Translate

Wednesday, August 29, 2012

የመድረኩ ሊቀመንበር ስለ አቶ መለስ ዜናዊ ምንም አይነት ምስክርነት እንዳልሰጡ ገለጡ::


ነሀሴ ፳፫ (ሀያ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋዜጠኞች የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ የሰጠሁትን የሐዘን መግለጫ ወደ ጎን ጥለው የራሳቸውን የፈጠራ ድርሰት አዘጋጅተው አስተላልፈዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንዳሻው ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
አቶ ጥላሁን የሀዘን መግለጫውን ባስተላለፉበት ወቅት የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋዜጠኞች ስለ ጠቅላይሚኒስትሩ የስራ ሁኔታ አስተያየት ለመቀበል ጥያቄ አቅርበው ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደሌለው በመግለፅ ምንም አይነት አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን መግለጻቸውን አውስተዋል።
የማዕከሉ ሰዎች ግን ከሌሎች ሚዲያዎች በተለየ ሁኔታ የራሳቸውን የፈጠራ ድርሰት በማዘጋጀት ከእርሳቸውም ሆነ ከመድረክ አቋም ጋር ተፃራሪ የሆኑ ኀሳቦችን ማስተላለፋቸውን ገልፀዋል። “የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ሰዎች እኔየሰጠሁትን መግለጫ በመተው የራሳቸውን ኀሳቦች በማካተት እጅግ አስነዋሪ በሆነ መልኩ በእኔ ስም ፅፈው ነሐሴ 23 ቀን 2012(እ.ኤ.አ) በኢንተርኔት ድረ-ገፃቸው ላይ ለቀውት መመልከት ችያለሁ” ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ ይህንኑ ጠቅሶ ነሐሴ 24 ቀን 2012 እትሙ መዝገቡን ገልፀዋል።

ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልም ሆነ ሄራልድ ጋዜጣ በዘገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ስርዓት መስፈን፣ ለሕግ የበላይነትና የሰብአዊ መብቶች መከበርና ድህነትን ለማጥፋት ከፍተኛ ሥራ እንደሰሩ ተደርጐ በእኔ ስም መስክረዋል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ “የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ሰዎች ይህን በራሳቸው ስም የመመስከር እንጂ እኔ ሳልወክላቸው በእኔ ስም የመመስከር መብት የላቸውም” ብለዋል።
ላለፉት 21 ዓመታት ለዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ስለፍትሐዊ ሥርዓት መስፈን ስለ የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እና ድህነትን ማጥፋት በኢህአዴግ አገዛዝ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመሸንገል ያህል የሚወራው ፕሮፓጋንዳ በተግባር ላይ ውሎ አለማየታቸውን የገለፁት አቶ ጥላሁን፣ ይህንንም በመቃወም እና በወረቀት ላይ የቀሩት ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ በአመራር አባልነት ተሰልፈው እየታገሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
“እነዚህ መብቶች በእርግጥ በእርሳቸው አመራር ስራ ላይ ውለው ቢሆን ኖሮ የስርዓታቸው ተቃዋሚ የምሆንበት ምክንያት አልነበረም። በእኔ እምነት እነዚህ መብቶች አሁንም በአግባቡ ሥራ ላይ ያልዋሉ ስለሆነ በሥራ ላይ እስኪውሉ ድረስ የሥርዓቱ ተቃዋሚ ሆኜ ትግሌን የምቀጥል ይሆናል” ብለዋል።
አቶ ጥላሁን የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል የፈጠራ ወሬ ያሉት ማእከሉ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነሀሴ 24 ቀን 2012 ” በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለፁ በሚል ርእስ ያወጣውን ዘገባ ሲሆን፣ ዘገባውም እንደሚከተለው ይላል።” ” የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድንት መድረክ ሊቀ-መንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ስርዓቱ እውን እንዲሆን ያስቻሉ በሳል መሪ ነበሩ ብለዋል። በሀገሪቱ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁና ህዝቡ ከድህነት እንዲላቀቅ ያደረጉት ጥረት ሁልግዜም እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ፓርቲያቸው ስልጣን ላይ ካለው ገዢ ፓርቲ ጋር በአገር ጉዳይ ላይ ተግባብቶ ለመስራት ፍቃደኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ከተተኪው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋርም በመግባባት ለመስራት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።”
አቶ ጥላሁን ” በፈጠራ ወሬ አገር አይገነባም ” በሚል ርእስ የዋልታን ዘገባ ለመቃወም ወረቀት አዘጋጅተው ለጋዜጦች መበተናቸውን ተናግረዋል::

No comments:

Post a Comment