Translate
Wednesday, October 31, 2012
የሙስሊም ችግር መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አዲስ የትግል ስልት መቀየሱን አስታወቀ
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ተወካዮች የ ኢህአዴግ መንግስት ከ ህገመንግስት እውቅና ውጭ በሀይማኖት ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ለማስቆም እና በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የአህባሽን አስተምሮ በግድ የሚጭንበት ፣ እንዲሁም በቅርቡ በወረዳዎች ባካሄደው ምርጫ ካድሬዎቹን በሙስሊሙ ላይ የሾመበትን ሁኔታ ለ አንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመግታት አዲስ ስልት መቀየሱን አስታውቋል።
እስካሁን በተደረገው መብትን የማስከበር ሁኔታ ህዝበ ሙስሊሙ የከፈለው መስዋትነት ታላቅ ነው ያሉት የኮሚቴው ተወካዮች ፣ ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ከማስተላለፍ ባሻገር በአዲስ አበባ፣ በአንዋር እና በቤኒ መስጊዶች ይደረግ የነበረው ተቃውሞ ተጠናክሮ በከተማዋ በሚገኙ መስጊዶች ሁሉ በፈረቃ በየሳምንቱ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቀዋል።
በክልል ከተሞችም በተወሰኑ መስጊዶች ብቻ ይደረጉ የነበሩ የመብት ማስከበር ትግሎች በክልሉ በሚገኙ ሁሉም መስጊዶች በየሳምንቱ በፈረቃ እንዲካሄድ ፣ የኮሚቴው ተወካዮችም ለህዝብ ሙስሊሙ ማህበረሰቡ ስለትግሉ በየወቅቱ እንደሚያሳውቁ ገልጠዋል።
ተወካዮቹ ለዚህ ውሳኔ ያበቃቸው በተወሰኑ መስጊዶች ብቻ ተጠናክሮ የቀጠለው የመብት ጥያቄ ውጤታማ ቢሆንም ፣ የኢህአዴግ መንግስት ሃላፊነት የማይሰማው በመሆኑ የበርካታ ሙስሊም ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ የጥቂቶች ብቻ በማስመሰል እና ለክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ደግሞ ስጋት እንደሆንን አድርጎ የፕሮፓጋንዳ ስራ እየሰራበት በመሆኑ ሰላማዊ የመብት ጥያቄያችንን እየሞትንም ቢሆን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሚገኙ መስጊዶች ለማሳየት ነው ብለዋል።
በየአካባቢው የሚገኙ ክርስቲያን እህቶችንና እና ወንድሞችን ሁኔታውን በቅርበት እንዲመለከቱት እና እኛ ለእነርሱ ስጋት ያለመሆናችንን ለማሳየት የኢህአዴግን መሰሪ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ለማጋለጥም ማሰባቸውን ተናግረዋል።
በየጊዜው ሳምንታዊው የጁማ ስግደት እና የመብት ጥያቄ የሚቀርብባቸውን መስጊዶች በየጊዜው በተለመደው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያሳውቁ አመራሮች ለኢሳት ዘጋቢ ገልጠዋል።
የኢህአዴግ መንግስት 29ኙን የሙስሊም አመራሮች በያዝነው ሳምንት ለፍርድ ማቅረቡ ይታወሳል።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment