Translate

Thursday, October 11, 2012

አቶ ጁነይዲን ሳዶ ሂስ በማውረድ ጥፋታቸውን አመኑ፤ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ከፌዴራል ኃላፊነታቸው ይነሳሉ



Junedin-Sadoበዘሪሁን ሙሉጌታ (ሰንደቅ ጋዜጣ)
የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ሰሞኑን በአዳማ ሲያካሂደው የቆየውን የድርጅቱን የማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ተከትሎ በተካሄደ ግምገማ በተጓደሉ አራት የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ምትክ አዳዲስ አባላትን ሾሟል።

ድርጅቱ ቀደም ሲል ባካሄደው ግምገማ የአመራር ውስንነት ታይቶባቸዋል ከተባሉት መካከል የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ለማ መገርሳ፣ የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነህ እንዲሁም የትራንሰፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አለማየሁ እጅጉ እና በሰሞኑ ስብሰባ የተገመገሙት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ በአቶ ጁነይዲን ሳዶ ምትክ አዳዲስ አባላትን ተክቷል።

የተተኩት አዳዲስ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ደግሞ የቱምሳ ኢንዶውመንት ኃላፊ አቶ አበራ ኃይሉ፣ የምስራቅ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልቃድር የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ
ኑሬ ቀመር እና የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ጉቾ ናቸው።

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ በፌዴራል ደረጃ ካላቸው የሥራ ኃላፊነቶች ተነስተው በክልሉ እንዲሰሩ መመደባቸው ታውቋል። በዚህ ውሣኔ መሠረት በአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ አዲስ ካቢኔ ውስጥ እንደማይካተቱ ከወዲሁ የተረጋገጠ ሆኗል።

ድርጅቱ የ2004 የስራ አፈፃፀም ግምገማና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትና ክርክር ማድረጉ የተዘገበ ሲሆን በተለይም አቶ ጁነይዲን ሳዶ የግምገማው ቁልፍ ሰው ሆነው ታይተዋል። አቶ ጁነይዲን በተወለዱበት አካባቢ የወላጅ እናታቸውን ኑዛዜ ለመፈፀም ሲሉ ካሰሩት መስጊድ ጋር በተያያዘ ባለቤታቸው ከሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ገንዘብና የተለያዩ የቁርአን መፃህፍቶች ይዘው ሲወጡ በፌደራል ፖሊስ መያዛቸውና ከሽብርተኛ ቡድን ጋር በማበር ተጠርጥረው መታሰራቸው ይታወሳል፤ አቶ ጁነይዲንም ባለቤታቸው ንፁህ መሆናቸውን በመጥቀስ ለሰንደቅ ጋዜጣና ለኢትዮ ቻናል ጋዜጣ መልዕክት በመላክ ጭምር ተከላክለዋል።

ድርጅቱም በዚሁ ጉዳይ ሰፊ ውይይትና ክርክር ካደረገ በኋላ አቶ ጁነይዲን ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ከስራ አስፈፃሚ አባልነት በማንሳት በተራ አባልነት እንዲቀጥሉ አድርጓል። አቶ ጁነይዲንም ቀደም ሲል የተፈፀመው ተግባር ሲከላከሉ ቢቆዩም በፓርቲው ግምገማ ላይ ግን ጥፋታቸውን በማመን በድርጅቱ የግምገማ ባህል መሠረት “ሂሳቸውን አውርደዋል” ሲሉ የድርጅቱ ምንጮች ገልፀዋል።

በቀጣይ አቶ ጁነይዲን በጥፋታቸው ተፀፅተው የሚታረሙ ከሆነ ከተራ አባልነት ወደ ከፍተኛ አመራርነት የመመለስ እድል እንደሚኖራቸውም የድርጅቱ ምንጮች ገልፀዋል። በዚህ ግምገማ ላይ እርምጃ ያልተወሰደባቸውና በከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የታለፉ አመራሮች መኖራቸው የታወቀ ሲሆን፤ አመራሮቹ እነማን እንደሆኑ ምንጫችን ከመግለፅ ተቆጥቧል።

በሌላ በኩል ድርጅቱ በ2004 ዓ.ም በክልሉ አበረታች የስራ አፈፃፀም መታየቱን ተመልክቷል። በ2003/2004 የምርት ዘመን በኦሮምያ ክልል 5 ሚሊዮን 492 ሺህ 725 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት በማረስ 108.1 ሚሊዮን ኩንታል የምርት ውጤት መገኘቱንና በተያዘው የ2004/2005 የምርት ዘመን ደግሞ 146 ሚሊዮን 542 ሺህ 122 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በሌሎች የትምህርት፣ የጤና እና ማኅበራዊ አገልግሎት አበረታች ውጤት መገኘቱንም ተገልጿል።

http://www.maledatimes.com/2012/10/10/%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%8C%81%E1%8A%90%E1%8B%AD%E1%8B%B2%E1%8A%95-%E1%88%B3%E1%8B%B6-%E1%88%82%E1%88%B5-%E1%89%A0%E1%88%9B%E1%8B%8D%E1%88%A8%E1%8B%B5-%E1%8C%A5%E1%8D%8B%E1%89%B3%E1%89%B8%E1%8B%8D/

No comments:

Post a Comment