Translate
Monday, October 29, 2012
ትንሽ ወግ ብጤ፤ የተቀበረው ባንዲራ “እየተከበረ” ነው
የኢትዮጵያ ባንዲራ በኢህአዴግ መንግስት አበሳውን ያየውን ያህል ማንም ጊዜ አበሳ አላየም ብንል ማጋነን አይሆንም። ማጋነነን ቢሆንም ማጋነን በኛ አልተጀመረም እና ወጋችን ይቀጥላል።
ባለፈው ጊዜ የዞን 9 ብሎግ ልጆች “የመለስ አስር የአፍ ወለምታዎችን” አስነብበውን ነበር። ከእነርሱ ውስጥም “ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አንድ ሰዓት ቁጭ ብሎ ማውራት ዩንቨርስቲ ገብቶ ከመውጣት እኩል ነው!” ብለው መለስ ኢሳያስን ያንቆለጳጰሱበት ካሳቁኝ መካከል ነበር።
ካሳቀቁኝ መካከል ደግሞ “ባንዲራ ጨርቅ ነው!” ብለው የተናገሩት ይጠቀሳል።
መለስ ባንዲራን ጨርቅ ብለው ያንቋሸሹትን ያህል ታድያ እድሚያቸው ወደ ሞት ሲቃረብ ፀፀት ተሰምቷቸው ነው መሰል የባንዲራ በዓል ይከበር ብሎ አንድ የተባረከ ሰውዬ ሲጠይቅ “እሺ” አሉ… አወጁም። ጎሽ…! ይኸው ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ ባንዲራ ቀን እየተከበረ ነው።
የባንዲራ ቀን ክብረ በዓል በአዋጅ ይከበር የተባለው መስከረም መጀመሪያው ላይ ቢሆንም የዛን ሰሞን ቀብር ነበረበት እና ሳይከበር ቀረ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዴ ሲዘቀዝቁት አንዴ ጨርቅ ነው ሲሉት የነበረው ባንዲራ የሞቱ ግዜ ደግሞ ይባስ ብሎ ከአስከሬን ጋር እንዲቀበር ተደረገ። ምስኪን ባንዲራ!
የሆነው ሆኖ፤ ዛሬ እነሆ ጨርቅ የተባለው፣ የተዘቀዘቀው እና የተቀበረው ባንዲራ “ሲከበር” ውሏል።
ባለፈው አመት ለአራተኛ ጊዜ ይሄ ክብረ በዓል ሲደረግ እኔም አዲሳባ ነበርኩ። በርካታ ሰው ነበር የተገኘው። ዛሬ ግን በኢቲቪ ዘገባውን ሳየው ስታድየሙ ባዶ ሆኖ አይቼው ለካስ ስታድየሙን የምናደምቀው እኛ ነበርን ስል አሽሟጥጫለሁ።
የምር ግን የዛሬ አመቱ የባንዲራ ክበረ በዓል ላይ ለመግባት ሲጋፉ ያየኋቸውን አንድ እናት “እናቴ ግፊያው ይጎዳዎታል ቀስ ብለን እንገባለን” ስለቸው ያሉኝ አይረሳኝም፤ “እኔማ ስም ጠሪዬ ያለበት ቦታ ልሁን ብዬ ነው ደግሞ አልገባችም ብሎ አበሌን እንዳይከለክለኝ!” ብለው አስቀውኛል።
በዘንድሮው በዓል የአበል እጥረት አለ መሰለኝ፤ ስታድየሙ ጭር ብሎ አይቼዋለሁ! ለማንኛውም ለባንዲራችን ክብር መስጠቱ ጥሩ ነው! ባንዲራችን ይከበር! የሚቀብረው ይቀበር! (ልበል እንዴ!?)
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment