አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል:: በእውነቱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን አይደለም ከአውሮፓውያንና ከአሜሪካኖች የዕድገት ደረጃ ብትደርስ የሁላችንም ፍላጎት ነው:: ነገር ግን ያላገኘነውን ዕድገት ተገኘ በማለት፣ ገና ያልተነኩትን ችግሮቻችን ቀርፈናቸዋል በማለት ምንም የምናገኘው ጠቀሜታ የለም:: እልቁንስ በዚህ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመዘናገት ሃገራችን ለዘመናት ካለችበት ረሃብ፣ ድህነትና ድንቁርና ለመላቀቅ ያለንን ቁጭት፣ተነሳሽነት፣ ቁርጠኝነትና ትብብር ከማጠናከር እንዳንዘናጋና እንዳንስተጓጉለ ነው የምፈራው::
ይህንንም ስጋቴን ለወገኖቼ ለማከፈል ይችን ትንሽ መጣጥፍ አቅርቤአለሁ:: በዚህ ጽሁፍ በእርግጥ ኢትዮጵያ “የአፍሪካ ኢኮኖሚ ፓወር ሃውስ” የምትባልበት ደረጃ ደርሳለችን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እሞክራለሁ:: ምላሼንም ለመስጠት ወያኔ ራሱ እንደ ምንጭነት የሚጠቅሰውን የዓለም ባንክ ዳታ (World Bank Country Data) ተጠቅሜአለሁ:: ለንጽጽራዊ ትንተናም ጠቅላይ ሚኒስትራች በንግግራቸው ከጠቀሱዋቸው ደቡብ አፍሪካና ግብጽ በተጨማሪ ጋናን እንዲሁም ከጎረቤታችን ኬንያን አካትቻለሁ::
እንደኔ እንደኔ አንድ ሃገረ የአህጉሯ የኢኮኖሚ ፓወር ሃውስ ናት ለመባል በኢንዱስትሪ ልማት፣ በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት፣ በኢንፎርሜሽንና ኮሚዩንኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ፣ በንግድ ህግና ሥርዓት ቀዳሚ ስፍራ መያዝ ይገባታል ብዬ አምናለሁ:: በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) እና ነፍስ ወከፍ ገቢም በከፍተኛ ደረጃ ላይ መገኘት የሚገባት ይመስለኛል::
በዓለም ባንክ የ2011 መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከ100 ሰዎች አንድ ሰው ብቻ የኢንተርኔት እንዲሁም 16 ሰዎች ብቻ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ሲሆን በደቡብ አፍሪካ 20 በመቶ ሰዎች ኢንተርኔት እንዲሁም 127 ከመቶ ሰዎች የሞባይል ተጠቃሚች ናቸው:: በግብጽና በጋናም በቅደምተከተል 14 እና 35 በመቶ የኢንተርኔት እንዲሁም 101 እና 84 በመቶ ሞባይል ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ነው የሚታወቀው:: ጎረቤታችን የሆነችው ኬንያ እንኳን 28 በመቶ የኢንተርኔት እና 59 በመቶ የሞባይል ስልክ አጠቃቀም ብልጫ እንዳላት ይዘገባል:: እንግዲህ በምን መለኪያ መዝነው እንደሆነ አላውቅም ጠ/ ሚንስት ሃይለማሪያም በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ አገራችንን ከደቡብ አፍሪካና ግብጽ ጋር ያወዳደሯት:: እንዴትስ ሆኖ ነው እንደዚህ በተዳከመ መሰረተልማት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዋና መናሃሪያ መሆን የምትችለው::
በእርግጥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢኮኖሚ መጧጧፊያ እንድትሆን ከተፈለገ በኢዱስትሪ ምርትና በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ ሊኖራት ይገባል:: በመሬት ላይ ያለው እውነት ግን ይህንን አያሳይም:: በ 2011 የዓለም ባንክ መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርት 3.8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ ሲሆን የደቡብ አፍሪካ $113 ቢሊዮን፣ የግብጽ $81 ቢሊዮን ይደርሳል:: ከጋናና ኬንያ ኢንዱስትሪ ምርት ጋር ሲነጻጸር እንኳን የአገራች ምርት ከግማሽ በላይ አይሆንም:: በኢሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትም በደቡብ አፍሪካና ግብጽ ከ140 ቢሊዮን ሜጋ ዋት አወር በላይ ለልማት እንቅስቃሴአቸው የሚያቀርቡ ሲሆን በኢትዮጵያ እስካሁን ከ 4 ቢሊዮን ሜጋ ዋት አወር በላይ አይመረትም:: በኬንያና ጋና እንኳን ያለው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከ 7 እስከ 9 ቢሊዮን ሜጋ ዋት አወር ይደርሳል:: በቂ ሃይል ባለበት ሁኔታ ይመስለኛል ብዙ የሃገር ውስጥና የአፍሪካ ኢንቨስተሮች በኢንዲስትሪው ዘርፍ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት:: ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ምርት ሲኖር ይመስለኛል በአፍሪካ ገበያ ትልቁን ድርሻ መያዝ የሚቻለው:: እነዚህ ሁኔታዎች ጭራሽ ባልተፈጠሩበት አግባብ ነው እንግዲህ አገሪቷ “የአፍሪካ የኢኮኖሚ ፓወር ሃውስ” እየተባለች የተጠራችው::
የሃገር ውስጥ ሃብትና መዕዋለ ንዋይ ከአፍሪካ ብሎም ከዓለም ዙሪያ በማስገባት ኢኮኖሚን ለማሳደግ ከተፈለገም የተቀላጠፈና አስተማማኝ የፋይናንስ፣ የንግድና የህግ ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል:: መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ለመቶ ሺህ ሰዎች እያገለገሉ ያሉት የንግድ ባንኮች ብዛት ከሁለት በታች ሲሆኑ በደቡብ አፍሪካ 10 ባንኮች እንዲሁም በኬንያ 5 ባንኮች የፋይናንሺያል አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ:: ለቢዝነስ ሥራዎች መቀለጠፍ፣ የንግድ ፍቃድ፣ የመሰረተ ልማት አገልግሎት ለማስፈቀድ፣ የንብረትና የፈጠራ ችሎታ ባለቤትነትን ለማስከበር የሚያስችል የህግና የአሰራር ሥርዓት እንዳለ ለማረጋገጥ Ease of Doing Business ተብሎ የሚጠራውን ዓመታው ሪፖርት ተጠቅሜ ነበር:: በዚህ ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ ከ183 አገራት 111ኛ ስትሆን ደቡብ አፍሪካ 35ኛ፣ ጋና 65ኛ፣ ግብጽ 110ኛ እንዲሁም ኬንያ 109ኛ እንደሆኑ ይታያል:: ይህ ዝቅተኛ ደረጃ የሚያመለክተው በሃገራችን ንግድና ኢንዱስትሪን በተስፋፋ መንገድ ለማካሄድ እምነት የሚጣልበት ሥርዓት ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ባነሰ ደረጃ ላይ እንደሆነ ነው:: ለዚህ ይመስለኛል አሁን በአገራችን ያለው ኢንቨስትመንት በገዢው ፓርቲ ቢዝነስ ኢምፓየር፣ በአድር ባይ ነጋዴዎች፣ በሙስና ላይ በተመሰረቱ የ ቻይና፣የህንድና የሳኡዲ ኩባንያዎች ተጠቅልሎ ሊያዝ የቻለው::
እንግዲህ ልብ እንበል፣ ኢትዮጵያ ናይጄሪያን በመከተል ጋናን በሶስት እጥፍ፣ ኬንያን በሁለት እጥፍ፣ ደቡብ አፍሪካን ደግሞ በ1/3ኛ ያህል የሚበልጥ የህዝብ ሃብት ያላት ሃገር ናት :: ይህ ከፍተኛ ህዝብ ብዛት ለአፍሪካና ለዓለም ነጋዴዎች ምርት (market supply) ማራኪ ገበያተኛ (potential consumer) በሆነ ነበር:: ነገር ግን የህዝቡዋ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ$380 በታች መሆን የሚያጓጓ የገበያ ፍላጎት (market demand)ያላት ሃገር ሊያደርጋት አልቻለም:: ለዚህ ይመስለኛል ብዙ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅቶች ደቡብ አፍሪካን ($8070 ነፍስ ወከፍ ገቢ)፣ ግብጽን ($2780)፣ ጋናን($1570) የሚመርጡት:: የኬንያ የነፍስ ወከፍ ገቢ ($800) ከኢትዮጵያ በሁለት እጥፍ በሆነበት አግባብ የአፍሪካ ንግድ ዋነኛ አንቀሳቃሽና ተጠቃሚ ነን እያሉ መመጻደቅ ምን ያህል ቅዥት ሊሆን እንደሚችል ይታያችሁ::
ከላይ በቀረበው ትንተና መሠረት ለቻይናው “… የጅግራና ቆቅ ጨዋታ…” ወይም ለወያኔ ፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያን “የአፍሪካ የኢኮኖሚ ፓወር ሃውስ” ነች ብሎ መዳዳት ስላቅ ይመስለኛል:: ባሁን ወቅት ህዝባችን በልማት ረገድ የደረሰበትን የንቃተ ህሊና ደረጃ፣ ጉጉነትና ተነሳሽነት በማስተባበር ይህንን ምኞት ማሳከት ይቻላል የሚል ሙሉ እምነት አለኝ:: ነገር ግን አሁን አገሪቱ ውስጥ የሰፈነው የነጻነትና ዲሞክራሲ አፈና ካልተቀረፈ በስተቀር ምኞታችን ህልም ብቻ ሆኖ የሚቀር ይመስለኛል:: ለዚህም ተግዳሮት ማስረጃነት በኽሪቴጅ ፋውንዴሽን (Heritage Foundation) የ2012 የኢኮኖሚክ ነጻነት ኢንዴክስ (Economic Freedom Index) ሪፖርትን መጥቀስ ጠቃሚ ይመስለኛል:: ይህ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከ 184 አገራት 134ኛ በመሆን በአብዛኛው ነጻነት ካጡ አገራት (mostly unfree) ተርታ መመደቧን ያሳያል:: ደቡብ አፍሪካ 70ኛ ጋና ደግሞ 80ኛ በመሆን በመጠኑ ነጻ (moderately free )የሆኑ አገራት መሆናቸውንም ያስገነዝበናል::
ይህ ፉከራ ከሌላም አቅጣጫ ቢታይ የሚያዋጣ አይመስልኝም:: ኢትዮጵያ በእውነት በዕድገት ጎዳና እየገሰገሰች ከሆነ ምን ወሬ ማራገብ ያስፈልጋል? ውጤቱ ካለ ራሱ ይናገር አልነበረምን? ባለቤቴ ሁል ጊዜ “ ሙያ በልብ ነው” የምትለው ብሂል ለዚህ የሚስማማ ይመስለኛል:: እኔ እስከማውቀው ድረስ ሰሚውን እስኪ ሰለች ድረስ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዘገብኩ እያለ የሚለፍፍ ሌላ ሃገር ሰምቼ ወይም አንብቤ አላውቅ:: እልቁንስ በባዶ ሜዳ ተገኘ የሚባለው “የኢኮኖሚ ልማት” ያልጠበቅነው ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል ብዬ እፈራለሁ:: በቅርቡ ያነበብኩክት የዩናይትድ ኪንግደሙ ዘሰን3 (The Sun News Letter) ኒውስ “ኢትዮጵያውያን የምዕራባውያን ገንዘብ ከእንግዲህ አያስፈልገንም: የራሳችንን ሀብት መፍጠ እንችላለን” እያሉ ባሉበት ሁኔታ ከሩብ ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ገንዘብ በዕርዳታ መልክ ማፍሰስ ተገቢ አይደለም የሚል ክርክር መነሳቱን መጠቆም የስጋቴን ተአሚነት ያጠናክርልኛል ብዬ እገምታለሁ::
xanadu.three@gmail.com
No comments:
Post a Comment