Translate

Monday, October 22, 2012

ኬኒያን በድርበቡ! (አቤ ቶኪቻው)



ይህ ጨዋታ በአዲሳባዋ አዲስ ታይምስ (ፍትህ) መፅሔት ለንባብ የበቃ ሲሆን መፅሔቷን ለማግኘት ላልቻሉ ወዳጆች “በአዲሱ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን” መሰረት “ወሬ ለሁሉም” እንዲዳረስ የተለጠፈ ነው። የኔታ “ለወሬ የለውም ፍሬ!” ይሉን ነበር። የኔታ ይቺን ብቻ ተሳሳቱ!
ወሬያችን ይቀጥላል!

ይምጡ ወዳጄ ወደ ኬኒያ ናይሮቢ ይዤዎት ልሂድ… ብቻዎትን ግን እንዳይሞክሩት። የናይሮቢ ፖሊስ ሀበሻ ሲመለከት የርሃብ ስሜቱ ይመጣል… ከዛም ያዛጋል። አፉን እንደከፈተም ቀጥታ ወደ እርስዎ ይመጣል። ይሄኔ አፉን የሚዘጉበት ሽልንግ፣ ወይም ደግሞ ክሽን ያለች ኪሱዋሊ ቋንቋ፣ አለበለዛ ደግሞ ቆፍጠን ያለ እንግሊዘኛ ከሌልዎት በስተቀር ወደ ኬኒያ ለመሄድ አይሞክሩ። አንድ ዘዴም አለ፤ ሙሉ ልብስዎ ላውንደሪ ገብቷል? ከደረሰ እርሱን ባማረ ከረባት ግጥም አድርገው ይልበሱ። ይሄኔ የኬኒያ ፖሊስ ዘንድ የተከበሩ ኖት!
እስቲ መጀመሪያ ሰላምታው ይቅደም፤ እንዴት ከረሙልኝ…! “ፍትህ ጋዜጣ ከምትወጣ ቀዳማዊት እመቤት ከቤተመንግስት ቢወጡ ይቀላል!?” ተብሎ እየተወራ ባለበት ሰዓት ፍትህ በአዲስ ማሊያ በመምጣቷ ዳግም ተገናኝተናል። እሰይ እንኳንም ተገናኘን!
እኔ የምለው ወይዘሮ አዜብ ግን ምን አስበው ነው ከቤተ መንግስቱ አልወጣም ያሉት…? አንዳንዶች በአቋራጭ “ቤተመንግስቱን ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥረነዋል!” እንዳንባል ሰጋን እያሉ በየጓዳው እያወሩ እኮ ነው። የምር ግን ማስጠንቀቂያ ደንገጥም የማያደርጋቸው ሴት እሳቸውን አየሁ… አሃ ለካስ ታንክ ተደግፈው መፅሐፍ ሲያነቡ የነበሩት ሰውዬ ባለቤት ናቸው!
ለማንኛውም ዛሬ ኬኒያን በድርበቡ ላሳይዎ ነው ሀሳቤ… እና እሜቴን ለቀቅ አድርገን ናይሮቢን ጠበቅ እናድርግ፤ ጎሽ አዲስ መስመር ላይ እንገናኝ፤
አርባ ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት ኬኒያ ያለፈው አመት በጀቷ ከአስራ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ይበልጥ ነበር። ሰማኒያ ሚሊዮን ህዘዝብ ያላት ኢትዮጵያችን አስራ አንድ ቢሊዮን ዶላር በጅታ ከእኛ በግማሽ የሚያንሱት እነሱ እንዴት ይሄን ሁሉ በጀቱ ብለው አይሰማዎ… ሰዎቹ በበጀት ብቻ ሳይሆን በሙስናም ስለሚበልጡን ብዙ አይቆጩ። በነገራችን ላይ ለህዝብ ተወካይ አባላት ወይም እነርሱ MP (Members of parliament) ለሚሏቸው የፓርላማ ሰዎች ክፍያ በአለም ራሱ ከፍተኛው የኬኒያ ሳይሆን አይቀርም። ይህ የተደረገው ሙስናን ለመከላከል ነበር። ነገር ግን የኬነያ ባለስልጣናት ገንዘብ አይንቁም። የፈለገ ቢከፈላቸው ሌላም ይፈልጋሉ!
