Translate

Friday, October 12, 2012

ጁነዲን፣ ኦህዴድ እና ኢህአዴግ – ልዩ ጥንቅር በደረጀ ሀብተወልድ (ኢሳት)


ልዩ ጥንቅር- በደረጀ ሀብተወልድ-ኢሳት
ESAT journalist Dereje Habtewoldየሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶና አራት ባለስልጣናት፤ ከኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሥራ አስፈጻሚነት ሰሞኑን ተነስተዋል።
ሚኒስትር ጁነዲንና አራቱ አመራሮች  ከሥራ አስፈፃሚነታቸው እንዲነሱ የተወሰነው፤ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ካለፈው መስከረም 21 ቀን እስከ መስከረም 24 ቀን  ባካሄደው ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ነው።
ከወራት በፊት አቶ ጁነዲን  ወደ አውስትራሊያ በመምጣት ከኢህአዴግ ደጋፊዎች ጋር ለማድረግ ያሰቡት ስብሰባ  ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ከፍተኛ ተቃውሞ ተደናቅፎባቸው ተልዕኳቸውን ሳይፈጽሙ  ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
በውጪ አገር ከፍተኛ ተቃውሞ አስተናግደው  በተመለሱ   በጥቂት ቀናት ውስጥ  በዘንድሮው  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የምርቃት ፕሮግራም ላይ የክብር እንግዳ  ሆነው የተገኙት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ፤ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ስለ ኮብል ስቶን  ማንጠፍ ሥራ ማንሳታቸው፤ በተመራቂዎቹ ዘንድ ከፍ ያለ ተቃውሞ አስነሳባቸው።
ብዙም ሳይቆይ ባለቤታቸው ወይዘሮ ሀቢባ ከሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ የሀይማኖት አታሼ ቢሮ 50 ሺህ ብርና 500 ቁርዓን ይዘው ሲወጡ በፖሊስ ተይዘዋል ተብለው ለእስር ተዳረጉ።
ቀደም ሲል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት፣ከዚያም  የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር፣ቀጥሎም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ከሚሽን-ኮሚሽነር እና አሁን ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር በመሆን ለረዥም ዓመታት ኢህአዴግን በታማኝነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው ለሚነገርላቸው ለአቶ ጁነዲን  ከኦህአዴድ ሥራ አስፈፃሚነት መወገድ ዋነኛው ምክንያት፦ ይኸው ባለቤታቸው ከሳዑዲ ኤምባሲ የሀይማኖት አታሼ ጋር በመሆን ፈጽመውታል የተባለው ድርጊት ነው።
ሚኒስትሩ ከወር በፊት <ኢትዮ-ቻነል> በተባለ ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሁፍ ባለቤታቸው ያለ ጥፋታቸው ለእስር እንደተዳረጉባቸው በማብራራት፦<የፍትሕ ያለህ!> በማለት- አገልጋይ የሆኑለትን መንግስት- መማጸናቸው ይታወሳል።
በሚኒስትርነት ስልጣናቸው ሳይሆን በግለሰብነታቸው  የማምለክ መብትና ነፃነታቸውን ተጠቅመው የሟች እናታቸውን ኑዛዜ ለማስፈጸም መስጊድ ለማሠራት  ከሌሎች ሰዎች ጋር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን፤ ባለቤታቸውም ይዘው የተገኙት ገንዘብና ቁርዓን  ለዚያ መስጊድ የሚውል መሆኑን በጽሁፋቸው የጠቀሱት አቶ ጁነዲን፤<< ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሠራሁት ጥፋት ስለሌለ ማንንም ይቅርታ አልጠይቅም>> ማለታቸውም አይዘነጋም።
