Translate

Monday, October 15, 2012

የመጀመሪያው የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን ጉባኤ በቨርጂኒያ ተካሄደ


ኢሳት ዜና:-የመጀመሪያው የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን መራጮች ጉባኤ በአሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ ተካሄደ።
ትናንት እሁድ፤ መስከረም 4 ቀን በተካሄደው ጉባኤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከተለያዩ የአሜሪካን ከተሞች የመጡ ኢትዮጵያዊያን የተገኙ ሲሆን፤ ለኮንግረስና ለሲቲ ካውንስል የሚወዳደሩ እጩዎች ቀርበው ንግግር አድርገዋል።
ኮንግረስማን ሞራን ግሪፊዝ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር እንደሚረዱ ገልጸው፤ ከኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
የአሌክሳንድሪያው ከንቲባ ዊሊያም ዲ ኢዩልም ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን በአካባቢያቸው በሚገኙ በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ውስጥ በተለያዩ መልኮች መሳተፋቸውን እንዲጨምሩ አሳስበው፤ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር በሚገናኙባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን ጉዳይ እንደሚያነሱ ቃል ገብተዋል።

ለዚህ ጉባኤ ከካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ ተጉዘው የመጡት የ”በቃ”ና የጉባኤው አስተባባሪ አቶ ዳኛቸው ተሾመም፤ በአሜሪካን ምርጫዎች ውስጥ መሳተፍ ለአገራችን ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም የተለያዩ ምሳሌዎችን በመስጠት አስረድተዋል።
የጉባኤው አዘጋጅ፤ “ቮት ፎር ፍሪ ኢትዮጵያ ዩኤስ” ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቅሶ፤ ይሄንን ቁጥር የሚመጥን ውክልና እንዲኖረን፤ ኢትዮጵያዊያን መደራጀትና መንቀሳቀስ አለብን ብሏል።
፤የኢሳት ቶምቦላ ወጣ፤ አሸናፊው 0889 ነው
በሌላ ዜና፤ የ2012 ቶዮታ ራቭ 4 መኪና የሚያስገኘው ቶምቦላ በኢትዮጵያዊያን ጉባኤ ላይ ወጥቶ አሸናፊው ቁጥር 0889 ሆኗል።
የመጀመሪያው እጣ ለኢሳት ቢወጣም የኢሳት አስተዳደር ቦርድ እጣው ትኬቱን ለገዙ ሰዎች መውጣት እንዳለበት በወሰነው መሰረት፤ ሁለተኛ ዙር እጣው ሲወጣ 0889 አሸናፊ ሆኗል።
አሸናፊው ሰው መኪናውን በማናቸውም ቀለም፤ ከየትኛውም ከተማ ሊረከቡ እንደሚችሉ ተጠቅሷል።

No comments:

Post a Comment