Translate
Monday, October 22, 2012
ኃይለማርያም ከመድረሱ፤ የንፁሃንን ሕይወት መቀንጠሱ!
ኃይለማርያም ደሣለኝ ምስለኔ ነው። ዋናው ባለሥልጣን ገና በውል አልታወቀም። ለሽያጭ ገበያ እንደወጣ ፈረስ ተስፈኛ ገዢዎች ኃይለማርያምን ለሙከራ እየጋለቡት ነው። በእርግጠኝነት የሚታወቀው ኃይለማርያም ደሣለኝ ምስለኔ እንጂ ዋናው ባለሥልጣን አለመሆኑ ብቻ ነው። እሱም ይህን ተቀብሎታል። የኃይለማርያም አዲስ ጌታ ነጥሮ ባለመውጣቱ ከቀድሞ ጌታው የተረከባቸውን ሹማምንት ይዞ ይቀጥል ወይም ጥቂት ለውጦችን ያድርግ ለጊዜው በውል የሚታወቅ ነገር የለም። ምን ያህል ሥልጣን በእጁ እንዳለም እንኳንስ ሌላው ሰው እሱም አያውቀውም። የመኖሪያ ቤትም ስላልተለቀቀለት ገና ወደ ቤተመንግሥት አልገባም።
እንዲህ ብዙ ነገሮች ገና ያልለየላቸው ቢሆንም ኃይለማርያም የቀድሞ ጌታው የመለስ ዚናዊን “ሌጋሲ” ለማስፈፀም ሲል ከአሁኑ ኢትዮጵያዊያንን መግደል ጀምሯል።
ለካስ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ መጨፍጨፍ ነበር ኃይለማርያም ደሣለኝ ገና ከጠዋቱ ደጋግሞ “የኔ ሥራ የታላቁ መሪያችንን ሌጋሲ ማስቀጠል ነው” ሲል የነበረው!! እንዳለውም “የመሪውን ሊጋሲ” የሚያስቀጥል መሆኑን ከጅምሩ አሳየን።
የኃይለማርያም ደሣለኝ የምስለኔ አገዛዝ የመጀመሪያ ሰለባዎች ሙስሊም ምዕመናን ሆኑ። ቀኑም እሁድ ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ነበር። በደቡብ ወሎ በምትገኘው ገርባ ከተማ የሚገኙ ሙስሊም ምዕመናን በሣምንታት በፊት በተካሄደው የውሸት ምርጫ ባለመሳተፋቸው ሰበብ ተፈልጎ የጥይት ዝናብ ወረደባቸው። ምዕመናኑ በመስጊዳቸው ለመጠለል ሞከሩ፤ ግን አልቻሉም። የፓሊስ ልብስ የለበሱ የጦር ሠራዊት አባላት ምዕመናኑን በጭስ አፍነው በጥይት ቆሏቸው። እስካሁን ከአራት ያላነሱ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተረጋግጧል። የሟቾች ብዛት ከዚህም በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። ጥቂቶቹ ደሴ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና ርዳታ ያገኙ ቢሆኑም ብዙዎች ግን ይህንን እድል አላገኙም።
የኃይለማርያም የምስለኔ አገዛዝ አንድ ፓሊስ ተገድሎብኛል ቢልም እውነት ይሁን አይሁን እስካሁን ማረጋገጥ አልተቻለም። የቀድሞ ጌታው መለስ ዜናዊ ሰው በገደለ ቁጥር “ፓሊስ ተገድሎብኛል” ይል እንደነበረው ኃይለማርያምም ተመሳሳይ ውሸት መፈብረክ “የሌጋሲው” አካል አድርጎት ሊሆን ይችላል፤ ለጊዜው እርግጠኛው አልታወቀም።
በእርግጠኝነት የሚታወቀው ነገር በጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በገርባ ከተማ ከአንድ መቶ በላይ በሆኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሕይወት መጥፋት ወይም የአካል ጉዳት ያስከተለ ግፍ መፈጸሙ ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል፤ ለሟቾቹ ገነትን ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ መጽናናትን ይመኛል። ግንቦት 7 እነዚህ ውድ ኢትዮጵያዊያን ለመብቶቻቸው መከበር ሲሉ ከፍተኛውን የሕይወት መስዋትነት የከፈሉ ሰማዕታት አድርጎ ይመለከታል።
ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ እውነተኛ ሥልጣን ኖረውም አልኖረው ለወያኔ በምስለኔነት ለመሥራት ፈቅዶና ወዶ ገብቶበታልና በወገኖቻችን ደም ቀጥታ ተጠያቂ ነው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል። የይስሙላም ቢሆን ገና በሥልጣን ወንበር ላይ እንደተቀመጠ የንጹሃንን ደም ማፍሰሱ ኃይለማርያምን ልክ እንደ ቀድሞ ጌታው መለስ ዜናዊ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ኢትዮጵያ ያደርገዋል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የወያኔ ዘረኛና አምባገነን ሥርዓት ለሰብዓዊ መብቶች ግድ ይኖረዋል ብለን አያምንም። ወያኔ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ግድ እንዲኖረው ሊቋቋመው በማይችለው ኃይል መገደድ ይኖርበታል አሊያም ጭራሹን ሊወገድ ይገባል።
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እስካሁን በሰላማዊ መንገድ ወያኔ ለማስገንዘብና ለማንቃት ያደረጉትን ተጋድሎ ግንቦት 7 ያደንቃል። ከእንግዲህ ግን የማስገደዱ አለያም የማስወገዱን ሥራ በተቀናጀ መንገድ ካልሰራነው በስተቀር የሕዝባችን መገደል፣ መደብደብና መረገጥን ማስቆም አንችልም። ስለሆነም ግንቦት 7፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ – ሙስሊሙም ክርስቲያኑም – ለሰብዓዊ መብቶታችን መከበር በጋራ እንዲነሳ ጥሪ ያደርጋል።
በዚህ አጋጣሚም ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሙስሊም ወንድሞቹና እህቶቹን ጥረት በጥርጣሬ መመልከቱን ትቶ ለጋራ ድል በጋራ እንዲነሳ ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment