Translate

Monday, October 22, 2012




አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፦”በመኪና ሰው ገጭተህ ገድለሀል” ተብሎ ለእስር በተዳረገበት ጊዜ፦”ቴዲ ገድሏል፤ምሥክር ነኝ” በሚል ርዕስ አቅርቤው ከነበረው ረዘም ያለ ግጥም ውስጥ የተወሰነውን ክፍል ዛሬ ላስታውሳችሁ ፈለግኩ።እነሆ፦
ፍልሚያው ባህሪያዊ ነው – ስር የሰደደ ዘመቻ-
የፅልመትና የብርሀን- የፍቅርና የጥላቻ…….
…እናም ጎልያድ ሲመጣ- እየፎከረ በሰይፉ፦
የፍቅር ጠጠር ቢተፋ -የብላቴናው ወንጭፉ_
የክፋት ራስ ሰከረ-ወደቀ ከነመርገፉ፣
የጥላቻ አንገት ተቀላ- ምድያም ተረታ ሰልፉ፣
ቆነጃጅት ከበሮ አንሱ- በዕልልታ ምድርን ሙሉ፣
አንድ ሰው ብቻ አይደለም- ቴዲ ዕልፍ ገድሏል በሉ፣
ገዳይ ጨካኝ ነህ ተብሎ- ቴ’ድሮስ በከሳሽ ተከሷል፣
አዎ! ቴዎድሮስ ገዳይ ነው-የጥላቻን ግንብ ደርምሷል፣
አዎ! ቴዎድሮስ ጨካኝ ነው-እልፍ ክፉ ልብ አስለቅሷል፣
በቀዘቀዘ ጎጆ ላይ- የፍቅር እሳት ለኩሷል።
አንድ፦
…በእምነት ሽፋን ጥንስስ ተጥሎ- ጠማቂዎች ሊጠጡ ሰክረው፣
ሰናዖራውያን ወደላይ- የልዩነት ጡብ ድርድረው፣
ግማሹን ከፍለው- ለፍቅሩ- _ገሚሱን ሊሰጡ ለሱ፣
የፍች ወረቀት አርቅቀው- መስመር ላይ ኖራ ሲያፈሱ፣
“አንተም ቱፍታህን ለራስህ- እሷም ጠበሏን ለራሷ፣
እንዳትደርሽበት ወደሱ- እንዳትደርስባት ወደሷ፣”
ብለው መክረዋት አጥንቱን- ልትሸፍትበት ከልቧ፤
“መኖር አይችሉም” ብለውት- ክታብህና ማተቧ፣
ስታሽኮበኩብ ልትጠፋ- ፍቅሩን ልትገድል ስታደባ፣
ጨካኙ ቴ’ድሮስ አንገቷን አቅፎ- በውብ ዜማ እያባባ፣
“ የመቻቻሉ ኑሯችን-የዘመናቱ ፍቅራችን-
በእምነት ሰበብ ላይደፈርስ- ይታደስ ኪዳን ውላችን፣
ላንችም ለኔም ይበቃናል -ሰፊኮ ነው ዕልፍኛችን”
እያለ እየቀጠለ- ጋራ ጢሻውን እያለፈ፣
በሸመንደፈር ባቡር- ከሸገር ሀረር እየከነፈ፣
የፍቅር እሳት እየተፋ- የመውደድ ማርሽ እየረገጠ፣
ስንት ሰው ይሆን ቴዲ ጨካኙ- በየመንገዱ የደፈጠጠ?
ሁለት፦
…ገና ሀሁ ሲል ባ’ሌፉ- ስለፍቅር ሲል ሸፍቶ፣
በፈቃዱ- ኣልለይ ቢል_ ከፍቅር ጋር ተቆራኝቶ፣
አንዱን ቀለም ለያይተው_ ደሙን ከደሟ አንጥረው፣
ዳግም ውዱን እንዳያያት- አስፈሪ ቅጥር ቀጥረው፣
እጅና እግሩን በብረት አስረው- ደሴት ጫፍ ላይ ቢወረውሩት፣
ልዩነትን አውጅ ብለው- የኑሮውን ጣዕም ቢያመሩት፣
ዳህላክ ደሴቱ ላይ- የትዝታ ቤት ቀልሶ፣
ባ’ሳብ ፈረስ መጭ እያለ- የዝሆኖቹን አጥር ጥሶ፣
“ ስጋችንን ቢያግደንም- ባቢሎናዊ ቋጥኝ ቅጥሩ
አቋርጨ በሀሩሩ- ሰንጥቄ በባህሩ
ካንችው ጋር ነኝ በመንፈሴ- ልቤ በፍቅርሽ ቆርቧል፣
ወጀቡ ማዕበሉ ሲያልፍ- አይዞሽ ፍቅራችን ያብባል”
እያለ ባራራይ ዜማ – ማህሌተ ፍቅርን እያለቀሰ፣
ስንት የክፋት ግንብ አፈራረሰ? ስንት የጥል አጥርደረማመሰ?
ሦስት፦
….የኢንተርሀሞይ ከበሮ- ባ’ደባባይ ላይ ሲመታ፣
ሰላምታ ወጉን- ረስተው- ጣቶች ሲሄዱ ለቃታ፣
ቤልሆርና ሰራዊቱ- በደም ስካር ሊራወጡ፣
የሳጥናኤል መልዕክተኞች- አሰፍስፈው ሲቋምጡ፣
በሉተር ህልም አለኝ ቅኝት- በማንዴላ የይቅርታ ጨው፣
“ጃ ያስተሰርያል” እያለ- ኤሎሄውን ሽቅብ ቢረጨው፣
እልፍ የክፋት መናፍስት- ምሳ’ቸውን ሳይጋቱ፣
በግብር እጦት ተኮራምተው- በደም ጥማት ስለሞቱ፣
ሊጠየቅ ይገባዋል- ቴዲ ብዙ ገ’ሎ አምልጧል፣
ነብርና ፍዬል ጠቦት- ከህግ አልፎ አጨባብጧል፣
የህግ ፍፃሜ ነውና – ፍቅርን ከህግ አስበልጧል::
አራት፦
መች ያቆምና በደሉ- ሲተረክ ቢውል የሱ ክፋት፣
ስንት ገዳይ እንዳልገደለ – በዛ ሰሞን በሠራው ጥፋት-
ብርጌዳቸው ተደምስሶ- ሲበታተን ታላቅ ሰልፉ፦
ለመርዶ ነጋሪ ያህል- ጥቂት ምርኮኞች ቢተርፉ፦
ለነሱ’ ሚሆንም ስፍራ- ምድራችን ውስጥ የለም ብሎ፦
አበባየሆሽ ባህሉን- በይቅርታና በዕርቅ አጅሎ፦
“ሆ በል! ዋሽንቱ” እያለ-“ሆ በል! ማሲንቆ “እያለ፦
ስንት የክፋት ሀይል አጠፋ? ስንት የጥል ጦር ገደለ?
እያለ ግጥሙም፣ግድያውም በየዓይነቱ ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment