Translate

Saturday, October 13, 2012

ይድረስ ለኢህአደግ መከላኪያ ሠራዊት አባላት በሙሉ !!!


በአንድ ወቅት መለስ ዜናዊ ድርጅታችን በስብሷል ብሎ ነበር። ይሄ እውነት ነው። ህወሃት/ኢሕ አዴግ ከመበስበስ በላይ ሁኗል። የበሰበሰ የሚያሰኘውም በህወሃት መሪነትና አስተማሪነት ድርጅቱ የተዘፈቀበት የዝሪፊያ ማእበል ነው። እነዚህ ዘረኞች የባእድ አገር የያዙ ይመስል በሁሉም አቅጣጫ በዝርፊያ ባህር ውስጥ እየዋኙ ነው። በዝርፊያቸው ጥልቅትና ስፋት የሚተካከላቸው ባለመገኘቱም  በዚያች አገር ሚሊየነሮቹ እነርሱ ሆነው ሌላው እነርሱ ካልፈቀዱለት መኖር እማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ዛሬ ሿሚና ሻሪ፤ ሰጪና ከልካይ እነዚሁ ዘረኞችና ዘራፊዎች ናቸው። እነዚህ ጥቂት ዘረኞች ትግራይን ነፃ እናወጣለን ብለው ከተነሱ እለት ጀምረው በውል የሚታወቁበት በነፍስ ግዲያና በዝሪፊያ ነው። ህወሃቶች ሳይገድሉ መኖር፤ ሳይዘርፉ ባለፀጋ መሆን እንደሚቻል አያውቁም። ከዚህ ነውር ተግባሮቻቸው ተላቀውም ወደ በጎ ሂሊና መመለስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸውም መሪያቸው በስብሰናል ብሎ እንዲናገር ግድ ሆኖበት ነበር። ህወሃት/ኢሕአዴግ በስብሷል ሲባል ወደ በጎ ሂሊና ተመልሶ ከሌሎች ጋር በሰላም ሊኖር የሚችልበትን ግዜና ሁኔታ አልፏል ማለት ነው። ይሄም ማለት ከገባበት ጥልቅ የዝሪፊያ ማእበል እና ከታሠረበት ዘረኛ ሰንሰለት  በልመናም ሆነ በሽምግልና መውጣት አይችልም ማለት ነው።

እንደሚታወቀው ህወሃቶች የሚዋኙበት የዝርፊያ ባህር እንደ ውቂያኖስ ጥልቅና ሠፊ ነው። የዘረጉትም የነፍስ ግዲያ መረብ የህልውናቸው መሠረት ሁኗል። ይህን የህልውናቸውን መሠረት ሠብረው፤ እንደ ውቂያኖስ ጥልቅና ሠፊ ከሆነው የዝሪፊያ ባህር እንዲወጡ ማስገደድ ግዜው የሚጠይቀው ትክክለኛ ተግባር ነው። እነዚህ ነፍሰ ገዳዮችና ዘራፊዎች በፈቃዳቸው ከገቡበት የዝሪፊያ ባህር ውስጥ ወጥተው ነፃነት ወዳለበት መጥተው እርቅ ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ ማለት  “እባብ ሆይ እርግብ ሁኝሊኝ” እንደ ማለት ይቆጠራል። ህወሃት ወደ እርቅ አይመጣም። ህወሃት በዚያች አገር ህዝቡ የሚፈልገው የህግ የበላይነት ሠፍኖ ሠላም እንዲሆን ምንም ፍላጎት የለውም።
እነዚህ ነፍሰ ገዳዮችና በዝሪፊያ ማዕበል ውስጥ የሚዋኙ ብድኖች ከሰሞኑ የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል ሰብስብሰው ሲገመገሙ ከርመዋል። የግምገማቸው ማሠሪያ ሃሳብ “በመሃላችን ጠላት ገብቷል፤ ይህን ጠላት ካላወጣችሁ እንደ ደርግ ወታደር ለማኝ ሁናችሁ ትቀራላችሁ የሚል ነው። ህወሃቶች ክፋታቸው የፈጠረባቸውን ፍርሃት ድሃው ወታደረም አብሯቸው እንዲፈራላቸው እየወተወቱ ነው። ህወሃት የቀደሞውን የአገሪቷን መከላከያ ኃይል በትኖ ሜዳ ላይ በመጣሉ ወታደሩ ለመለመን መገደዱ የሚታወስ ነው። ህወሃት የሚያስበው በራሱ የአስተሳሰብ ደረጃ ስለሆነ እርሱ ያደረገውን ነውር ነገር ሁሉም የሚያደርገው ይመስለዋል። እነዚህ ቡድኖች ነውርን ከደጉ መለየት የማይችሉ የጨካኝ ግለሰቦች ስብስብ መሆኑን ተግባሮቻቸው ሁሉ ህያዋን ምስክሮች ናቸው። በአሁን ሠዓት ነፃነት ይሁን፤ ፍትህ ይንገስ፤ እውነተና ዴሞክራሲ ይምጣ እያሉ ትግል የጀመሩ ኃይሎች ለአገሪቷ ዘላቂ ጥቅም እና ሠላም የሚሠሩ እንጂ እንደ ህወሃት ደምና አጥንት እየቆጠሩ ለበቀል የተዘጋጁ አይደሉም።
ህወሃቶች እንደሚሉት አሁን ባለው መከላከያ ውስጥ ጠላት መግባቱ ሃሰት አይደለም። ይህም ጠላት “እውነት” ይባላል። እውነቱ – ደግሞ ህወሃት የእኔ ናቸው ብሎ የሾማቸው ካርታ ይዘው የቆሙበትን ቦታ ለማሳየት እንኳ ብርቱ ችግር ያለባቸው ጄኔራል ተብየዎች ከድሃው ህዝብ ላይ ዘርፈው ተንደላቀው ሲኖሩ የድሃው ልጅ ወታደር ግን  ከነ ዘመድ አዝማዶቹ የጥቂት ጄኔራሎችና ወዳጆቻቸው አኗኗሪ ሁነው መቅረታቸው ነው። እውነቱ – ጄኔራሎቹ ከህግ በላይ ሁነው በአንድ በኩል ነጋዴዎች በሌላ በኩል ደግሞ የጦር አበጋዞች ሁነው የፈለጉትን አድርገው ሲኖሩ ወታደሩ ግን ሳያውቀው የእነርሱ ወንጀል ተከላካይ ሁኖ መኖሩ ነው። እውነቱ – ጄኔራሎቹ ከድሃው ህዝብ ላይ የዘረፉት ሃብት ለዘመድ አዝማዶቻቸው ተከፋፍሎ ባለ ብዙ ሃብት ባለቤት እንዲሆኑ ሲደረግ የወታደሩ ዘመዶች በርሃብ አለንጋ የሚገረፉ መሆናቸው ነው።
ዋናው እውነት ግን ህወሃት/ኢሕአዴግ ከያዘው ስልጣን ቢወርድ ወታደሩ የሚጎድልበት አንዳችም ነገር አለመኖሩ ነው። ይልቁንስ ህወሃት/ኢሕአዴግ ቢወገድ ወታደሩ ከአንድ ዘረኛ ድርጅት ጥቅም አስጠባቂነት ወጥቶ ለአገሩ ልዕልናና ለዜጎቹም ጋሻ መከታ የሆነ መከላከያ ኃይል መሆን በቻለ ነበር ። ህወሃት ባይኖር ኑሮ በየሜዳው እየወደቀ ተረስቶ የሚቅር ወታደር አስታዋሽ ኑሮት ከወገኖቹ የሚገባውን ክብርና ሞገስ ባገኘ ነበር። ህወሃት ባይኖር ኑሮ በሠላም አስከባሪ ሥም በየባእድ አገራት ዘምቶ ሲያበቃ በስሙ የተገኘውን ገንዘብ የህወሃት የጦር አበጋዞች እርስ በርሳቸው ተከፋፍለው አንቱ የተባሉ ቱጃሮች ሆነው የፈለጉትን የሚጠግኑ፤የጠሉትን የሚሰብሩ ሁነው ቁጭ ባላሉ ነበር። ህወሃት ባይኖር ኑሮ በሶማሊያ ጎዳና ላይ አስከሬኑ የተጎተተው ያ ኢትዮጵያዊ ማን መሆኑን ባወቅነውና ያለ ጧሪ የቀሩ ዘመዶቹ የሚገባቸውን ክብር ማግኘት በቻሉ ነበር። ህወሃት በመኖሩ ወታደሩ ያተረፈው አንዳችም ጥቅም የለም። ለራሱ ማረፊያ አጥቶ ለዘመዶቹም ጋሻ መከታ መሆን አቅቶት በሰቀቀን ለመኖር ከመገደድ በቀር ያተረፈው ሌላ ነገር የሌለው የህወሃት / ኢህአደግ ወታደር የመኖር ህልውናው ከድርጅቱ መኖር አለመኖር ጋር የሚያስተሳስረው ምንም ነገር አይኖርም።
