Translate

Monday, October 29, 2012

ባለፉት 30 አመታት ከኢትዮጵያ ተዘርፎ ወደ ውጭ አገራት ባንኮች የተሻገረው ገንዘብ 450 ቢሊዮን ብር ደረሰ


ኢሳት ዜና:-አሜሪካ የሚገኘው የማሳቹሴትስ ዩኒቨርስቲ በያዝነው ወር ባወጣው አዲስ ጥናት ከኢትዮጵያ እየተዘረፈ ወደ ውጭ አገራት ባንኮች የተሻገረው ገንዘብ ባለፉት 30 አመታት ውስጥ 25 ቢሊዮን ዶላር ወይም 450 ቢሊዮን ብር መድረሱን ይፋ አድርጓል። ይህ አሀዝ  አገሪቱ ካላት አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 84 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው።

ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲተያይ የ8ኛ ደረጃነት ብትይም ነዳጅ ከማያመርቱ አፍሪካ አገሮች ጋር ስትወዳደር ደግሞ ቀዳሚ ሆናለች።

አብዛኛው ገንዘብ የሚዘረፈው ወደ ውጭ አገራት ከሚላኩና ከውጭ አገራት ከሚገቡ እቃዎች እንዲሁም በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ከሚልኩት ገንዘብ ነው፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ስፖንሰርነት ጥናቱን ያካሄደው ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ባለፉት 7 አመታት ከኢትዮጵያ ከ 11 ቢሊዮን ዶላር  ወይም ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ መዘረፉን ይፋ ባደረገ አመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ነው ማሳቹሴትስ ዩኒቨርስቲ አዲሱን አስደንጋጭ ሪፖርት ይፋ ያደረገው።


ከቻይናና ህንድ የተገኘውን ብድር ጨምሮ ኢትዮጵያ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ እዳ እንዳለባት መዘገባችን ይታወሳል።

ከኢትዮጵያ በሙስና እና በተለያዩ የንግድ ወንጀሎች  ወደ ውጭ አገር  የሚወጣው ገንዘብ በአገር ውስጥ ባንኮች ቢጠራቀም ኖሮ 3 የአባይን ግድቦችን፣  በመቶዎች የሚቆጠሩ ዩኒቨርስቲዎችን፣ ሆስፒታሎችንና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መስራት ይቻል ነበር።

በአጠቃላይ ከሰሀራ በታች ካሉ አገራት ከ800 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተዘርፎ  በውጭ አገራት ባንኮች መቀመጡ ተመልከቷል።

በአቶ መለስ የቀድሞው አስተዳዳር በኢትዮጵያ ታሪክ ተስምቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ገንዘብ ተዘርፎ በውጭ አገራት ባንኮች ተቀምጧል።

ውድ ተመልካቾቻችን በዚህ ዙሪያ ሰፊ ዘገባ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

No comments:

Post a Comment