ሚኒስትሩ ያን ጽሁፋቸውን በጋዜጣ ላይ ማውጣታቸውን ተከትሎም፤  የኢትዮ ቻነል ባለቤትና  ዋና አዘጋጅ  ሳምሶን ማሞ ፤ <ባልታደሰ ግብር መሥራት>በሚል ክስ  ለእስር ተዳረገ።
በማስከተልም የዛሚ ኤፍ ኤም አዲስ ራዲዮ  የክብ ጠረጴዛ  ፕሮግራም መደበኛ ተወያይ የሆኑት የድርጅትና የመንግስት ጋዜጠኞች፤  መንግስት በአቶ ጁነዲን ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠየቁ።
ይሁንና በጊዜው በአቶ መለስ መሰወር የተነሳ በኢህአዴግ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና አለመረጋጋት በመስፈኑ፤ የአቶ ጁነዲን ጉዳይ ሊቆይ ግድ ነበር።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ  ለረዥም ጊዜ በቅርበት ሲከታተሉ  የቆዩ ወገኖች፤ አቶ ጁነዲን  ቅሬታቸውን  በጋዜጣ ላይ  መፃፋቸው በባለቤታቸው አማካይነት ፈጽመውታል ከተባለው ድርጊት በበለጠ የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ሊያስቆጣ እንደሚችል ፤ ህወሀት ለሁለት በተከፈለ ጊዜ የሆነውን ነገር ወደ ሁዋላ ሄደው በማስታወስ ያስረዳሉ።
በወቅቱ  በአቶ መለስ ቡድን እየተመቱ  የመጡትና ሀሳባቸውን ለመግለጽ የመንግስት ሚዲያን  እንዳይጠቀሙ የተከለከሉት የነ ተወልደ እና የነ ስዬ ቡድን  አባለት ፤ሀሳባቸውን በጽሁፍ አድርገው ለጋዜጦች ማሰራጨታቸው፤ በአቶ መለስና በተከታዮቻቸው ዘንድ እንደ ከባድ ጥፋት ተቆጥሮ  እንደነበር ይታወሳል።
<<ሰዎቹ ለይቶላቸው በነጦቢያ ላይ መጻፍ ጀምረዋል።ከዚህ በላይ መበስበስ የለም>> ነበር ያሉት-በጋዜጦች ላይ  ሀሳብን መግለጽን እንደ ኢ-ዲሞክራሲያዊነት ያዩ የነበሩት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር።
<,ይህን ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁት አቶ ጁነዲን በተለያዩ ጋዜጦች ባለቤታቸውን አስመልክቶ ለወጡባቸው ጽሁፎች- የፃፉትን ማስተባበያ  ለኢትዮ-ቻነል  መላካቸው፤ ጋዜጣው ካለው ድርጅታዊ ወገንተኝነት አኳያ  በነ ስዬ ላይ የደረሰው ዓይነት ተጨማሪ ቁጣ ላይደርስብኝ ይችላል ከሚል ግምት ይመስላል >ያሉት አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፤ሆኖም  አንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን ሆነህ ቀርቶ -ተራ አባልም ሆነህ ቅሬታህንና ሀሳብህን  በነፃነት ለመግለጽ መሞከር የማይታሰብ በመሆኑ፤ጦሱ ከእርሳቸውም አልፎ ለጋዜጣው አዘጋጅም ተርፏል ብለዋል።
ከዚህና ከባለቤታቸው ጋር ፈጽመውታል ከተባለው  ድርጊት ጋር ተያይዞ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየው የአቶ ጁነዲን ጉዳይ ሰሞኑን  በተካሄደው የኦህአዴድ ጉባኤ  ላይ  ነው፤  የመጨረሻው-መጀመሪያ የተባለውን ውሳኔ ያገኘው።
በጉባኤው ፤  በሟች እናታቸው መኖሪያ ላይ እያሠሩት ካለው መስጅድ ጋር በተያያዘ የተወቀሱት ሚኒስትር ጁነዲን፣<< ከፍተኛ የዲሲፕሊን ጉድለት ፈጽመሀል፤ ካለህበት ኃላፊነትና ሥልጣን አኳያ ተገቢ ያልሆነ ሥራ ሠርተሀል>>ተብለው  ክፉኛ ተገምግመዋል።
በዚህም ምክንያት በኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ስበሰባ ላይ በተደረገው ግምገማ፣ ከሥራ አስፈጻሚነት ተነስተው በተራ አባልነት እንዲቀጥሉ ተወስኗል።
በአቶ መለስ ሞት ማግስት በግምገማም ሆነ በተለያዬ ምክንያት ከድርጅቱ የሚለዩና  የሚታገዱ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ መታየታቸው፤ ሥርዓቱ ሊረጋጋ አለመቻሉንና በራሱ ሰዎች ዘንድ እምነት የማይጣልበት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ እንደሆነ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ መገናኛዎች እየሰጧቸው ባሉት አስተያዬቶች  ይገልጻሉ።
ከሁለት ሳምንት በፊት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩትና ከወራት በፊት በተካሄደ ግምገማ ከሀላፊነታቸው ዝቅ የተደረጉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አቶ ከፍያለው አዘዘ ከነ ቤተሰቦቻቸው ወደ አሜሪካ ሲኮበልሉ፤ከሳምንት በፊት ደግሞ ቀደም ሲል የገቢዎች ሚኒስትር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የትግራይ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት- ኢፈርት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት የህወሀቱ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው በላይ -ሥርዓቱን በመክዳት   ከነ ቤተሰባቸው አሜሪካ ጠቅልለው መግባታቸው ይታወሳል።
ከህወሀት ውስጥ በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ  ሥርዓቱን ሲከዱ  አቶ ጌታቸው የመጀመሪያው ባለስልጣን ናቸው።
በሌላ በኩል አቶ መለስ ማለፋቸውን ተከትሎ  በኢህአዴግ ውስጥ በተካሄደው የሥልጣን ሽግሽግ  እንደ ብዙሀን ወኪልነታችን የረባ ቦታ አላገኘንም የሚል ተቃውሞ ያነሱ የኦህዴድ አባላት <ራሳችሁን አጥሩ> ተብለው  አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጡት  በአዲሶቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመት ማግስት ቢሆንም፤ አባላቱ ያነሱት ተቃውሞ እስካሁን ሊበርድ አለመቻሉን ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ድርጅቱ ሰሞኑን በአዳማ ሲያካሂደው የቆየውን የድርጅቱን የማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ተከትሎ በተካሄደ ግምገማ ፤<የአመራር ጉድለት አሳይታችሁዋል >ተበለው ከስልጣን የተወገዱት አቶ ጁነዲን  ብቻ አይደሉም-ሌሎች ሶስት ባለስልጣናትም ታግደዋል– የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ለማ መገርሳ፣ የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነህ  እና የትራንሰፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አለማየሁ እጅጉ።
ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ሲል የስፖርትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር  የነበሩትና  ቀጥሎም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ፤ በፌዴራል ደረጃ ካላቸው የሥራ ኃላፊነቶች እንዲነሱ ተወስኗል።
ኦህዴድ፤በኢህአዴግ ውስጥ ከባድ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ከአባል ድርጅቶቹ  በአንፃራዊነትም ቢሆን ጠንከር ያለ አቋም በማንሳት ይታወቃል።
ህወሀት ለሁለት በተከፈለ ጊዜ ብአዴን -ከአቶ መለስ ጎን፤ ደኢህአዴግ ደግሞ ከነ ስዬ ወገን አሰላለፋቸውን ሲያስተካክሉ፤ ኦህዴድ ግን፦ <ህወሀት የራሱን ችግር በራሱ ይፍታ!>የሚል አቋም በማንጸባረቅ በገለልተኝነት መቆሙ አይዘነጋም።
በወቅቱ የኦህአዴድ አቋም ያበሳጫቸው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤  የድርጅቱን ሊቀመንበር አቶ ኩማ ደመቅሳን ከቦታቸው በማንሳት ለረዥም ጊዜ ያለ ሥራ ሲያስቀምጧቸው፤ቀሪዎቹን የኦህዴድ አባላት ደግሞ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ  በሀይለ-ቃል ዘልፈዋቸዋል።
ዘለፋውን መቋቋም ያቃታቸው የወቅቱ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔርና የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳም፦<<አሁንስ መንግስቱን መሰልከኝ>>በማለት አቶ መለስን  በአደባባይ እስከመናገር ደርሰዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን  በኦህዴድ አቋም እጅግ የተበሳጩት  የህወሀቱ መስራች አቶ ስብሀት ነጋ በሌላ  የድርጅቱ ስብሰባ ላይ፦<< እናንተማ ምን ታደርጉ? ከሜዳ ላይ እያነሳን ሚኒስትር አደረግናችሁ ..>> በማለት ሲዘልፏቸው ፤ንዴታቸውን መቋቋም የተሳናቸው የወቅቱ የውሀ ሀብት ልማት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ጃርሶ፦< እናንተም ከጫካ መጣችሁ፤ እኛም ከሜዳ መጣን። ምን ልዩነት አለው?>> በማለት መልስ እንደሰጧቸው መዘገቡ ይታወሳል።
እንደወትሮው ሁሉ ኦህዴድ ዘንድሮም የአቶ መለስን መሞት ተከትሎ  ያነሳው የሥልጣን ጥያቄና የያዘው ጠንካራ አቋም ለኢህአዴግ ራስ ምታት ሆኗል።
ከምልክትነት ባለፈ ምንም ተግባር በሌላቸው በመከላከያ ሚኒስትርነትና በርዕሰ-ብሔር ሹመት ሲሸነገል ላለፉት 20 ዓመታት የቆየው ኦህዴድ፤ በቅርቡ የተካሄደውን የስልጣን ሽግሽግ ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያቀረባቸው ዕጩ ወድቀውበታል።

ከቀሩት የስልጣን ቦታዎች  ሁነኛ ትርጉም ያላቸውና ወሳኞቹ፤_  የውጪ ጉዳይ  እና የደህንነት ሚኒስትር ናቸው።ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በሚያዋቅሩት አዲስ ካቡኔ ውስጥ ኦህዴዶች እነዚህንም ቦታዎች ሊያገኙ እንደማይችሉ ታማኝ ምንጮች እየጠቆሙ ነው።
በተለይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነቱ የህወሀት ድርሻ  ለመሆኑ ከወዲሁ እንደተደመደመ ነው-  ለኢሳት የደረሱት መረጃዎች የሚያሳዩት።
<<ወሳኝ ናቸው ከተባሉት የስልጣን ቦታዎች  ኦህዴድ አንድኛቸውንም  የማያገኝ ከሆነ፤  አባላቱን ፀጥ ለማሰኘት ማናቸውም እርምጃ ቢወሰድ፤ የውስጥ ቅራኔው እያደገ እንጂ እየጠፋ አይመጣም>> ይላሉ-የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው።
<<የጦርነት አለመኖር ሰላምን አያመለክትም። ኢህአዴግ የተነሳበትን ተቃውሞ፤ በሀይልና በማስፈራራት ቢያፍነውም፤የተዳፈነው ፍም አንድ ቀን ሲገለጥ ማገርሸቱ አይቀርም>>ሲሉም አክለዋል።
ኢህአዴግ-በኦህዴድ ውስጥ የተፈጠረውን ውጥረት እንዴት ይፈታዋል? አቶ ጁነዲንን እና አራት አመራሮችን  በማንሳት የተጀመረው እርምጃ ባለበት ይቆማል?ወይስ በሹመት ሽግሽጉ ተቃውሞ ወዳነሱ  ሌሎች የኦህዴድ አባላት ይሸጋገራል? የኦህዴድ አባላትስ   በእርምጃው ተደናግጠው ጥያቄያቸውን ይስባሉ?ወይስ ያለምንም ፍርሀት በጠንካራ አቋማቸው እንደጸኑ ይቀጥላሉ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

No comments:

Post a Comment