Translate

Saturday, August 25, 2012

መከተል እና የኅሊና ዳኝነት


ወቅታዊ እና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊመራበት የሚገባ የግል ውሳኔ።
ከአቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወ-መንፈሳዊ
የአስተሳሰብ ለውጥን ለማስረፅ አስቀድመን ራሳችንን ወደውስጥ ስንመለከት ኅሊና ቅድሚያ ሥፍራውን ይይዛል።በተለይም ኅሊና ከዳኝነት ጋር ተቆራኝቶ ሲገለፅ ኃይለ-ቃሉ ምን ያህልETHIOPIAN FLAGጥልቅና ረቂቅ እንደሆነ እንረዳለን።ኅሊና ኅለየ ከሚል የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ዐሰበ ማለት ነው።በእርባታውም ኅልዮ ማሰብ ሲሆን ኅሊና፦ዐሳብ፡ልባዊ፡ረቂቅ ሥራ፦ እያለ ይገልጸዋል።ዳኝነት ደግሞ የሰውን ልጅ ያስተሳሰብ ሚዛን የሚፈትን  ከእዚአብሔር የሚሰጥ ችሎታ ነው።ቃሉ ዳኘ(ዳነየ) ከሳሽ ተከሳሽን ዋስ አስጠራ፣ አስቻለ፣ አነጋገረ፣ ፈረደ፣ በየነ፣ ቃኘ፤ ሕዝብን ጎበኘ፤ ባጠቃላይ በየነ ብለውታል ደስታ ተ/ወልድ በአማርኛ መዝገበ-ቃላት መፅሃፋቸው።እናም የኅሊና ዳኘነት በተግባር ሥጋዊ ይምሰል እንጂ ከእግዚአብሔር የሚሰጠንና በዕድሜና በዕውቀት የሚዳብር የመንፈሳዊ ክህሎት ውጤት ነው።ከዚህ ተነስተን ነው እኛነታችንን እየቀረፅን ትንሿን እድሜአችንን በተፈጥሮ ፀጋ እየመራን እስከዚያኛው ድረስ በምድር የምንኖረው።

ታዲያ በዚህች በምንኖርባት ዕድሜአችን ውስጥ በተፈጥሮ ግንዛቤአቸው ብቻ በተለያዩ ነገሮች ከእኛ የተሻሉ እና የሚበልጡን እንዳሉ ሁሉ፥ የምንበልጣቸው እና ያልተሻሉ መኖራቸውን ልናውቅ ይገባል(ዴዚዴራታን ይመልከቱ)።ቁምነገሩ ልዩነቱን በቅንነት ተመልክተን ከእኛ የተሻሉትን ሰዎች በተሻሉበት ሙያ አክብረን ለትብብር በመዘጋጀት እና አንገታችንን አዙርን በመመልከት ቅን መሆናችን ሲሆን፦ከእኛ ያልተሻሉትን ለመርዳት ደግሞ ፍቃደኛነታችንን መግለጻችን ነው። ከዚህ አንፃር በርዕሴ ላይ እንደገለፅኩት”መከተል እና የኅሊና ዳኝነት”በፍፁም ሳይለያዩ በአንድ ላይ መጓዝ እንዳሉባቸው ልንገነዘብ ይገባል።በተለይ በአሁኑ ያገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የማንንም ሃሳብ ከመደገፋችን በፊትም ሆነ ከመንቀፋችን በፊት መመዘኛ መሳሪያችን ይህ ብቻ ሊሆን ይገባል።በግድ ፖለቲካ ወይም ሐይማኖት መሆን የለበትም።በሰብዓነት በግልፅ ወይስ በድብቅ የሚለው ነው መመዘኛችሁ።
ስለዚህ የአንድን ድርጊት ንድፈ-ሃሳብ ለመፈፀም የኅሊና ዳኝነታችን ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው።እቅዱ በግልፅ እና በቅንነት ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ ቀላልና የምንከተለው ይሆናል።የምናፍርበት ሳይሆን የምንደሰትበት በጎ እና መልካም ተግባር ስለሚሆን በአራያነቱም በምስጉንነት ይኖራል።ስለሆነም ታየም አልታየም ተነገረም አልተነገረም ተወራም አልተወራም ተባለም አልተባለም ምንም በአደባባይ አናፍርበትም።በትንሹ እንኳ ከየራሳችን ሕይወት አልፈን ያገርን ጥፋት ጉዳይ ስንመለከት የዚህ ግንዛቤ ውጤት እንደሆነ ከታሪክ ስላየን እንገነዘባለን።በመረጃ እናስደግፈውና ከስህተቱ እንማር።
ከቅርቡ  የኢትዮጵያ ታሪክ እንኳ ብንጀምር ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወይም ከፕሬዘዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አሊያም ከፕሬዘዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ወይም ከፕሬዘዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ(መለስ በጉልበቱ በሽግግር ወቅት ለራሱ የቀረፀው ሕግ እንጂ ፕሬዘዳንት ሆኖ አያውቅም ሥሙም መነሳት የለበትም።)አመለካከትን መናገር ወይም ድርጊቶች መገለፃቸው ስለሚያሳፍራቸው በሕግ ከለከሉ።እናም በግልፅነት ባለመተማመናቸው እና እርገጠኞች ባለመሆናቸው በክልከላ ሥም ወንጀሎችን ፈፅመው የሚሊዮን ሕዝቦችን የማይደገም ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉት።ሃሳብን መግለፅ ተፈጥሮአዊ ነው።ሌሎች ነገሮች በሙሉ የሚመጡት ከዚህ የመግለፅ መሠረታዊ እና የሰብዓዊ ፍጥረት ሥጦታ ሲሆን ከዚህ ንፍገት የሚነሱ ወንጀሎች ናቸው ችግሩን ውስብስብ የሚያደርጉት።ቻይና፣ራሺያ፣ኩባ ድፍን አፍሪቃ እና ኤሺያ በሙሉ በሽታቸው”መደበቅ”ነው።
ለዚህ ነው በምሁራን ዘንድ እንደሚባለው “እኔ ይህንን የምከተለው ወይም በተግባር የምፈፅመው ስለተባልኩ ሳይሆን ስላመንኩበት ነው።”የሚሉት።
በጣም መጠንቀቅ የሚያስፈልገን ስለተከተልን ወይም ስላደረግን አይደለም ወንጀል የሚሆኑት በግልፅ በሕዝብ(በሕብረተሰባችን)ዳኝነት የተወሰነውን አለመፈፀማችን ነው።ይህ እምቢታ ውሸትን ማጭበርበርን ሌብነትን ድብቅነትን እና ሌሎችንም ይፈለፍልና ወንጀል ሆኖ በፈጻሚው አዕምሮ ውስጥ ይወለዳል።ለኅሊና ዳኝነት ከተገዛን ግን የሚደረገውን በጉልበት ሳናከላክል እንዲደረግ ወይም እንዲሆን ፈቃደኝነት ኖሮን ፍርዱን መቀበል ብልኅነት ነው።በዚህ አጋጣሚ ሰዎች በጎ ነገር ሊያደርጉ ሲያስቡ ተንኮለኞች እያጨበጨቡ እንደማይቀመጡ ተረድተን መፍትሄው ግልፅነት ብቻ መሆኑን ማወቅ ብቻ ነው።ከዚያ በኋላ አውቀንም ቢሆን አለመናገሩን የምንወስነውና የምንጋፈጠው እንደአቅማችን አንፃር ብቻ ነው።
በዚህ መሃል በምሳሌነት ሕይወተ-ክርስቶስን  ከመፅሐፍ ቅዱሳችን አውጥቼ የተወሰኑ የተቃርኖ ምሳሌዎችን <ከመከተል እና የኅሊና ዳኝነት> አንፃር በሌላ ማዕዘን ሆናችሁ እንድታዩልኝ ለማመላከት እወዳለሁ።”ክርስቶስ ሞሞቱ ላይቀር ይሁዳ ሰበብ ሆነበት፤”የሚለውን ሐቅ ምን ያህል እንደምትረዱልኝ  እርግጠኛ አይደለሁም።በእኔ አስተያየት ግን መፈታተን ባይሆንም”ማዳም ኩሪ ሜርኩሪን አገኘችም አላገኘቺም አንድ ቀን ባንዱ ግለሰብ መገኘቱ አይቀርም እላለሁ፣እንደተማርኩት፤የእሷ ግኝትም የአጋጣሚ ነው ባይ ነኝ።የተነሳሁበት ነጥብ ግን በትንቢት የተነገረ ስለሆነ በመጥፎ ጎኑም ቢሆን ይኸው በክርስቶስ ደም ከኅጢያታችን እንድንድን ቀላሉን ነገር “ማመን” ብች እንድንከፍል አድርገው አቅልለውልናል።
እስኪ እነዚህን ጥያቄዎች እና መልሶች ብቻ በጥልቀት እንመልከት፦
ጥያቄ-ክርስቶስ የሞተው በማን ውሳኔ ነው?መልስ፡በእስራኤል ሕዝብ።ሌላው፡ያለም፡ሕዝብ ግን ድምፅ ለመስጠት አልተጠየቀም፡ሳናይ፡ግን አምነናል።
ጥያቄ፡ክርስቶስ መሞት ነበረበትን?መልስ፦በትንቢቱ መሰረት፦አዎን።ምክንያቱም አባቱ የላከው ሕዝቡን ከኅጢያት በደሙ እንዲያነፃ ነውና።
ጥያቄ፡ክርስቶስስ ውሳኔውን አልቀበልም አለ???መልስ”አምላኬ ሆይ እንደፍቃድህ ይሁን”ብሎ ተቀበለ።በስቃይም ተገደለ፤ተቀበረ እናም አረገ።አሜን
ይህን ምሳሌ ያነሳሁት በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን ሁሉ ያለችን ሕይውት በአንድነቷ ለእኛ እንደምናምነውም የሌላውን ስለምንዘነጋ ነው።
እኛስ በየግላችን የምናደርገው ተግባር ወይም የምንሰራው ሥራ በሕዝብ መዳኘቱን እንቀበላለን??ትልቁ ፈተና ይህ አይደለም።
ትልቁና መጨረሻ የሌለው ፈተና በግል የኅሊና ዳኝነታችንን የሚፈታተነን አቢይ ጉዳይ በግልፅ የሚፈፀመውን ነገር ነው የምንደግፈው? ወይስ ብድብቅ የሚደረገውን (ወንጀል) ? ?የሚለው ነው።
ትልቁ ፈተና ይህ ነው፤የእያንዳንዳችን የግል ውሳኔ ሊሆን ይገባል።ይህንን አውቀን ከፈፀምን ስለተባልን ሳይሆን (በቂ መረጃዎችን በግልፅነት ውስጥ እናገኛለንና)ስላመንንበት፤መከተልም አይደለም፣መምራትም አይሆንም፤ በጋራ እንፈፅመዋለን።ምክንያቱም ትክክል መሆኑን የ-ም-ን-ዳ-ኘ-ው በሕዝብ ብቻ ነውና።
በመጨረሻም የሕይወቴ መመሪያ በሆነው “የዴዝዴራታ” ጥቅስ ቅንጣቢ ጦማሬን ልደምድም።
” እባክዎ ከፊት ከፊቴ ቀድመው አይራመዱ:-ላልከተልዎት እችላለሁ::ከበስተ-ኋላዬም ሆነው አይራመዱ አልመራዎትም ይሆናልና::
ይልቅስ በእኩልነት እና በንፁህ ልቦና ከጎኔ ሆነው በሰብዓዊነት አብረውኝ ይጓዙ::”

No comments:

Post a Comment