Translate

Thursday, August 30, 2012

“ቴዲ ለመለስ ነጠላ ዜማ ለመስራት ሀሳብ የለውም”


Tewodross Kassahun Ethiopian pop singer “ቴዲ ለመለስ ነጠላ ዜማ ለመስራት ሀሳብ የለውም” ዘካርያስ ጌታቸው (የቴዲ አፍሮ ማናጀር)

ፍኖተ ነጻነት
ታዋቂው አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የሟቹን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት አስመልክቶ ነጠላ ዜማ አዘጋጅቷል መባሉን የድምፃዊው ማናጀርና የአዲካ ኮሙኒኬሽን ሚዲያ ማናጀር ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አስተባበሉ፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም አቶ መለስ ከዚህ አለም በሞት የመለየታቸውን ዜና መንግስት ይፋ ካደረገ በኋላ ላለፉት ሰባት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን መታወጁን ተከትሎ ታዋቂው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የአቶ መለስ ዜናዊን ሀዘን ምክንያት በማድረግ ነጠላ ዜማ ለቋል የሚሉ መረጃዎች ሲሰራጩ ሰንብተዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ድምፃዊው በብሄራዊ ቤተመንግስት በመገኘት ሀዘኑን ለመግለጽ በሞከረበት ወቅት በስፍራው የተገኘው ህዝብ ጩኽት በማሰማቱ ወደ ውስጥ ሳይዘልቅ እንደተመለሰ ተናግሯል፡፡

ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአዲካ ኮሙኒኬሽን ሚዲያ ማኔጀር ሠርካለም ታፈሰ ግን ቴዲ አፍሮ ለአቶ መለስ ምንም አይነት ነጠላ ዜማ አለመስራቱን ተናግረው “ከሁለት ዓመት በፊት የሰራውን ሙዚቃ በአቶ መለስ እና በቴዲ ፎቶዎች በማጀብ የተቀናበረ ምስል በዩቲውብ ተለቆ አይቻለሁ” ካሉ በኋላ ቅንብሩ ከቴዲ እውቅና ውጪ እንደተሰራ ለፍኖተ ነፃነት አረጋግጠዋል፡፡ የቴዲ አፍሮ ማናጀር የሆኑት አቶ ዘካርያስ ጌታቸውም ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው “ቴዲ ምንም አይነት ሙዚቃ አልሰራም፤ ለመለስ ነጠላ ዜማ ለመስራት ሀሳቡም የለውም” ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ቤተመንግስት አጋጠመው የተባለውም ተቃውሞ መሠረት ቢስ መሆኑን አብራርተው “አርብ ዕለት ቤተመንግስት ሳንገባ የተመለስነው በተቃውሞ ምክንያት ሳይሆን ለጀነራሎች የተዘጋጀ ልዩ የሀዘን ስነ ሥርዓት በመኖሩ ነው” ካሉ በኋላ በስፍራው የነበረው ህዝብ የአድናቆት ድምጽ ማሰማቱን ብቻ እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዘካሪያስ ጌታቸው ጨምረውም በትላንትናው ዕለት ቴዲ አፍሮ ብሔራዊ ቤተመንግስት በመገኘት ለቅሶው እንደደረሰ የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ አረጋግጠዋል፡፡ ታዋቂው ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ በ1997 ዓ.ም ያስተሰርያል በሚል ርዕስ ባወጣው አልበሙ ምክንያት ከመንግስት ጋር እሰጣገባው ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ በአወዛጋቢ ክስ ከሁለት አመት በላይ በቃሊቲ በእስር ማሳለፉም አይዘነጋም፡፡

No comments:

Post a Comment