ፖሊሱም የዚህ ነፀብራቅ ነው። ብዙ ግዜ ታድያ ፖሊስ የሚበረታው ሰደተኛው ላይ በተለይም ሀበሻው ላይ ነው።
በናይሮቢ ከተማ በርካታ ሀበሾች አሉ። ብዙዎቹ “ከመንግስታችን ጋር ተኳርፈናል” በሚል በስደተኝነት ተመዝግበው ከአሁን አሁን ወደ አሜሪካ፣ ካናዳ እንዲሁም አውሮፓ ለመሄድ ያቆበቆቡ ናቸው።
እስቲ እኔ እኖርበት የነበረው የሀበሾች ሰፈር እንሂድማ…
ናይሮቢ በርካታ ኢንተርናሽናል ድርጅቶች ለዋና ቢሮነት የሚመርጧት አሪፍ የአፍሪካ ከተማ ብትመስልም እኔ እና ሌሎች ሀበሾች ያለንበት ሰፈር ሲመጡ ግን “ድንቄም የአለም አቀፍ ድርጅት መቀመጫ” ይሏታል።
ይህ ቦታ የከተማዋ ምስራቃዊ ክፍል ነው። “ኢስሊ” ይባላል። በተለይ አስረኛ የሚባለው ሰፈር ሲሄዱ መርካቶ የገቡ ነው የሚመስልዎ። ታድያ ማልደው አይሂዱ ማንም በጠዋት አይነሳም። በኢስሊ ነጋ የሚባለው ቢያንስ አራት ሰዓት አካባቢ ነው።
የናይሮቢ ምስራቃዊ ክፍል “ኢስሊ” በዝናብ ጊዜ ጭቃው በፀሀይ ጊዜ አዋራውን ሲያዩ የኬኒያን መንግስት ማማረር ይጀምራሉ። ትንሽ ሲቆዩ ግን ማማረሩን ይተዉታል። ምክንያቱም ይለምዱታል። ለማንኛውም ይህ ቦታ የኢትዮጵያወያን የሱማሌያዊያን እና የኤርትራዊያን መገኛ ነው።
ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ያሰቡት ተሳክቶ ወደ ፈረንጆቹ ሀገር ከማምራታቸው በፊት በኢስሊ የተለያየ ስራ ይሰራሉ። “ማታቱ” የተባለችው በመጠኗ ከሎንችና ጋር የምትስተካከል የትራንስፖርት መኪና ላይ ገንዘብ ተቀባይ ሆነው የሚሰሩት ብዙ ግዜ ኢትዮጵያውያን ወይም ኤርትራውያን ናቸው። ቀደም ባለው ጊዜ ሹፌርም ሆነው ይሰሩ እንደነበር ሰምቻለሁ። በኋላ ላይ ግን ኬኒያውያን አመፁ “እኛ በሀገራችን ስራ አጥ ሆነን እነርሱ እንዴት የማታቱ ሹፌር ይሆናሉ” ብለው “ቀወጡት” ከዛ ወድያው መንግስታቸው “ከዚህ በኋላ አበሻ የማታቱ ሹፌር አያሳየኝ” አለ እና ዜጎቹን አስደሰታቸው።
“ቀወጡት” የሚለው ቋንቋ በአራዳ ብሄረሰብ አባላት ዘንድ የተለመደ ሲሆን “ረበሹ፣ ሀገር ይያያዝ አሉ” የሚል ትርጓሜ አለው። በኬኒያ “መቀወጥ” ብርቅ አይደለም። ማታቱ ውስጥ ሲሳፈሩ ሙዚቃው “ቀውጢ” ነው። መምህራን እና ሌሎች ሰራተኞች በየግዜው ደሞዝ አነሰን እያሉ ይቀውጡታል። የትራንስፖርት ዋጋ ናረ ብሎ ተሳፋሪው ይቀውጠዋል። ወዘተ ሆነ ብለው እነ ወዘተም ይቀውጡታል። ታድያ አንድም ጊዜ “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ የሚያራምዱ ግለሰቦች” ሲባሉ ሰምተን አናውቅም። መንግስት ከቻለ ይመልስላቸዋል። ካልቻለ ምክንያቱን ያብራራል። አለቀ!
እናልዎ፤ በርካታ ኤርትራዊያን ወዳጆቻችን በናይሮቢ ኢስሊ የማታቱ ባለቤት ናቸው። ነገር ግን መኪናቸውን ለመዘወር ህጉ አይፈቅድላቸውም። ስለዚህ ኬኒያዊ ሹፌር መቅጠር አለባቸው ማለት ነው። ባይሆን ገንዘብ ተቀባዩ አበሻ ይደረጋል ወይም ራሱ ባለቤቱ ይሆናል። አንድ የአዲሳባ ታክሲ ሰፈር አባባል ትዝ አለችኝ “ቻንስ ከለሌለህ በራስህ ታክሲ ረዳት ትሆናለህ!” የምትል!
ከማታቱ ሌላ አበሻ በኬኒያ የሚሰራው ስራ ጫት ንግድ ነው። ጫት ንግድ ብቻ ሳይሆን ጫት መቃምም ዋናው የሀበሻ ስራ ነው። ለዛውም ሰዓት ዝንፍ ሳይል በትጋት የሚሰራ የታታሪ ሰው ስራ ነው። ጫት ቅሚያ። ንጥቂያ አይደለም። መቃም ነው። የውበት ሳሎን፣ ሙዚቃ ቤት፣ አነስ ያሉ ምግብ ቤቶች እና አልፎ አልፎ ድለላም የአበሻ ስራ ናቸው። በኢስሊ ዋነኛ ሀብታም ሱማሌዎች ሲሆኑ፤ ከትልልቅ ህንፃዎች ጀምሮ እስከ ትንንሽ የህንፃ መሳሪያ መሸጫዎች ድረስ ሶማሊያውያን ተቆጣጥረዋቸዋል። ይሄ በኢስሊ አካባቢ ነው በጠቅላይ ናይሮቢ ግን ከፍተኛው ባለሃብቶች ህንዶች ሳይሆኑ እንደማይቀር እጠረጥራለሁ።
ኬኒያ ሱማሊያን “አረጋጋለሁ” ብላ ከአልሸባብ ጋር ጦርነት ከገጠመች ወዲህ ፍንዳታ የተለመደ የከተማዋ ክስተት ሆኗል። በቤተ ፀሎት ስፍራ እና በሱቅ አካባቢ “ዷ…. ደሽ” ማለት ተለምዷል። እዚህ ጋ ከአልሸባብ ጋር ኢትዮጵያስ ትፋለም የለ እንዴ!? የታለ ፍንዳታው? ብሎ የሚጠይቅ ይኖራል። ባይኖርም እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ አልሸባብ የማያፈነዳበትን ምክንያት መጠርጠሬ አይቀርም። ጠርጥሬም ለእርስዎ መናገር ግዴታዬ ነው፤ ይከተሉኝማ…
በኬኒያ ከተማዎች አልሸባብ ተደጋጋሚ ፍንዳታዎችን አድርሷል። በኢትዮጵያ ግን ምንም ሰምተን አናውቅም። ምክንየቱ በጣም ግልፅ ነው። የደህንነት ሀይሎቻችን ጥንካሬ አይምሰልዎ! ኢትዮጵያዊ የፈለገውን ገንዘብ ማባበያ ቢሰጠው በሀገሩ ላይ ጥቃት አይሰነዝርም።
በኬኒያ ግን ማንኛውንም ነገር ለማደረግ “ፔሳ” ብቻ ነው የሚያስፈልገው። “ፔሳ” ማለት ገንዘብ ነው። ፔሳ ካለ በኬኒያ የፈለጉት ነገር ሁሉ አለ። አጋነንክ አይበሉኝና… ቢሉኝም ይበሉኝ፤ ኬኒያ ውስጥ ግን፤ የብሩ መጠን ይለያያል እንጂ የቤተመንግስቱም ቁልፍ ይሸጣል።
እዝችጋ አንዴ ወደ አዲሳባ ደረስ ብለን እንመለስ፤ ይህንን የኬኒያ ሁኔታ የነገርኩት አንድ ወዳጄ “…እንደዚህማ ከሆነ ወይዘሮ አዜብም አልወጣም ብለው ስላስቸገሩ ለአቶ ሃይለማሪያም የፈጀውን ብር ፈጅቶ በቦንድም ቢሆን አዋጥተን ለምን ከኬኒያ ቤተመንግስቱን አንገዛላቸውም” ብሎ አሽሟጦኛል። የምር ግን እኒህ ሰውዬ አሁንም ድረስ ከሰፈራቸው ቤተመንግስት እየተመላለሱ ነው የሚሰሩት አሉ። በጣም አንጀቴን ነው የበሉት። እስቲ አስቡት አንድ “የተከበሩ” ጠቅላይ ሚኒስቴር ምሳ ቋጥረው ስራ ውለው ሲመለሱ! ለነገሩ አንዳንዶች እንደሚሉት ቂም ቋጥሮ ስራ ከመስራት ምሳ ቋጥሮ ስራ መስራት በስንት ጣዕሙ! ማነው ቂም ቀጥሮ ሲሰራ የነበረው? ብለው እንዳያስጨንቁኝ… እኔ ስም አልጠራሁም። ነብስ ይማርም አላልኩም። ሆ ሆ… ወዳጄ ሌላ ነገር ሳይመጣ ወደ ናይሮቢ ወሬያችን እናሳልጥ…!
እናም በኬኒያ አልሸባብ ከሚያደርሰው ፍንዳታ ጀርባ፤ ብዙውን ጊዜ አረ እንደውም ሁልጊዜ ገንዘብ የተቀበለ ኬኒያዊ ይኖራል።
ታድያ አንድ ቦታ ፍንዳታ ሲሰማ የአበሻ ቤት በፍተሻ ቁምስቅሉን ያያል። ነገሩ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው። “ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንዲሉ፤ በኬኒያ ደግሞ ፍንዳታ ለፖሊስ ይመቻል ነው። ፍንዳታውን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለማደን “አሰሳ ይደረግ” የሚል መመሪያ ይወጣል። ይሄኔ ፖሊስ ሆዬ በየሀበሻው ቤት እኩለ ሌሊት ሁላ እየሄደ ሻንጣ ይበረብራል። ወንጀሉን የሚፈልግ አይምሰልዎ… “ፔሳ” ነው የሚፈለገው። የፈረደበት አበሻ ቤቱ የመጣውን ፖሊስ ሁላ በሽልንግ እያበሰ ይሸኛል።
ለዚህ ለዚህ መድሃኒቱ ሱማሌ ነው። ፖሊሶች በሆነ ባልሆነው ፍተሻ እያሉ ሲያስቸግሩ ከያሉበት ተጠራርተው መሳሪያ የታጠቀውን ፖሊስ ሱማሌ ነብሴ ቀበቶ እንኳ ሳይታጠቅ ከበባ አድርጎ ሊደበድባቸው ይችላል። ስለዚህ ነው መሰል የኬኒያ ፖሊሶች አበሻን ይበልጥ ይደፍራሉ። አበሻ ፖሊስ ሲመጣበት ካለው በእጁ “ፔሳ” አስጨብጦ፤ ከሌለው በእግሩ ሮጦ ነው የሚያመልጠው።
ኬኒያ በነበርኩበት ጊዜ በጣም ሲያንገበግበኝ የነበረው ነገር በሄድንበት ሁሉ መደፈራችን ነበር። በሀገራችን የገዛ መንግስታችን ይደፍረናል። በሰዉ ሀገር ደግሞ የጠገበ ፖሊስ አበሳችንን ያበላናል። ይሄ በጣም ያበሳጫል። በእውኑ ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮው እንዲህ ነውን!?
በመጨረሻም
ኬኒያውያን ለስጋ ያላቸው ፍቅር ተነግሮ አያልቅም። ወዳጆቼ እንዳሉኝ ከሆነ በኬኒያ የሆነ አለመረጋጋት ነገር ቢከሰት እና ዘረፋ ቢጀመር ዘራፊው መጀመሪያ የሚሄደው ወደ ወርቅ ቤት ሳይሆን ወደ ስጋ ቤት ነው ብለውኛል። የኬኒያ ጎረምሳ ላፈቀራት ልጅ የፍቅሩን ልክ ሲገልፅ እንዲህ ብሎ ነው አሉ፤ “ናኩፔንዳ ዌዌ ከማ ኛማ ቾማ!” ይላታል። ወደ አማርኛ ሲመለስ “ልክ እንደተጠበሰ ስጋ ነው የምወድሽ”
እኔ የምለው እኛም ዘንድ ስጋ ኪሎው 180 ብር ገባ ብሎ የፒያሳው አራዳ ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ ነገረኝ! እኛም ወደፊት ቆነጃጅቶቻችንን “እንደ ቁርጥ ስጋ የተወደድሽው ፍቅሬ!” ማለት ሳንጀምር አንቀርም።
ወዳጄ ለዛሬ ኬኒያን በድርበቡ ለማሳየት ሙከራ አድርጌያለሁ። ወደፊት ብዙ የምናወጋው ይኖረናል። እድሜ ይስጠን ብቻ!

No comments:

Post a Comment