እንዲያውም ህወሃት ከያዘው ስልጣን ቢወርድ ወታደሩ ከዘረኛ እና አድሎዋዊ አስተዳደር ነጻ በመውጣት እስከዛሬ በቃል እንጂ በተግባር አይቶት ያማያውቀው መብትና ጥቅም ባለቤት ይሆናል እንጂ የሚጎድልበት አንዳችም ጥቅም የለም። ህወሃት ከስልጣን ቢወርድ ቀን ከለሊት እየተዘረፈች ያለች አገር እና በችጋር እየተሰቃየ ያለው ህዝብ እፎይ ይላሉ እንጂ በተራው ወታደር ላይ የሚደርስ አንዳችም ክፉ ነገር አይኖርም። ወታደሩን “እኛ ከሌለን ለማኝ ትሆናለህ” በማለት ዘረኛና ዘራፊ አልቆቹ ሊያስፈራሩት የሚሞክሩት   ወታደሩን ተገን አድርገው የሚያካሂዱት ዝሪፊያ የሚያበቃ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በነፍስ ግድያና በዝሪፊያ እጃቸው ተይዞ በስልጣን ዘመናቸው ባዋረዱት ፍርድ ቤት ፊት ለፊት እንደሚገተሩ ስለሚያዉቁ ነው። ወታደሩና ወያኔ ውስጥ ያለው የበታች መኮንን ሁሉ አገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ትግል ፍትህ እኩልነትና የህግ የበላይነት የሚሰፍንበትን ሥርዓት ለመገንባት እንጂ በበቀልና በጥላቻ ስሜት እርሱን ከስራው አፈንቅሎ ለማኝ ለማድረግና ዘረኞቹ በቀድሞው አገር መከላኪያ ሠራዊት ላይ የወሰዱትን አይነት ኢፍትሃዊ እርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ለሥራ አጥነት መዳረግ እንዳልሆነ ጠንቅቆ ይረዳል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ወታደሩ በዘሩና በፖለቲካ እምነቱ ምክንያት እየደረሰበት ያለውን አድሎና በአለቆቹ የሚካሄደውን ዝሪፊያ ስለሚያውቀው የህወሃት ጄኔራሎች የሚነዙትን የፈጠራ ሽብር እንደማይጋሯቸው እውነት ግድ ትለዋለች። በህወሃት ከሥልጣን መወገድ ሊፈሩ የሚገባቸውና ቀን የሚጎድልባቸው ዘርፈው ሚሊነየር የሆኑት፤ንጹሃን ዜጎችን ገድለው የጀገኑ የመሠላቸው እነዚያ ጥቂቶች እንጂ ድሃው ወታደር ሊሆን አይገባም።
ድርጅታችን ግንቦት ሰባት የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ሌቦችን ከንጹሃን ይለያል። አገራችንን የበደሏትም ያዋረዷትም ጥቂቶች ደምና አጥንታቸውን ቆጥረው የተደራጁ መሆናቸውን ጠንቅቆ ይረዳል። ብዙሃኑ ጭቁን ወታደር የአድልዎና የበደሉ ገፈት ቀማሽ እንጂ በምንም መስፈርት የገዢዎቹ አካል ተደርጎ ሊቆጠሩ ይገባል ብሎ አያምንም። ስለዚህ ጭቁን ወታደሮች ከጥቂት ዘረኞችና ዘራፊዎች መረብ ራሳችሁን አላቃችሁ ለፍትህ፤ ለነፃነት እና ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ግንባታ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለማበርከት የምትችሉትን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን። ህወሃት/ኢሕአዴግ በስብሷል። መበስበሱንም በመሪው አንደበት አውጆአል። እናም ደግመን ደጋግመን የምናቀርብላችሁ ጥሪ እናንተ የህዝብ ወገን የሆናችሁ ብዙሃን ወታደሮች ሆይ፤ ከበሰበሰ ስፍራ ምን ታደርጋላችሁ? ኑና ዛሬውኑ የነጻነት ትግሉን ተቀላቀሉ፤ እንዲህም በማድረጋችሁ  ከሂሊናና ከታሪክ ተወቃሽነት ራሳችሁን ነጻ ታወጣላችሁ የሚል ነው።
                    ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment