አቶ ግርማ ለጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ዘለፋ መልስ ሰጡ
በተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መድረክ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ መድረክ የምርጫ ስነምግባር ኮዱን ላለመፈረሙ ያቀረቡትን ምክንያትና ዘለፋ አጣጣሉት። አቶ ግርማ ኦክቶበር 22 ቀን 2005 ዓ ም ከሪፖርተር ከጋዜጠኛ ዮሐንስ አምበርብር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት “ከአይ ዲ ኤ በቀጥታ ተቀዳ የተባለው የምርጫ ስነ ምግባር ኮድ ሁለት ፓኬጆች የተካተቱበት አይደለም” ብለዋል።
“ኢሕአዴግ ግን ነጥሎ ያመጣው አንዱን ነው፤ ቀሪ ሁለት ፓኬጆች አሉ፤ እነሱ ይጨመሩ ነው የምንለው፡፡ ምክንያቱም በጣም ጠቃሚ ስለሆኑ ጉዳዮች ነው የሚያስረዱት፡፡ ስለ ምርጫ አስተዳደር የመሳሰሉ፤ ነገር ግን አይፈልጉም፤ ምክንያቱም ምርጫ ቦርድ ወንድማቸውን ሊነካባቸው ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ጠንካራ አስተዳደር እንዲኖረው አይፈልጉም” ሲሉ ያልተካተቱትን ደንቦች አስፈላጊነት ያስታወቁት አቶ ግርማ ፓርቲያቸው በሁለቱ ፓኬጆች መካተት መከራከሩን አመልክተዋል።
“ኢሕአዴግ የሥነ ምግባር ኮዱን ደንብ ብሎ ይዞት ሲመጣ ደንብ የማውጣት ሥልጣን የላችሁም፡፡ ደንብ ማውጣት የሚችለው ምርጫ ቦርድ ነው የሚል አቋም ተይዞ ነበር፡፡ መድረኩን ራሱ ምርጫ ቦርድ ይምራው የሚል ክርክርና ሰነዱን የራሱ ያድርገው የሚል ክርክር ነበረው፡፡ ምክንያቱም ፓርቲዎች ደንብ የማውጣት ሥልጣን የለንም፤ ኢሕአዴግም አይችልም፡፡ ሐሳብ ማመንጨት ይችላል ነገር ግን ይህንን ሐሳብ ለምርጫ ቦርድ ነው ማቅረብ ያለበት፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ያንን ደንብ ማውጣት አለበት ብለን ነበር ስንከራከር የነበረው፡፡ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ አልተዘጋጀም አቅምም የለውም ነበር፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ በአቋራጭ አዋጅ አድርጐት አፀደቀው፡፡ አዋጅ ከሆነ ደግሞ አዋጁ ልክም ይሁን አይሁን ሁሉም ሰው ይገዛበታል፡፡ በዚህ ሕግ ላይ መፈራረም ለእኛ የማይረባ ነው የሆነብን፡፡ ምክንያቱም አዋጅ ሆኖ ወጥቷል፤ እንገዛበታለን፤ እንተዳደርበታለን፡፡ ነገር ግን አሁን ፈርሙ ሲባል ትርጉም አይሰጥም፡፡ እኛ የወንጀለኛ ሕግ ሲወጣ አልፈረምንበትም፤ ግን እንጠየቅበታለን፡፡ እንደዚህ ከሆነ እኮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰብስቦ በሕገ መንግሥቱ አምናለሁ እያለ መፈረም አለበት፡፡ ስለዚህ መፈረም ምንም ሥነ አመክኖአዊ ምክንያት የለውም፡፡ አለመፈረምም እንዲሁ ምክንያታዊ አይደለም” ሲሉ አቶ ግርማ የስነ ምግባር ደንቡን መድረክ ላለመፈረሙ አቶ ሃይለማርያም ያቀረቡትን ማብራሪያና ዘለፋ አጣጥለውታል። አቶ ግርማ አቶ ሃይለማርያም ፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ በሰጡት ወቅት በእስር ላይ ያሉትን አቶ አንዷለም አራጌን “የአገር ጀግና” በማለት ማወደሳቸው የሚታወስ ነው።
በጉዲፈቻ ስም አጭበርብሯል የተባለው እየታደነ ነው
በጉዲፈቻ ህጻናትን የሚያጓጉዙ ደላሎችና በህግ የተመዘገቡ ተቋማት እየፈጸሙት ያለው ተግባር በየጊዜው ቅሬታ የሚቀርብበት ነው። ህጻናት በጉዲፈቻ ከተሰጡ በኋላ ያሉበት አድራሻና የጤናቸው ሁኔታ እንደማይታወቅ፣ በድንበር በህገወጥ እንደሚሻገሩ፣ ከጉዲፈቻ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ተቋማት የመንግስት ሃላፊዎች ልጆቻቸውን ወደ ውጪ በመላክ፣ ገንዘብ በመቀበልና በዘመድ አዝማድ አማካይነት ከድርጅቶቹ ጋር በሽርክና በመስራት በህጻናት ንግድ ላይ ስለመሰማራታቸው በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ቢባልበትም እየተድበሰበሰ የሚታለፍ ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጸምበት ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር ነው።
ፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ በጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ኢትዮጵያን 18 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ አሳጥቷል ብሎ የጠረጠሩትን ዘ ግላድኒ ሴንተር ፎር አዶፕሽን የተባለ በአሜሪካ የቴክሳስ ግዛት የሚገኘው የማደጎ ድርጅት የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ የነበረውን አቶ በላይነህ ታፈሠ እያደኑ ነው፡፡ ሕፃናትን ወደ አሜሪካ በመውሰድ በማደጎ ለሚያሳድጉ አሜሪካውያን ለማቅረብ ከ125 ዓመታት በፊት የተቋቋመው ዘ ግላድኒ ሴንተር ፎር አዶፕሽን በተለያዩ ታዳጊ አገሮች ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ በኢትዮጵያም በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ ከገባ ከአሥር ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ሪፖርተር ጋዜጣ ኦክቶበር 28/2005 እንደዘገበው። በኢትዮጵያ በተመሳሳይ ህጻናትን በመነገድ የሚጠቀሙ ብዙ ናቸው።
አንድን ሕፃን ከኢትዮጵያ በማደጎ ለመውሰድ በኢትዮጵያ በኩል የሚያስፈልገው ወጪ 20 ሺሕ ዶላር እንደሆነ የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ድረ ገጽ ይገልጻል፡፡ አቶ በላይነህ ታፈሠ የማጭበርበር ወንጀሉን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረውም፣ አንድ ሕፃንን በማደጎ ለመውሰድ በሚቀበለው 20 ሺሕ ዶላር ምክንያት ነው፡፡ ግለሰቡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ ይላክ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እዚያው አሜሪካን ባለ የግል አካውንቱ ውስጥ እንዲቀመጥ በማድረግ ኢትዮጵያን 18 ሚሊዮን ዶላር አሳጥቷል ተብሏል፡፡ ዋናው መሥሪያ ቤት ሕፃናቱን ለመውሰድ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ኢትዮጵያ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ድርጅቱ የአገር ውስጥ የባንክ አካውንት ከመላክ ይልቅ፣ በግለሰቡ የአሜሪካ የግል አካውንት ውስጥ እንዲገባ አድርጓል በሚል ነው የተጠረጠረው፡፡ ፍትህ ሚ/ር ግለሰቡን ለመያዝ ክትትል እያደረገ ሲሆን በባለቤቱና በራሱ ስም የተመዘገቡ ተሽከርከሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ጨምሮ ተዘግቧል፡፡
የመለስ የኢኮኖሚ እድገት ቀመር አልታመነም
