Translate

Saturday, October 27, 2012

“ቃሊቲ”ን በጨረፍታ – በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ክፍል ሁለት)



ቃሊቲን በጨረፍታ – ክፍል ሁለት

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

. . . እድሜዋ በግምት ወደ 50 የሚጠጋ፤ በክንዷ ላይ የአስር አለቃ ማዕረግ የለጠፈች (ሳጅን) በጥያቄ ታጣድፈኝ ጀመር፤ ለነገሩ በጥፊ ከመጣደፍ በጥያቄ መጣደፍ በብዙ የተሻለ ነው ብዬ ስለገመትኩ ያለቅሬታ ነበር የጠየቀችኝን ሁሉ የመለስኩላት፡፡ “ስምህ ማነው?” የተረከብሽበት ወረቀት ላይ አለልሽ ልላት አሰብኩና ተውኩት፡፡  በምትኩ ሙሉ ስሜን ነገርኳት፡፡

“ብሔርህ ምንድን ነው?” “እግዜር ይይልህ ኢህአዴግ!” በሆዴ ያልኩት ነው፡፡  በአፌ ግን እንደምንም ቀጣጥዬ እና ሰፋፍቼ ብሄሬን ተናገርኩ፡፡  መቼም በብሶት ተወልዶ ለበርካታ ብሶቶች መወለድ መንስኤ የሆነው ኢህአዴግ በእግዜር ፊት ለፍርድ ቢቀርብ (በሰው ፊት እንኳ ይቀርባል ብሎ ማሰቡ አዳጋች ነው) ከሚከሰስባቸው ክሶች መሀከል ዋነኛው ሀገሬውን በአያት ቅድማያቱ (አያት ቅድማያቱን የማያውቀውን ደግሞ በሩቅ ዘመዱ) በመከፋፈሉ ይመስለኛል፡፡  አማራ፤ ኦሮማ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ ሲዳማ፤ ወላይታ፤ ሐረሪ፤ አፋር . . .

የሆነው ሆኖ የሳጅን ጥያቄ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምን አስታወሰኝ፡፡ “ፕሮፍ” ከሚጠሉት ጥያቄ ሁሉ “በሔርዎት ምንድን ነው?” የሚል እንደሆነ አውቃለሁ፡፡  ዛሬም ድረስ የሚጠቀሙበት የቀበሌ መታወቂያ “ብሔር” የሚለው ቦታ ላይ “ኢትዮጵያዊ” የሚል ውድ ቃል ተጽፎበት ይገኛል፡፡  ይህ የሆነው ግን በቀበሌዎቹ በጎ ፍቃድ አይደለም፡፡  በፕሮፍ የማይታጠፍ ብርቱ ተቃውሞ እንጂ፡፡  እናም ከ80 ሚሊዮን ሕዝብ የቀበሌ መታወቂያም ላይ ሆነ የምርጫ ካርድ ላይ ብሔሩን ሳያጽፍ የወሰደ ብቸኛ ሰው ቢኖር ፕሮፍ ይመስሉኛል፡፡  እንዲያውም እርሳቸው ይንገሩኝ ከመጽሐፎቻቸው ወይም ከቃለ-መጠይቆቻቸው ላይ በአንዱ ላነበበው ማስታወስ ተሳነኝ እንጂ እንዲህ ብለው ነበር፡- “የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ አንድ መምህር ነበሩ፡፡  ሁልጊዜም ክፍል ገብተው ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት እናንተ ምንድር ናችሁ? ሲሉ ይጠይቁናል የሰው ልጅ ስንል እንመልስላቸዋለን፡፡  ይህ ሁኔታም ሶስት ጊዜ ከተደጋገመ በኋላ ነው ትምህርት የምንጀምረው፡፡”  እንግዲህ ፕሮፍ የሚሉን በአንድ ሀገር ውስጥ ተከልለው በአንድነት የሚኖሩ ሕዝቦች ሊተሳሰሩበት የሚችሉት “ሰው” በሚለው ክቡር ቃል ብቻ ነው፡፡

ኢህአዴግ ከዚህ አይነቱ አመለካከት ደም የተቃባ ነው፡፡  የሉሲ ዘሮች እንደሆንን ይደሰኩርልናል እንጂ አማራ የሚባል ዝንጀሮ፤ ኦሮሞ የሚባል ዝንጀሮ፤ ትግሬ የሚባለ ዝንጀሮ… የት እንደሚገኝ አይነግረንም፡፡  ስለዚህም የየብሔራችንን አባወራ ዝንጀሮ ካልነገረን በብሔር መከፋፈላችንንም አለመቀበል እንችላለን፡፡  ወይም “ሉሲ” የተሰኘችው ምንጅላታችን የዝንጀሮ ዝርያ አይደለችም የሚል ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ሊሰጠን ይገባል፡፡  ይህ ካልሆነ ግን እራሱ ኢህአዴግ አቶ መለስ እንደሚሉት (ነፍሳቸውን ይማረውና) አጥር ላይ ተንጠልጥሏል፡፡

መቼም ሳጅን ብሔሬን የጠየቀችኝ ልትጎዳው ወይም ልትጠቅመው የምትፈልገው ብሔር ኖሮ አይመስለኝም፡፡  ትእዛዝ ሆኖባት እንጂ፡፡  በነገራችን ላይ ቃሊቲ ያለው አድሎ እና መድሎ በብሔር ላይ የተመሰረተ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ወይም ለአጭር ጊዜ ብቻ በመታሰሬ ሳላስተውል ቀርቼ ይሆናል፡፡  ሆኖም በጥቂት ቀናት ቆይታዬ እንዳየሁት ከሆነ በቃሊቲ ያለው ግልጽ አድሎ እና መድሎ ተከዳሹ በፈጸመው ወይም በተጠረጠረበት ወንጀል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡  ለምሳሌ የሶስት አመት ሕጻንን አስገድዶ የደፈረ ወይም የሰው ገንዘብ ለመዝረፍ ሲል ንጹሐንን የገደለ ከየትኛውም ብሔር ቢመጣ ከእስረኝነት መብቱ ላይ ጥቂት እንኳ አይሸረፍበትም፡፡  በግልባጩ የተከሳሹ ወንጀል ከኢህአዴግ ጋር የተያያዘ አልያም መንግስትን አስከፍቶ ከሆነ እውነት እውነት እልሀለሁ ለእርሱ ቃሊተ የተረገመ ምድራዊ ሲኦል ነው፡፡  መብቱ ብቻ ሳይሆን ከራሱ ላይም አንዳች ነገር ሊጎድል ይችላልና፡፡  ለምሳሌ እስክንድር ነጋ ከቤተሰቡ ውጭ ሌላ ዘመድ ወዳጅ እንዳይጠይቀው ጽኑ እግድ ተጥሎበታል፡፡  አንዱአለም አራጌ፤ በቀለ ገርባ፤ ናትናኤል መኮንን እና ስማቸውን የማላስታውስው ሌሎቸ ለውጥ ፈላጊዎች የዚህ ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡  ርዕዮት አለሙ ደግሞ ጠያቂ ባይቀነስባትም የመጠየቂያ ሰአት ተቀንሶባታል፡፡ ርዕዮት አብረዋት እንደታሰሩ ሴቶች ከጠዋቱ ሶስተ ሰአት እስከ ስድስት ሰአት እንድትጠየቅ አልተፈቀደላትም፡፡  የርዕዮት መጠየቂያ ሰአት ከ6 ሰአት እስከ 6 ተኩል (ለ30 ደቂቃ) ብቻ ነው፡፡ እናም በየመንደሩ ሳይቀር የሚሹለከለኩ የባቡር መስመሮች እዘረጋለሁ፤ አባይን እገድባለሁ የሚለው ኢህአዴግ እንዲህ ነው፡፡  ግለሰብን ሳይቀር ለማበሳጨት፤ ለማማረር የማያንቀላፋ መንግስት፡፡  የዚህ ሁሉ መነሻ ደግሞ ታሳሪዎቹ ጸባቸው ከመንግስት ጋር ስለሆነ ብቻ እንደሆነ ደግሜ እነግርሃለሁ፡፡

“የምትሰራው ምንድን ነው?”

“ጋዜጠኛ ነኝ” ካቀረቀረችበት ቀና ብላ አየችኝ፡፡  እንደገና አይኗን ወደ ክስ ቻርጁ መለሰች፡፡  ደግማ ከላይ እስከ ታች ገረመመችኝ፡፡  አንዴ ወደ ክስ ቻርጁ፤ አንዴ ወደ እኔ እያፈራረቀች ስትመለከት ነገረ ስራዋ ግራ አጋብቶኝ “ምነው! ችግር አለ?” ስል ጠየኳት፡፡

“ምንም ችግር የለም፡፡” ጫን ባለ ድምጽ ቀጠለች

“ምን አድርገህ ነው የተሰርከው?”

“ክስ ቻርጁ ላይ አለልሽ ”

“ክስ ቻርጁ በደንብ አይገልጽም”

“ደጋግመሽ እይው፤ እኔም ለራሴ አልገባኝም ” ከፊት ለፊቷ ተቀምጦ በተመሳሳይ መልኩ አንድ እስረኛን እያናዘዘ ላለ ጎልማሳ ፖሊስ ክስ ቻርጁን አቀበለችው፡፡  እሱም ለደቂቃ ካተኮረበት በኋላ እንዳልገባው ገልጾ መልሶ እኔኑ ጠየቀኝ፡፡

“ለእኔም ግልጽ አይደለም” ለእርሷ የነገርኳትን ደገምኩለት፡፡ ይህን ጊዜ “ዝም ብለሽ ቻርጁ ላይ ያለውን ጻፊው” አላት፡፡  ሳጅኗም በክስ ቻርጁ መሰረት “የሰውን ሀሳብ ማናወጥ እና ማሳመጽ” በሚል መዘገበችው፡፡  የሰው ሀሳብ በምን ይሆን ያናወጽኩጽት፤

ከዚህ በኋላ አሻራ እንድነሳ ተደረገ እና ከሰባት እስረኞች ጋር ወደ ሌላ ክፍል ተወሰድኩ፡፡  በክፍሉ ውስጥ ያለው ፖሊስ ቁጡ ይመስላል፡፡  ገና ከመድረሳችን “ውጡ፤ ተሰለፉ….” በሚል ትእዛዛት በጩኸት አጣደፈን፡፡  ይኸው ፖሊስ በረድፍ አሰልፎን ሲያበቃ በየተራ እያስገባ ፎቶ እንድንነሳ አደረገና ግዴታውን ጨርሶ ወደ ሌላ ክፍል አስገባን፤ አሁን የተረከብን ፖሊስ ደግሞ “ፈታሽ” ነው፡፡  የያዝናትን እያንዳንዷን እቃ ልምድ ባካበቱ እጆቹ በጥንቃቄ በርብሮ ሲያበቃ ኪሶቻችንን ፈተሸ እና ስራውን ጨረሰ፡፡   እነዚህ ሂደቶች የሚያጥሩት እንዲህ በአጭሩ ሲተረኩ እንጂ ሲተገበሩማ ከአንድ ሰአት ከግማሽ በላይ ይወስዳሉ፡፡

