Translate

Friday, October 19, 2012

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ዛሬም በአንዋርና በበኒ መስጊዶች ተቃውሞአቸውን አሰሙ


ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ በኢህአዴግ መንግሥት ደረሰብን ላሉት የሕገ-መንግሥትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዛሬ ከጁምዓ የጸሎት ፕሮግራም በኋላ ፒያሳ በሚገኘው የበኒ መስኪድ እና መርካቶ በሚገኘው አንዋር መስኪድ ተቃውሟቸውን ገለጹ፡፡
በከፍተኛ ቁጥር ፒያሳ በሚገኘው በኒ መስኪድ እና መርካቶ በሚገኘው አንዋር መስኪድ የተሰባሰበው የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ከጸሎተ ሥግደት በኋላ ለ30 ደቂቃ ያህል እጅ ለእጅ በመያያዝ አንድነታቸውን ያሳዩ ሲሆን፣ እጃቸውንም በመቆላለፍ የኢህአዴግ መንግሥት አፍኖናል- አስሮናል ያሉ ሲሆን እጃቸውን ያለ ድምጽ በማውለብለብ መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ እየገባ ካድሬዎቹን መሾሙን እና የአህባሽን አስተምህሮ ካልተቀበላችሁም የሚለውን የግፍ አካሄዱን እስካላቆመ ትግላችን ይቀጥላል ሲሉ በአካላዊ እንቅስቃሴ ተቃውሟቸውን መግለፃቸውን የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ተወካዮች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

ፒያሳ በሚገኘው በኒ መስኪድ የነበሩ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ድምፅ እያሰሙ በማጨብጨብ ተቃውሟቸውን ማሰማት ሲጀምሮ በአካባቢው አድፍጡ ሲጠባበቅ የነበረው ፌዴራል ፖሊሶች ስብስቡን ለመበተን ዳር ዳሩን ሙከራ ያደረጉ ሲሆን አንዳንድ ግለሰቦችንም እየያዙ አነጋግረዋል የታሰሩም ሊኖሩ ይችላሉ ሲሉ በቦታው ለነበረው ዘጋቢያችን አንድ ኢማም ገልጸዋል፡፡

በመርካቶ አንዋር መስኪድ  በመቶ ሺህዎች የሚቆጠረ የሙስሊም ማህበረሰብ በተቀናጀ ሁኔታ ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን በዖመር ሰመተር ትምህርት ቤት፣ በአራተኛ ፖሊስ ጣቢያ እና በመርካቶ ዙሪያ በትልቅ ካሚዮን መኪና ውስጥ ያደፈጡ ፌዴራል ፖሊሶች እንደነበሩ ዘጋቢያችን ተዘዋውሮ ያስተዋለ ሲሆን የኢህአዴግ የቀበሌና የወረዳ ካድሬዎችም ከደህንነቶች እና ከአንዋር መስኪድ አሰጋጅ ሸህ ጠሃ መሐመድ ሀሩን ጋር ሆነው አክራሪ ነው እያሉ ሰዎች ላይ ሲጠቁሙ ተስተውለዋል፡፡
ዛሬ ድምጽ የለሽ ተቃውሞ ነው ያካሄድነው በማለት ለዘጋቢያችን የገለጹት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ተወካይ በሚቀጥለው ዓርብ (ጁምዓ) አረፋ /ዒድ/ በመሆኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ለማድረግ ዝግጅታችንን አጠናቀናል፡፡ ምናልባትም ኢህአዴግ መንግሥት በቢጫ ካርዱ ራሱን ሊገመግምና ሊያስተካክል ባለመቻሉ ቀይ ካርድ ለማሳየት እንገደድ ይሆናል ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እንድሪስ ሙሀመድና ሙሀመድ የሱፍ የተባሉ ከሙስሊሙ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩ የኮምቦልቻ ነዋሪዎች ተፈትተዋል። ፍርድ ቤት ማስረጃ እንደሌለ በመግለጽ እንዲፈቱ ቢወስንም የወረዳው መስተዳድር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመገልበጥ ግለሰቦቹ ላለፉት 4 ወራት ፍትህ አጥተው እንዲታሰሩ አድርጓል።

No comments:

Post a Comment