Translate

Tuesday, October 23, 2012

እባካችሁ ይህንን “ኢትዮጵያዊነት” አክብሩት!!


(ርዕሰ አንቀጽ)

sendeq
ኢትዮጵያዊነት ከአጭበርባሪነት፣ ከሸፍጥ፣ ከሴራ፣ ከኩርፊያ፣ ከበቀል፣ ከተንኮል፣ ከደባ፣ ከድብቅ ዓላማ፣ ከአድማ፣ ከባንዳነት፣ ከአቃጣሪነት፣ ከከሃዲነት፣ ከተቀጣሪነት፣ ከማወናበድ፣ በተለይም ከማስመሰለና ከተራ የፖለቲካ ንግድ በላይ መሆኑንና ማንም ሊበርዘው ቢደክምም ሊሸረሽረው የማይችለው የልብ ማህተም መሆኑን ሰሞኑን አየን።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግርኳስ ቡድን ድል እውን ይሆን ዘንድ ሠንደቅ ዓላማቸውን ለብሰው ሌሊቱን ሙሉ ላገራቸው ያዜሙ፣ በየቤታቸው ሆነው በጸሎት የማለዱ፣ በመላው ዓለም በየድረገጹ የመልካም የደስታ ምኞታቸውን ሲገልጹ የነበሩ፣ በዋናው የትግል ሜዳ የአገራቸውን መለያ ለብሰው ታሪኩን ያከወኑና የትግሉን ስትራቴጂ በመንደፍ ታሪክ የሰሩ ድርና ማግ ሆነው አገራቸውን አብርተዋታል።
ብንዘገይም ለመላው የኢትዮጵያ እግርኳስ ቡድን አባላት፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና አፈጣጠሩ ጤነኛ ባይሆንም ለፌዴሬሽኑ አመራሮች እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን። በአፍሪካ ዋንጫ ብቁ ተፎካካሪ የመሆናችን ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ ለዚህ ታላቅ ዕድል መብቃት አዲሱ ትውልድ የረሳቸውን አህጉራዊ ታሪኮቻችንን እንዲያወቅ ረድቶታልና ደስታችን ወደር የለውም። ድሉን ተከትሎ የመንግስት ባለሥልጣናትና የስፖርት ጋዜጠኞች የግል፣ የመንግስት ሳይባሉ ሲያሰሙ የነበረው ቡራ ከረዩ ግን አሳዝኖናል። ፕሮፓጋንዳው እስኪያቅለሸልሸን ድረስ ተጠይፈነዋል። ምክንያቶቻችንን እናቅርብ።
የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ ከሩጫው በስተቀር ሙሉ በሙሉ ሞቷል። ሩጫው በውስን አትሌቶች ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ ቆይቶ የለመድነውን የአስር ሺህ ድል ሙሉ በሙሉ ማስከበር እንኳን ተስኖናል። ቤቱ በሙስናና በህገወጥ አሰራር መጠቃቀሚያ መሆኑን ጸረ ሙስና ኮሚሽን የፈረደበት ነው። ሌሎቹ ፌዴሬሽኖችም የሚወራ ዜና የላቸውም። እግር ኳሱም አንዴ ኩዴታ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ብር አለን የሚሉ የአገራችን ባንኮች ቁጥር አንድ ተበዳሪዎች ጀሌ እየኮለኮሉ የሚነዱትና የሚክቡት፣ በብልሹ አሰራር፣ በሙስናና በብክነት የተመደበ ተቋም ነው።
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉት ከሃያ አንድ በላይ ፌዴሬሽኖችና የስፖርት ማኅበራት ሙሉ በሙሉ የሚመሩት ስለስፖርቱ ምንም እውቀት በሌላቸው ካድሬዎችና የመንግስት ባለስልጣናት መሆኑ የአገሪቱን ስፖርት እንደገደለው በጥናት ተረጋግጦ ሳለ አሁን የተገኘውን ድል የአገሪቱ የስፖርት ፖሊሲ ውጤት ተደርጎ ለፖለቲካ ንግድ ስራ ሲውል አገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ ከአገር ውጪ የሚገኙ ሚዲያዎች አብረው ማጫፈራቸው ያሳዝናል። ሚዲያ አብሮ ሲያብድ ጉዳቱ የከፋ ነውና እናስተውል ለማለት እንወዳለን። ቢያንስ ቢያንስ መንግስት በየመንደሩ የነበሩ የመጫወቻ ሜዳዎችን በሊዝ ጨረታ ለወዳጆቹ እየቸበቸበ ታዳጊዎችን መጫወቻ በማሳጣት አደገኛ ቦዘኔ በማለት ለአደገኛ ሱስ መዳረጉ ያስጠይቀዋል።
ደስታን መግለጽ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፣ ደስታው ስፖርቱ በደረሰበት ድርሽ የማይሉት የአቶ መለስ “አርቆ አሳቢነት” ውጤት እንደ ሆነ አድርጎ ኢቲቪ ማቅረቡ ከተለመደው የኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ የተለየ ባለመሆኑ አያስገርምም። “የባንዲራ ቀን” ለማክበር በህይወት ዘመናቸው አንድ ቀን ለዚያውም ለሰላሳ ደቂቃ ስታዲየም የተገኙትን አቶ መለስን ባልዋሉበት ቦታ መሰንቀር የሙያም ስነ ምግባር አይመስለንም። ያለ ምንም ማጋነን መለስ ለስፖርቱ ካላቸው ደንታ ቢስነት አንጻር አዲስ አበባ ስታዲየም መሰቀላቸውም አግባብ አይደለም እንላለን። በተስፋ አገርና መላውን ስፖርት ቤተሰቦችን በኦርኬስትራ የሚያታልሉት የሼኽ መሃመድ ሁሴን አላሙዲን ጨምሮ!!
ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ለታዳጊ ህጻናት ፕሮጀክት ስልጠና ከፊፋ የተላከ የርዳታ ብር ተዘርፏል። ሰልጣኞች ኳስና ጫማ የሚገዛላቸው በማጣት ሲበተኑ አቶ መለስም ሆኑ የስፖርት ሚኒስትሩ የፈየዱት ነገር አልነበረም። ተጠሪነቱ ለአቶ መለስ የሆነው የጸረ ሙስና ኮሚሽን አበጥሮ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ እንዲተገበር አላደረጉም። ስታዲየም እንዲሰራ ሲጠየቁ ተዛልፈው እንደነበር አይረሳም። አሁን ስታዲየም ይሰራበታል የተባለውና ከበሮ የሚመታበት ሜዳም ድሮ በ1974 ኮሎኔል መንግስቱ ብሔራዊ ስታዲየም እንዲሰራበት በስጦታ የሰጡት ቦታ መሆኑ እየታወቀ እስአከሁን አለመሰራቱ አጀንዳ መሆን ሲገባው እንደ ታላቅ ስኬት መቅረቡ ሊዋጥልን አይችልም። የዛሬ 60ዓመት በተሠራ ስታዲየም ቡድናችን ከ31ዓመት በኋላ ለድል በቃ ሲባል ከዚህ ለድል ካልበቃንባቸው ዓመታት ውስጥ ኢህአዴግ ሃያ አንዱን ይወስዳል – 70በመቶ ማለት ነው፡፡
ሚዲያ መረጃ አቀባይ ቢሆንም ብሔራዊ ስሜትን በተመለከተ የሕዝብ አካል እንደ መሆኑ ያንን መካፈሉ ስህተት ባይኖረውም ዋናውን ጉዳይ ግን መርሳት የለበትም፡፡ ድልን ሲያበስርና ችቦ ሲለኩስ ስኬት ዓልባ የነበሩትን ዓመታት ማስታወስና መጪው ደግሞ ምንያህል ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል በሰከነ መንገድ የማስገንዘብ ኃላፊነቱን መዘንጋት አይገባውም፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ያለንን ብቃትና ተወዳዳሪነትም ሳይጠቁም በድል ብቻ የሰከረ ሚዲያ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉት ከሚያደርጉት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የተለየ አያደርገውም፡፡
በድሉ የተደሰትነውን ያህል በድሉ አማካይነት የሚፈጸመውን የታሪክ ሽሚያ አልወደድነውም።ኢህአዴግ ተራ የፖለቲካ ቁማሩን በመተው ይህንን ከባድሜ ዘመቻና መለቀቅ በኋላ የታየውን ሊደበዝዝ የማይችል ብሔራዊ ስሜት ትምህርት ይውሰድበት – መማር ከቻለ፡፡ ኢህአዴግ እንደሚለው ኢትዮጵያዊነት “በአየር ላይ” ያለ ባዶ ስሜት ሳይሆን በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ የታተመ ውድ ጉዳይ ነውና ይኩራበት፤ አሁንም ድል ለኢትዮጵያ ህዝብና ለቡድናችን!! ለቀጣዩ ውድድር ልዩ ወገብ ጠበቅ!!

No comments:

Post a Comment