ህዝበ ውሳኔ በብቸኛ አማራጭነት ቀረበ!
የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አወጪ ግንባር /ኦብነግ/ እና ኢህአዴግ ጀምረው የነበሩት ድርድር መጨናገፉ ታወቀ። ድርድሩ የተጨናገፈው በኢህአዴግ በኩል በቀረበ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ተገልጿል። መግለጫው ለሁለት ተከታታይ ቀናት ስለተደረገው ንግግር በዝርዝር ሳያብራራ ህዝበ ውሳኔን በመፍትሄነት አስቀምጧል። 74 ንጹሃንን የገደሉት የኦብነግ ሰዎች ጉዳይ በድርድሩ ስለመካተቱ እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።
ኦብነግ በድረገጹ ኦክቶበር 17 ቀን 2012 በይፋ እንዳስታወቀው የሰላም ድርድሩ የተጀመረው የኢትዮጵያ መንግሥት ለኬኒያ መንግስት ባቀረበው የአሸማግሉኝ ጥያቄ መሰረት ነበር። በዚሁ ጥያቄ መሰረት የኬንያ መንግስት አሸማጋዮች ለግንባሩ አመራሮች ጥያቄውን አቅርቦ ቀና ምላሽ በማግኘቱ የመጀመሪያ ደረጃ ንግግር ተደርጎ ነበር።
የግንባሩ አመራሮች በቀናነት የድርድር ሃሳቡን ተቀብለው እንደነበር ያስታወቀው መግለጫ የመጀመሪያው ንግግር በድርድሩ መርህ፣ ቅርጽና አጠቃላይ የመደራደሪያ አጀንዳዎች ዙሪያ መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር አስታውሷል። በዚሁ መነሻ ኦክቶበር 15 እስከ 17 በተደረገው ሁለተኛ ንግግር ላይ ቀደም ሲል ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ለማካሄድ የተደረሰውን ስምምነት ኢህአዴግ ጥሶታል።
በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑካን “ኦብነግ በቅድሚያ ህገ መንግስቱን መቀበል አለበት” በማለት ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ በመግለጫው ተወስቷል። ድርድር ለማካሄድ ያመች ዘንድበተደረገው የመጀመሪያ ንግግር ሁለቱም ወገኖች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የሰላም ድርድሩን የሚያሰናክሉ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው ለመነጋገር ተስማምተው ሳለ ከኢትዮጵያ ወገን በቀረበ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ሳቢያ የሰላም ድርድር ለማካሄድ የተጀመረው ጥረት መቋረጡን አስታውቋል። በማያያዝም አቋሙን ይፋ አድርጓል። ግምባሩ በጥቅል በቀረበለት ቅድመ ሁኔታ ሳቢያ የሰላም ድርድሩን መጨናገፍ ሲያስታውቅ ሰነድ ሰንቆ ማሰረጃ አደራጅቶ ለሁለት ቀናት በናይሮቢ ስለተካሄደው ድርድር ዝርዝር ጉዳይ ዝምታን መምረጡ ለድርድሩ መቋረጥ ተጨማሪ ምክንያቶች እንዳሉ አመላካች ነው ተብሏል።
“በእኛ እምነት” ሲል የግንባሩን አቋም ያስታወቀው መግለጫው በኦብነግ እምነት በኦጋዴን ውስጥ ያለው ግጭት መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው የክልሉ ህዝብ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታና ገደብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸውን እንዲጠቀሙ ሲደረግ ብቻ ነው። ግንባሩ በዚህ መሰረታዊ እምነቱ ሳቢያ ለድርድር የቀረበለትን አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ አለመቀበሉን ይፋ አድርጓል። በመጀመሪያው ንግግር መሰረት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የሰላም ድርድሩ ቢቀጥል ፈቃደኛ እንደሆነም አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኦክቶበር 17 ቀን 2012 ኦብነግ ድርድሩ መጨናገፉን ይፋ ሲያደርግ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለተወካዮች ምክር ቤት ስም ሳይጠቅሱ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ድርድር በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በማብራሪያቸው ተቃዋሚዎችን ያወገዙት አቶ ሃይለማርያም መንግስታቸው ለመቻቻልና ለሰላም ያለውን ቁርጠኛነት ባስታወቁበት የንግግራቸው ክፍል ከቶውንም የማይደራደሯቸው ክፍሎች እንዳሉ አስታውቀዋል። እርስ በርሱ በሚጋጨው ገለጻቸው ስለ ሰላምና ስለ ኃይል እርምጃ አይቀሬነት ከማስጠንቀቂያ ጋር መልዕክት ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትሩ በተለይ ስለ ኦብነግ በስም ጠቅሰው የተናገሩት ነገር የለም።
በኦጋዴን፣ ከደገሃቡር 19 ኪ/ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ኢቦሌ የነዳጅ ፍለጋ ስራ ላይ በተሰማሩ 68 የኢትዮጵያ፣ 9 የቻይና ዜጎች ላይ አፕሪል 24/2007 በድንገት ለደረሰው ጭፍጨፋ ኦብነግ ሃላፊነቱን መውሰዱ አይዘነጋም። በ74ቱ ያልታጠቁ ሲቪል ሰራተኞች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎ በተደረገ አሰሳ መንግስት ወንጀሉን በዋናነት በማስተባበር ፈጽመዋል ያላቸውን ዘጠኝ ሰዎች በቁጥጥር ስር በማዋል በሶማሌ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ በሞት ፍርድ እንዲቀጡ መወሰኑም አይዘነጋም። ይሁንና ኢህአዴግ ከሁለት ዓመትተኩል በፊት ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር አንድ ክንፍ ጋር ሰላም ማውረዱን ይፋ ባደረገበት ወቅት አቶ አባይ ጸሃዬ በሸራተን አዲስ መግለጫ ሲሰጡ “ … በስምምነቱ መሰረት የታሰሩና በህግ ለሚጠየቁ ምህረት ይደረጋል። የሚታየው የወደፊቱ ዘለቄታዊ ሰላም ነው” በማለት ሞት የተፈረደባቸው በድርድሩ አስገዳጅነት እንደሚፈቱ አስታውቀው ነበር። የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ፍርደኞች ከሶማሌ ክልል ወህኒ ቤት ወደ ዝዋይ ተዛውረው፣ ቤተሰቦቻቸውም ዝዋይ ከተማ ቤት ተከራይተው እየጎበኟቸው መሆኑን ከጎልጉል የኦሮሚያ ፖሊስ ምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
ፍርደኞቹ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ጨለማ ክፍል ውስጥ በልዩ ጥበቃ ለተወሰነ ጊዜ ከኖሩ በኋላ ቤተሰቦቻቸውን የሚያነጋግሩበት የተለየ ኮሪደር ተዘጋጅቶላቸው ከሁሉም በተሻለ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ መደረጉን የዓይን ምስክሮች ይናገራሉ። አዲስ ተጀምሮ የተሰናከለው ድርድር እነሱን ስለማካተቱ እስካሁን ከኦብነግ በኩል የተባለ ነገር የለም። ከመንግስት ጋር ስምምነት ላይ የደረሱትን ክፍሎች አስመልክቶ ኦብነግ ውስን ወታደር ያላቸው አነስተኛ አፈንጋጮች በሚል ግንባሩን እንደማይወክሉ በተደጋጋሚ መግለጹ አይዘነጋም።
No comments:
Post a Comment