Translate

Saturday, October 13, 2012

ጎል ጎል ጎል… ነገ ነገ ነገ!


አቤ ቶኪቻው

አዲሳባ ብሆን በፍፁም ከማልቀርባቸው ቦታዎች ውስጥ ሶስቱን ጥቀስ ብባል አንድ ታላቁ ሩጫ ሁለት ኢህአዴግ የሚጠራቸው ሰልፎች (በቅንፍም ተቃዋሚዎች ሰልፍ ስለማይጠሩ አምሮት መወጫ ነው!) ሶስት አዲሳባ ስታድየም ናቸው።ጎል ጎል ጎል… ነገ ነገ ነገ!
በነገራችን ላይ ታላቁ ሩጫ ንብረቱ ሊወረስ ነው የተባለው ነገር ምን ደረሰ…? ሃይሌ ገብረ ስላሴ ባለፈው የጠቅላዩ ሞት ግዜ ስቅስቅ ብሎ ያለቀሰበት ምክንያት አሁን ገባኝ። የምር ግን እርሳቸው በሞቱ በማግስቱ ትዕዛዝ የውርስ ትዕዛዝ ሲወጣበት “አጎደሉኝ አጎደሉኝ” ብሎ ድጋሚ ስቅስቅ ብሎ ማልቀሱ እንደማይቀር እጠረጥራለሁ።

እንዴ… የሃይሌ ታላቁ ሩጫ ለካስ ራሷን “ትርፋማ ያልሆንኩ፣ መንግስታዊም ያልሆነ ድርጅት” ነኝ ብላ… መንግስት በጠበሸው ሀገር ላይ ብሪቱን እንዳሻት ታጠረቃቅም ነበርና! ይኸው እፍስፍስ አድርጎ ወረሳታ! እንዲገጥምልን ያህል “ወረሳታ!” ከሚለው ቀጥሎ ወንዳታ! እንበል። እኛ ድሮም ገንዘባችንን የምናወጣው ብሶታችንን ብንወጣበት ብለን እንጂ የሀይሌን ገንዘብ አምሮት ለማውጣት አይደለም! ውይ ወዳጄ እንደምን ያለሁት ክፉ ተናጋሪ ወጣኝ… ወረድኩበት እኮ! ይቅርታ ሃይልዬ በላዬ ላይ ያደረው ነው የተናገረህ እንጂ እኔ በአንተ ላይ እንዲህ አልናገርም!
የሆነው ሆኖ አዲሳባ ብሆን ከማልቀርባቸው ቦታዎች… ብዬም አይደል የጀመርኩት? አዲሳባ ስታድየም የባንዲራ ቀን ሲከበርም ሆነ ደመቅ ያለ እግር ኳስ ጨዋታ ሲኖር አልቀርም ነበር። እውነቴን ነው ይፍረዱኝ እነ ጌታ ዘሩ… ድራፍት ቤት…!
ልክ እሁድ ሲሆን ከሰዓት በኋላም ሲመጣ ደመቅ ያለ እግር ኳስ ጨዋታ አለ። ኢትዮጵያ ከደርቡሽ! “በአባቴ ሚኒሊክ በእናቴ ጣይቱ በአገሬ አይደፍረኝም ደርቡሽ ምናባቱ!” የሚል ግጥም የፌስቡክ ሰፈር ልጆች ገጥመው አይቻለሁ። በእነ ሚኒሊክ ተገጥሞ ሌሎቹ መሪዎቻችን እንዳይከፋቸው ብዬ እኔም ልግጠም እስቲ ብዬ ስነሳ… “በአባቴ ተፈሪ በእናቴ መነን እንዴት እጅ ይሰጣል ህዝቤ ለሱዳን ” አልኩ። ከዛስ… መንጌ ፊቴ ድቅን ብለው እኛስ… ቢሉኝ ግዜ፤ “በእናቴ ውባንቺ… በአባቴ መንግስቱ ሽንፈቴ ነው ሞቴ ይፍረድ አብዮቱ!”  አልኩ። ወደ ወጋገኑ መንግስታችን ስንመጣ…
በነገራችን ላይ የውጪ ምንዛሬ በሀገሪቱ ባንኮች ሁሉ ጠፍቶ በወጋገን ባንክ ብቻ ነው ያለው አሉ… እሱም በስንት እጅ መንሻ ነው የሚገኘው ሲባል ሰምቻለሁ። “እጅ ነስተናል” አሉ መለስ… “ምን ያልነሱን ነገር አለ!?” አሉ ታዛቢዎች። ለማንኛውም አሁን ወደ ግጥማችን እና ወደ ግጥሚያችን…  “በአባቴ መለስ በናቴ አዜብ ሁሉም የቦንድ ያምጣ ጎል ለመገደብ”
ኦ… ሚስተር “ሌጋሲ” እርሳቸውም እኮ መሪ ናቸው ይገጠምላቸው እንጂ… “ባባቴ ሃይለማሪያም በናቴ ሮማን ራዕዩ እንዲፈፀም ክፉ አታሰሙን!”
ለማንኛውም ነገ ልክ እሁድ ሲሆን ከዛም ከሰዓት በኋላው ሲጀመር “ሲምባ ሶሴ… ሶሴ! ሶሴ ያና… ያና! ያኒ ሱምሱም… ሱም ሱም…” እየተባለ ስታድየሙ በጭፈራ ይደምቃል። ትርጉሙ ምንድነው? አይባልም ዋናው ስታድየሙ መድመቁ ነው። “ኦ…ሆ አ…ሃ… መሸነፍ የለም!” “ጎል ጎል ጎል… ሳላ ሳላ ሳላ…” “ጎል ጎል ጎል… አዴ አዴ አዴ!” ይባላል። ከዛ እነርሱም እየወሰዱ ብቻ ደርቡሽ ላይ… ጎል… እየወሰዱ ብቻ…ጎል!
አዲሳባ ብሆን በፍፁም አልቀርም ነበር። የአዲሳባ ወዳጆቼ በፍፁም እንዳትቀሩ። ጮክ ብላችሁ ብሄራዊ ቡድናችንን ደግፉ! ከዛም አሽፈን እንጨፍር። ለጊዜውም የኑሮ ውድነቱን የፖለቲካ ዕብደቱንም እንርሳው!
ድል ለብሄራዊ ቡድናችን!

No comments:

Post a Comment