Translate

Wednesday, October 10, 2012

በምእራብ ጎጃም ዞን አንድ የፌደራል ፖሊስ ጓደኛውን ጨምሮ 4 ሰዎችን ገድሎ 2ቱን አቆሰለ


ኢሳት ዜና:-የኢሳት ምንጮች እንደተናገሩት ድርጊቱ የተፈጸመው በአማራ ክልል፣ በምእራብ ጎጃም ዞን፣ በሽንዲ ከተማ እሁድ መስከረም 28፣ 2004ዓም ነው።
የአይን እማኞች ለኢሳት እንደገለጡት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች  ትንሳኤ በሚባለው ሆቴል ውስጥ የባሪሴሎና እና የሪያል ማድሪድን ኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት፣  አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል ህዝቡን በማስተናገድ ላይ የነበረችን  ወጣት ለመውሰድ ለሆቴሉ ባለቤት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የሆቴሉ ባለቤትም መደበኛ ስራ እንዳለቀ ወጣቱዋን መውሰድ እንደሚችል ቢገልጽለትም፣ የፖሊስ አባሉ ግን ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም። በባለቤቱና በፌደራል ፖሊስ አባሉ መካከል ያለው አለመግባባት እየጨመረ በመሄዱ አንድ የቀበሌ ባለስልጣን መታወቂያውን በማሳየት ችግሩን ለመፍታት ጣልቃ ለመግባት ሞክሯል።  የፌደራል ፖሊስ አባሉ ” አንተ የቀበሌ መታወቂያ ይዘህ እኔን ልትጠይቅ አይገባም” በማለት ከቀበሌው ባለስልጣን ጋር ሌላ ውዝግብ መፍጠሩን አይን እማኞች ገልጠዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባሉም ጓደኞቹን ሰብስቦና የጦር መሳሪያ ይዞ ሲመለስ  የቀበሌ ባለስልጣኑንና ተፈላጊዋን ወጣት ሊያገኛቸው ባለመቻሉ፣ የሆቴሉን ባለቤት እንዲንበረከክ በማዘዝ ገድሎታል። የፌደራል ፖሊስ አባሉም መሳሪያውን ወደ ሟቹ ታላቅ ወንድም በማዞር እርሱንም ገድሎታል። በሆቴሉ ውስጥ ምግብ ለመመገብ የመጣ አንድ የግብርና  ሰራተኛም፣ ፖሊሱን እረፍ በማለቱ ተገድሏል።  ድርጊቱን የተቃወመው ሌላ የገዳዩ ፖሊስ ጓደኛ “  ለምን እንዲህ ታደርጋለህ” ብሎ ሲቃወመው፣ እርሱንም በጥይት መትቶታል። ተመቺው ፖሊስ ከወደቀበት ቦታ ሆኖ ፣ ገዳዩን ፖሊስ በጥይት በመምታት የገደለው ሲሆን፣ ትንሽ ቆይቶም ራሱን በያዘው መሳሪያ ጨርሶአል። ሁለት ሌሎች ነዋሪዎችም በጽኑ ቆስለው በመታከም ላይ ናቸው።
ሟቾቹ የሆቴሉ ባለቤቶች የ25 አመቱ መላክ አስተራይና የ39 አመቱ ሙላት አስተራይ እንዲሁም የግብርና ሰራተኛው አቶ የአቶ አይተነው አስሬ የቀብር ስነስርአት ተፈጽሟል።
በዛሬው እለት የሆቴል ባለቤቶች ለደህንነታችን ዋስትና የለንም በማለት የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል። በከተማዋም በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት አመጽ ሊነሳ ይችላል በሚል ስጋት በፒክ አፕ መኪናዎች ላይ ሆነው ቁጥጥር እያካሄዱ ናቸው።

    No comments:

    Post a Comment