ኢሳት ዜና:-የህዝባዊ ወያን ሀርነት ትግራይ ንብረት የሆነውና ወ/ሮ አዜብ መስፍን በዋና ስራ አስኪያጅነት የሚመሩት ሱር ኮንስትራክሽን አመታዊ ገቢውን ከ1 ቢሊዮን 3 ሚሊዮን ወደ 2 ቢሊዮን 3 መቶ ሚሊዮን አሳድጓል።
ሱር ኮንስትራክሽን እየተባለ የሚጠራው የህወሀት ኩባንያ ባለፈው አመት 203 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ይህም አሀዝ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ማደጉን ብሉምበርግ ዘግቧል። ሱር በመንግስት ቁጥጥር ስር ከሚገኙት ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንና ከሜታል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሆነ የኮንትራት ስምምነት እንዳገኘ ብሉምበርግ ዘግቧል።
ሱር ኮንስትራክሽን ያገኘው ትርፍ ሌሎች የህወሀት ኩባንያዎች ለሆኑት አዲስ ለሚቋቋም የብረት ፋብሪካ፣ ለመሰቦ ስሚንቶ፣ መስፍን ኢንጂነሪንግ እና አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፈሰስ ይደረጋል። ኢፈርት የንግድ እንቅስቃሴውን ከውሀ ስራዎች ወደ ባቡር ግንባታ ለማዞር እቅድ እንዳለውም ተዘግቧል።
የኢፈርት ኩባንያዎች ገቢያቸው ለህዝብ ግልጽ እንደማይደረግና ከመንግስት ድጋፍ እንደሚያገኙ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ገንዘቡን ለፖለቲካ ስራ እንደሚያውለው የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተናግረዋል።
የህወሀት ኩባንያዎች የተቋቋሙት ከደርግ ጋር በተደረገው የ17 አመታት ጦርነት ከኢትዮጵያ ህዝብ በተዘረፈ ሀብት መሆኑን ተቃዋሚዎች ይናገራሉ። የኢፈርትም ሆነ የሌሎች ድርጅቶች ሀብት አንድም ቀን ኦዲት ተደርጎ ለህዝብ ይፋ ሆኖ አያውቅም።
ኢፈርት በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ኩባንያ እየሆነ መምጣቱን በአንድ ወቅት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ስብሀት ነጋ መናገራቸው ይታወሳል።
በወ/ሮ አዜብ መስፍን የሚመራው የህዝባዊ ወያን ሀርነት ትግራይ ንብረት ከሆኑት ኩባንያዎች መካካል ሰላም ትራንስፖርት፣ ሰገል ኮንስትራክሽን፣ መሜጋ ኔት ኮርፖሬሽን፣ ሀይቴክ ፓርክ አክሲዮን፣ ፋና ዲሞክራሲ፣ ኤክስፕረስ ትራንዚት፣ ኢትዮ ሬንታል፣ ዴልታ በሪዌሪ፣ ደሳለኝ ካተርነሪ፣ አዲስ ኮንሳልታንሲ፣ ብርሀኔ ቢዩልዲንግ፣ ሸባ ታነሪ ፋክተሪ፣ መስከረም ኢንቨስትመንት፣ ግሎባል አውቶ ሰስፔር ፓርት፣ ኤክስፒሪአንስ፣ አዲስ ኢንጂነሪንግ ሜካናይዜሽን፣ ብርሀኔ ኬሚካል አክሲዮን፣ ራህዋ የበግና ፍየል ኤክስፖርት፣ ስታር ፋርማሲዩቲካል፣ ተስፋ ላይቭ ስቶክ፣ አልመዳ ጋርሜንት፣ መስፍን ኢንዳስትሪያል፣ መሰቦ ሲሚንቶ፣ አልሜዳ ቴክስታይል፣ ሱር ኮንስትራክሽን፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ደደቢት ቭድርና ቁጠባ፣ ኢዛና የማእድን ልማት፣ አዲስ ፋርማሲዩቲካል፣ እንዲሁም ታና ትሬዲንግ ይገኙበታል።
No comments:
Post a Comment