ከዚህ በኋላ የቀረው በቦታው ያለነውን እስረኞች ወደ መታሰሪያ ቤት ማስገባት ነውና ሰባቱን እየነዱ ከወሰዱ በኋላ ለእኔ “አንተ እዚሁ ቆይ!” የሚል ፖሊሳዊ ትእዛዝ ሰጡኝ፡፡  ሁኔታው ግራ ቢያጋባኝም እንደታዘዝኩት ክፍል ውስጥ በለአግዳሚ ወንበር ላይ አረፍ ብዬ ከእስረኞች ለምን እንደተለየሁ አና ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማንሰላሰል ጀመርኩ፡፡  እንዲህ እያንሰላሰልኩ ለካስ እንቅልፍ ወስዶኞ ኖሯል፡፡  እናም በግምት ከአንድ ሰአት በኋላ “ተነስ!” የሚል የፖሊስ ትእዛዝ ከሸለብታዬ አናውጦ ቀሰቀሰኝ፡፡  እቃዬን ይዤ እንድወጣ ተነገረኝ፡፡  እኔም ወጣሁ፤ መጀመሪያ ከሳጅን ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ያገኘሁት ፖሊስ እየመራ እኔ እየተከተልኩ አንድ አነስተኛ ግቢ ጋ ስንደርስ “እዚህ ጋ ቁጭ በል” ብሎኝ እርሱ ወደ ግቢው ውስጥ ገባ፡፡  (በነገራችን ላይ ቃሊቲ እጅግ በጣም ሰፊ ግቢ ቢሆንም ውስጡ በበርካታ ግቢዎች የተከፋፈለ ነው) ጥቂት ቆይቶ ተመልሶ መጣ፡፡  እኔን አልፎም ከግቢወ በር ፈንጠር ብለው ወደቆሙ ሁለት “ኮማንደሮች” አጠገብ ሄዶ ወደ እኔ አቅጣጫ በጣቱ እየጠቆመ የሆነ ነገር ነገራቸው፡፡  ኮማንደሮቹም ለደቂቃ ያህል ከተመለከቱኝ በኋላ ፖሊሱ የሚነግራቸውን ማዳመጥ ጀመሩ፡፡  በእኔ ጉዳይ እየተነጋገሩ እንደሆነ ቢገባኝም ምን እያሉ እንደሆነ ላውቅ አልቻልኩም፡፡  ከሁኔታቸው ግን አንድ ያልተግባቡበት ጉዳይ ያለ ይመስለኛል፡፡  ከትቂት መወዛገብ በኋላ ሰውነቱ ደንደን ያለው ኮማንደር በመገናኛ ራዲዮኑ ተነጋግሮ ሲያበቃ ወደ እኔ ተጠግቶ ከፊት ለፊት ባለው የጥበቃ ማማ ላይ የተቀመጠውን ፖሊስ ጠርቶ በቁጣ ይፈትሸኝ ዘንድ አዘዘው፡፡  ይህ ኮማንደር ከፍርድ ቤት የተረከበውን እስረኛ ሳይሆን በከባድ ውጊያ ላይ የማረከውን ጠላቱን የሚያናግር እስኪመስል ድረስ ምንጭቅጭቅ አደረገኝ፡፡  በምን ተከስሼ እንደመጣሁና ማን እንደሆንኩ ይዞኝ የመጣው ፖሊስ ሳይነግረው አልቀረም፤ እንደ ክፉ ባላጋራው አየኝ፡፡  በድጋሚም እቃዬ ተመነቃቅሮ እና ኪሴ ተበርብሮ ተፈተሸ፡፡  ኮማንደሩ ፍተሻውን በጥንቃቄ እየተከታተለ ነው፡፡  ፈታሹ ፖሊስ ከያዝኩት ፌስታል ውስጥ ቲሸርቶችን ማውጣት ሲጀምር “ቲ-ሸርቶቹ ጽሑፍ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው አረጋግጥ”  ሲል ኮማንደሩ ተእዛዝ ሰጠ፤ መቼም ኮማንደር በያዝኩት ቲ-ሸርት ላይ “ስሜ ተጠቅሶ እረገማለሁ” ወይም “እወገዛለሁ” ብሎ እንደማያስብ ስለማውቅ ምን አይነት መልእክት ያለው ጽሑፍ ከቲሸርቶቼ ላይ እየፈለገ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡  ፍተሻው እንዳለቀ “እቃህን ሰብስብና ተከተለኝ!” አለ-ከመሬት ተነስቶ የጠላኝ ኮማንደር፡፡  ጓዜን እንደምንም ሸካክፌ ተከተልኩት፡፡ ከላይ የጥበቃ ማማ ያለበት ከሲሚንቶ የተሰራ ቤት ጋ ስንደርስ ቆመና ከኪሱ ቁልፍ አውጥቶ ከፈተው፡፡  ሶስት በሶስት የምትሆን ኦና ቤት፡፡  “ግባ!” ከአስደንጋች ቁጣ ጋር ተያይዞ የመጣው የኮማንደር ትእዛዝ፡፡

ባዶዋ ክፍል ከገባሁባት በኋላ በሯ ከውጭ ሲዘጋ ሙሉ በሙሉ አይንን በሚወጋ ጨለማ ተዋጠች፡ ከጨለማው በተጨማሪም ክፍሏ አንዳች ክፉ ሽታ አውዷታል፡፡ ምንድር ነው የሚሸተው? እነዚህ ሰዎች እደደርግ ዘመን ሰው እየገደሉ ይቀብራሉ እንዴ ብዬ በውስጤ አሰብኩ፡ በእርግጥ ደርግ የአፄ ሃይለሥላሴ ባለሥልጣናትን እና ‹‹ፀረ አብዮተኛ›› ያላቸውን ወጣቶች ከርቸሌ ግቢ ውስጥ ገሎ እንደነበርና ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ አፅማቸው በቁፋሮ እንደወጣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሰማሁት ወሬ ድንገት ትዝ ብሎኛል፡፡ ሆኖም ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ ፍራሼን አንጥፌ ጋደም አልኩ፡፡ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ሽታውንም ጨለማውንም ለመድኩት ከውጭ የዘቦቹ ኮቴ በጥበቃው ማማ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ይሰማል፡፡ በመፅሐፍ ቅዱሱ ያዕቆብ በበረሃ ተኝቶ መላዕክት ሲወጡና ሲወርዱ አየበት የተባለው መሰላል ትዝ አለኝ፡ በዚህ አይነት ሁኔታ በግምት ለሰዓታት ከቆየሁ በኋላ ቀን ፍርድ ቤት ከአንበሳ ቤት የእስር ጓደኛዬ ጋር ተካፍዬ ከበላሁት በርገር ውጭ ምንም እንዳልበላሁ ትዝ ሲለኝ ረሃብ ሞረሞረኝ፡፡ እናም በያዝኩት ፌስታል አንዳች የሚበላ ነገር እንዳለ ስለማውቅ ከተጋደምኩበት ተነስቼ ፈታተሽኩ፤ በርገር አገኘሁ፡፡ አወጣሁት ሁለቴም እንደገመጥኩት በጨለማ መብላቱ እንደ አንዳች ነገር ስለቀፈፈኝ የታሰርኩበትን ክፍል በር መደብደብ ጀመርኩ፡፡ ከውጭ ያለ ፖሊስ

‹‹ምን ፈለክ?›› አለ በአስገምጋሚ ድምፅ

‹‹በሩን ክፈትልኝ››

‹‹ለምን?››

‹‹በጨለማ እራት መብላት አልቻልኩም››

‹‹ተወውና ተኛ አይከፈትም››

ይህን ጊዜ አዕምሮዬ ወደ ህንድ ይዞኝ ነጎደ፡፡ መፅሐፉን ባላስታውሰውም አንድ ያነበብኩት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በሒንዱ ሃይማኖት ጀንበር ካዘቀዘቀች በኋላ ምግብ አይበላም፡፡ ይህ ከእምነቱ ትዕዛዝ አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በጨለማ ሲበላ ነፍስ ያለው ነገር ከምግቡ ጋር ተደባልቆ ነፍስ እንዳይጠፋ ለሃይማኖታዊ ጥንቃቄ ነው፡፡ እኔ ግን እንዳው ሳላውቀው በጨለማ መብላቱን ጠላሁት፡፡ እናም ፖሊሱ እንዳለው ትቼው እንደራበኝ ተኛሁ፡፡ የሚያነጋግሩት ሰው ሳይኖር ያውም በጨለማ የተዋጠ ክፍል ውስጥ ለብቻ መሆን እንዴት ይጨንቃል?

መቼና እንዴት እንቅልፍ እንደወሰደኝ አላወኩም፡፡ ብቻ የጨለማ ቤቷ በር ተንኳኩቶ ተከፈተና ለሽንት እንድወጣ ተነገረኝ፡ በማረሚያ ቤቱ ደንብ የእስረኞች ክፍል የሚከፈተው ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ሲሆን የሚዘጋው ደግሞ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ነው፡፡ የጨለማው ክፍል እስረኞች ግን ሌላ እስረኛ ከመውጣቱ በፊት ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት ለሽንት እንወጣለን፡፡ እኔ በዚህ ሰዓት እንድወጣ የተፈለገው እስረኞች ከክፍላቸው ሳይወጡ ነው፡፡ ነገርየው ማንም እስረኛ እንዳያየኝ ለማድረግ ነው፤ ማታም ለሽንት የሚከፈትልኝ እስረኞች በየክፍላቸው ከገቡና በር ከተዘጋ በኋላ ነው፡፡ እናም ለጥቂት ደቂቃ መጸዳጃ ቤት ተጠቅሜ ፊቴንም እንደነገሩ በውሃ አስነክቼ ወደ ክፍሌ ተመለስኩ ፡ በሩ ከውስጥ ወደውጭ ተስቦ ተዘጋ ጨለማውም መልሶ በእኔ ላይ ነገሰ፡፡

የሆነ ሆኖ ብዙም ሳይቆይ በአንደኛው መስኮት በኩል በምስማር በተበሳች ቀጭን ቀዳዳ ብርሃን ሲገባ አየሁ፡፡ አይኔን ወደቀዳዳው አስጠግቼ ወደውጭ ለማየት ሞከርኩ፤ ብዙም አልተሳካልኝም፡፡ ተውኩትና ክፍሉ ውስጥ ‹‹ወክ›› ማድረግ ጀመርኩ፡ ጥቂት ከቆየሁ በኋላ ጨለማው አይኔን ስለወጋኝ ፍራሼ ላይ ተጋደምኩ፡፡ ጨለማ ቤት የመታሰር ቅጣቱ በጨለማ የመከበብ ዕዳ ብቻ አይደለም፡ ጨለማው ከመግዘፉ የተነሳ አይንህ መስራትና አለመስራቱን ማረጋገጥ ይሳንሃል፡፡ እንዲሁ ተዳፍኖ የሚቀር ሲከፈትም የማታይ እስኪመስልህ ድረስ የአይንህን ብርሃናማነት ትጠራጠራለህ፡፡ ማረጋገጫህ ምንድን ነው? ምንም! አንዲትም የብርሃን ሰበዝ ተሰርቆ በማይገባበት ልስን ጨለማ ማረጋገጫህ ምንድን ነው? በተስፋ መቁረጥ እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ፤ ምን ያህል ሰዓት እንደተኛሁ ሳላውቅ በሩ ተከፈተና አንድ ፖሊስ ከቤተሰቦቼ የተላከ የምሳ ሳህን ሰጥቶኝ በሩን ዘግቶ ተመልሶ ሄደ፡፡ ጥቂት ቆይቼ በሩን ደበደብኩ

‹‹ምንድን ነው?››

‹‹ሰዓት ስንት ነው?››

‹‹ሃያ ጉዳይ››

‹‹ለስንት?››

‹‹ለስድስት››

ሳህኑን ከፍቼ ለመመገብ ሞከርኩ ግን አሁንም አልቻለኩም፤ ከዚህ በፊት ተሞክሮው ስላልነበረኝ በጨለማ መመገብ እንደሚከብድ አላውቅም ነበር፡፡ ጥቂት ጉርሻዎችን በውሃ አምጌ ከጎረስኩ በኋላ የበረሮ ድምጽ ስለሰማሁ ተውኩትና እስከ አሁን ምን ያህል በረሮ ከምግቡ ጋር ቀላቅዬ እንደጎረስኩ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ከሃሳቤ ሳልላቀቅ እንቅልፍ አሸነፈኝ፡፡ ስነቃ በጣም ብዙ ሰዓት እንደተኛሁ እርግጠኛ ስለሆንኩ አሁንም በሩን ከውስጥ ወደውጭ ደበደብኩ

‹‹ምን ፈለክ?›› አለኝ የቅድሙ ድምፅ

‹‹ሰዓት ስንት ነው?››

‹‹ጤና የለህም! አሁን ጠይቀኸኝ ነግሬህ የለ እንዴ?››

‹‹አሁን አይደለም የጠየኩህ፡ ለስድስት ሃያ ጉዳይ ላይ ነው››

‹‹ታዲያ አሁን ስድስት ሰዓት ተኩል እኮ ነው››

‹‹ይቅርታ እንቅልፍ ወስዶኝ ስለነበር ብዙ ሰዓት የተኛሁ መስሎኝ ነው››

መልስ የለም፤ ለራሴ ፈገግ አልኩ፡ ለካስ ሃምሣ ደቂቃ ተኝቼ ነው እንዲህ ብዙ ጊዜ ያለፈ የመሰለኝ!. . . . የሚነበብ ነገር አልያዝኩም ብቸኝነቱ ደግሞ ሊውጠኝ ደርሷል፤ የክስ ቻርጄን አነሳሁና ሚስማር ወደበሳት ቀዳዳ አስጠግቼ አንድ አንድ ፊደል ላይ እያነጣጠርኩ ማንበብ ጀመርኩ፤ በዚህ አይነት መልኩ አንድ አራቴ ደጋግሜ ካነበብኩ በኋላ ግን ጨለማው ብዥ አለብኝና ምንም ነገር ማየት ተሳነኝ፤ በጣም ደነገጥኩ፤ እንደምንም በዳሰሳ ፍራሼ ላይ ሄጄ ተኛሁ፡፡ ያ የአይኔ ብርሃን ጥርጣሬ መልሶ ተቆጣጠረኝ፡ ስጋት! አይን ያለ ቅንጣት ብርሃን ተራ ብልቃጥ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ከተጋደምኩበር ተነሳሁ፡፡ መልሼ ተኛሁ፡፡ በዚህ አይነት ድግግሞሽ ቀኑ መሸና ለሽንት ተከፈተልኝ፡፡ ተመስገን! አይኔ ብርሃን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ህልው መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡ ከሽንት ቤት መልስ ደግሞ መልሶ ተዘጋብኝ፡፡ ሌሊቱም እንዲሁ ስቆም ስተኛ አለፈ፤ እናም ወፍ ጭጭ ሳይል ለሽንት ተከፈተልኝ፡፡ ወጣሁ፤ ተመልሼ ገባሁ፡ ይህን ጊዜ የዝነኛው አሽሙረኛ አቤ ቶኪቻው ‹‹ከምገባ ወጣሁ›› ፅሁፍ ውልብ አለብኝና ድንገት ደርሶ ፈገግ አሰኘኝ፤ የጨለማ ፈገግታ. . . .

ዛሬ እለቱ ቅዳሜ ነው፡፡ በተለምዶ እስረኞች በወዳጅ ዘመድ በብዛት የሚጠየቁበት ቀን፡ የእስረኞች ሳምንታዊ ‹‹አውደአመት››፤ በጉጉት የሚጠበቅ እለት፡፡ በግምት ወደ ሦስት ሰዓት ላይ የእስር ቤቱ የበር ቁልፍ ጥቂት ተንጓጉቶ ወለል አለ፡፡ ግራ ገባኝ! ስንቅ የሚመጣበት ሰዓት አልደረሰም፤ ለምንድር ነው የተከፈተው? ስል አሰብኩ፡፡ አንድ የፖሊስ ሃላፊ በፍራሼ ላይ እንደተንጋለልኩ ጥቂት ካስተዋለኝ በኋላ

‹‹ዕቃህን ይዘህ ውጣ›› አለኝ፡፡

‹‹ወዴት ነው የምወጣው?›› ስል ጠየኩት

‹‹ዝም ብለህ ያዝና ተከተለኝ››

ዝም ብዬ ወዴት ነው የምከተለው? እነዚህ ሰዎች ምን ሊያደርጉኝ ነው? ቀይ ሽብር ሊያፋፍሙብኝ? ወይስ. . .  የተለያዩ ሃሳቦች በውስጤ ተመላለሱ፡፡

ይቀጥላል . . .

No comments:

Post a Comment