ዓለም ባንክ መንግስት አስመዝግቤዋለሁ የሚለው የአስራ አንድ ከመቶ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት ስሌቱ ሊገባው እንዳልቻለ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጉዋንግ ዚ ቼን መናገራቸዋን አዲስ ፎርቹንን ጠቅሶ ኢሳት ጥቅምት 16 ቀን 2005 ዓም ዘገበ። ዳይሬክተሩ የማዕከላዊ ስታስቲክስ መስሪያ ቤትን የአቅም ማነስ እንዳለበት አስታውቀዋል።
የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም IMF እና የዓለም ባንክ ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት የሚያወጡት መረጃና አሃዝ ተመሳሳይ መሆኑንን፣ ነገር ግን መረጃው ኢትዮጵያ ከምታወጣው አሃዝ ጋር ሊጣጣም አለመቻሉን የባንኩ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
የስታስቲክ አዘጋጁ ተቋም የአቅም ችግር ተቋም የብቃት ማነስ ሊሆን ስለሚችል ተቋሙን ለማጠናከር አስር ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የእቅድና የአቅም አለመመጣጠን ችግር መኖሩን ጠቁመዋል። በዚህም ሳቢያ መንግስት ከብሄራዊ ባንክ ሳይበደር ወይንም ገንዘብ ሳያትም በምን መልኩ እቅዱን እንደሚያሟላ አልታወቀም ብለዋል። ይህንኑ የገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት ብር ካተመ መጠነኛ መሻሻል ያሳየውን የዋጋ ግሽበቱን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያባብሰው ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ኢቲቪ “መሳቂያ!” ተባለ
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የኢድ አል አረፋን በዓልን እንደወትሮው በቀጥታ ባለማስተላለፉ ተወገዘ። በአዲስ አበባ በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ስታዲየም ሲጓዙ የነበሩ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የጸሎት ስርዓታቸውን ሲያካሂዱ ይዘውት በነበረው “ቢጫ የማስጠንቀቂያ ሪባን/ካርድ” ሳቢያ ቀረጻውን ቢያከናውንም አየር ላይ ለመዋል አልቻለም።
ፌደራል ፖሊስ በተደጋጋሚ ፍተሻ በማካሄድ ሊያገኘው ያልቻለው ቢጫ ካርድና የተለያዩ ጽሁፎች ጎልተው መታየታቸው ኢቲቪ ለፕሮፓጋንዳ የሚውል መረጃ እንዳያገኝ አድርጎታል። ይልቁኑም ከወትሮው በተለየ መልኩ በዜና እወጃው ከኦሮሚያ ቴሌቪዥን አገኘሁ ያላቸውን ፊልሞች የመቼ እንደሆነ ባይታወቅም ሲያስተላልፍ ታይቷል።
“ወኪሎቻችን ይፈቱና በመረጥነው መጅሊስ እንተዳደር” በሚል ድምጻቸውን የሚያሰሙትና የተለያዩ መግለጫዎች በማዘጋጀት ተቃውሞ የሚያሰሙት የእስልምና ተከታዮች አሁንም ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ ኢቲቪን እንደ ወትሮው ሁሉ አውግዘዋል።ኢቲቪ በአሉን አስመልክቶ ተቃውሞውን ቀንጨብ አድርጎ ለማሳየት ሞክሯል። እስካሁን በሚታየው የመረጃ ፍሰታቸውና የግንኙነት መስመራቸው በየትኛውም ቦታ የሚከሰተውን ተግባር በድምጽ፣ በስዕል፣ በፊልምና በጽሁፍ በማሰራጨት መንግስትን የሚያጋልጡት የእንቅስቃሴው አመራሮችና መላው ደጋፊዎቻቸው ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታላቅ ትምህርት እንደሆኑ አስተያየት እየተሰጠ ነው።
አዜብ መስፍን የቀበሌ ነዋሪ ሆኑ
ከቤተመንግስት አልወጣም በማለታቸው ጎልጉልን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛዎች ሲጎተቱ የከረሙት ወ/ሮ አዜብ መስፍን በሳምንቱ መጀመሪያ በግዳጅ በቪላ ቤት የቀበሌ ነዋሪ እንዲሆኑ መደረጉን ታወቋል።
በስፋት ሚዲያዎች የዘገቡት የወ/ሮ አዜብ የቤተመንግስት ስንብትና ሽኝት እንዴት እንደተከናወነ ባይገልጹም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ቤተሰቦቻቸው ወደቤተመንግሥት መዛወራቸው በታጣቂዎች ልዩ ጥበቃና በመንገድ መጨናነቅ ግራ ለተጋቡት የአቶ ሃይለማርያም ጎረቤቶች መልካም ዜና እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ወ/ሮ አዜብ በቪላ ውስጥ የሚኖሩ የቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፤ የኤርትራ የዘር ግንድ አለባቸው ተብለው የነበሩትና አቶ ሃይለማርያምን ጨምሮ የሚያውቋቸው ያስተባበሉላቸው ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ ወደ ቤተ መንግስት በመግባት ተክተዋቸዋል።
በሸራተን ጋዜጦች ተመርጠው ተሰናበቱ
“አስቂኝ ዜና ከሸራተን አዲስ” በሚል ርዕስ በሸራተን አዲስ ያጋጠመውን ክስተት የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፍሬው አበበ በግል በፌስ ቡክ ቤተ መረጃ ላይ አስፍሯል። ፍሬውን ያጋጠመው አስቂኝ ጉዳይ የተነሳው በሴቶች ብሄራዊ ቡድን አባላትን ሽኝት ወቅት ነው። “በዛሬዉ የሽኝት ፕሮግራም ላይ ከሚድያ እንዲገኝ የተፈቀደለት ETV ብቻ ነዉ” በማለት ጥሪ ለተደረገላቸው ጋዜጠኞች እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድንገት አስታወቀ። በዚህን ጊዜ የተባሳጩም የተሳለቁም ነበሩ።
“ባለፈዉ ጊዜ ሉሲዎች ወደ አፍሪካ ዋንጫ ካለፉ ከዚህ በፊት አይተዉት የማያቁትን ሽልማት እንደሚያቀርብ ፌደሬሽኑ ቃል ገብቶ ነበር፣ ይህ ጉዳይ የት ደረሰ?” በሚል ከሽኝቱ በፊት ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ያስታወሰው ፍሬው “በወቅቱ ከጋዜጠኞች ፊት ለፊት ለተሰየሙት መላሽ ብዙ የማይጥም ጥያቄ እንደነበር መገመት አላደገተኝም ነበር፡፡ሆኖም በወቅቱ የተሰጠኝ ምላሽ “ማታ ሸራተን ትሰሙታላችሁ” የሚል ነበር፡፡ ስለሆነም ከሸራተን በራፍ ብዙ ጋዜጠኞች የመመለሳቸዉ ምስጢር የዚህ ጥያቄ ምላሽ ከእናካቴዉ መጥፋቱ ይሆን?” የሚል ጥያቄ እንደጫረበትና ሚዲያን ከፋፍሎ አንዱን ማስተናገድ አግባብ እንዳልሆነ አመልክቷል። በአገራችን አብዛኛውን ጊዜ መረጃ ኢቲቪ እየተለየ፣ወይም የመንግስት ሚዲያዎች እየተመረጡ መረጃ የሚያገኙበት አግባብ የተለመደ ነው።ይህንን ልዩ የሚያደርገው የስፖርት ዜና ለማስተላለፍም ልዩነት መደረጉ ነው።
ርዕዮት ብርቱካን ሚደቅሳን ሰየመች
“የጀግና ጋዜጠኛ Courage in journalism” ሽልማት በማግኘት ሁለተኛዋ ኢትዮጵያዊ የሆነችው ርዕዮት አለሙ ሽልማቱን እንድትቀበልላት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ወክላለች።በእስር ወህኒ ቤት የምትገኘው የርዕዮት አለሙ እጮኛ ስለሺ ሐጎስን ጠቅሶ ሰንደቅ ጥቅምት 14 ቀን 2005 ዓ ም እንደዘገበው ርዕዮት አሜሪካን አገር ዘመድም ሆነ የቅርብ ጓደኛ ስለሌላትና ከወ/ት ብርቱካን ጋር የቀረበ ግንኙነት ስላላቸው ልትወክላት እንደቻለች አስታውቋል።
ስለሺ የእጮኛውን ሽልማት ለመቀበል ያልቻለው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ቪዛ ስለከለከለው እንደሆነ አስታውቋል። ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነው የሴቶች ሚዲያ ፋውንዴሽን ከዚህ ቀደም ለጋዜጠኛ እስክንድር ባለቤት ሰርካለም ፋሲል ይህንን ሽልማት መስጠቱ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment