Translate

Thursday, August 30, 2012

ሳይደረጁ እንደርጅ

Author and writer Tesfaye Zenebe from Norway
ከተስፋዬ ዘነበ (ኖርዌይ በርገን)
30-08-2012
“አምላክ ሲቆጣ ልምጭ አይቆርጥም ያረጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም”  ይሉ ነበር ልጅ እያለን  አንድ የሰፈራችን አዛውንት ፡፡ ይህው እንግዲህ ለሃገር ለምድር ከብደውም ይሁን?
እራሳቸውን አክብደው፣ በህሊና ቢሶችና ለሆዳቸው ባደሩ ጥቂት ሰዎች እስከ መመለክ የደረሱት ፈላጭ ቆራጮች አምላክ ለኢትዮጲያና ለህዝቡዋ አስቦ  ወይም የምድሩን ፍርድ እንዳያዩ እርሱ ፈቅዶ የጥፋት ዘመናቸውን ጨርሰው እስከ እኩይ ስራቸው የፈነጩባትን ምድር ተሰናብተዋል፡፡
እንደ  ሰማነው  ከሆነ እንግዲህ በአብዛኛው የዛኛው መንደር ጉልቤዎች የመቃብር ጠርዝ ላይ ሆነው አንዱ  ለአንዱ ሳይሆን  ሁሉም ለየራሱ እያለቀሰ  እና እያስለቀሰ በሚመስል ሁኔታ አገሪቱን የሙሾ ተቋም አድርገዋታል፡፡

እንደሚታወቀው  ሟዋች በስልጣን ዘመኑ ማለትም ለሁለት አስርተ አመታት በወጣና በገባ ቁጥር  ከምኒልክ  በቤተ-መንግስት እስከ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ድረስ ለመግለፅ በሚያሰቸግር ሁኔታ ስፍራው በአጋዚ እየታጠረ፣ መንገድ ተዘግቶ ነዋሪው እየተዋከበ፣ ከመንገድ ግራና ቀኝ ያሉ ህንፃዎች ማማ   ሳይቀር በአልሞ ተዃሽ ተከቦ፣ ህዝብ ጀርባውን ሰጥቶ እንዲቆም ተደርጎ፣ በከፍተኛ ጥበቃ በሽፍን ብረት ለበሰ ተሽከርካሪ  በከፍተኛ ፍጥነት ሲደርስና ሲመልስ የነበረው መለሰ !. . . . .ለስድብና ለማስፈራራት  በቴሌቪዢን መስኮት ሲመጣ  ከማየት በሰተቀር በአካል የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር የአሁኑን ሟዋችን በአይኑ አይቶት የማያውቀው ሕዝብ  የመሪውን  በድን ለመቀበልም ሆነ ለቅሶ ለመድረስ ዝናብ እና ብርድ ሳያግደው ለያዥ ለገናዥ ማሰቸገሩ ግርምትን ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እነ በረከት አለቃቸው በሕይወት ዘመኑ ሲሸሽ እና ሲደበቅ የነበረውን ሕዝብ! በገንዘብ እና በምልጃ  ይዘው ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ አይን ያወጣ ተግባር ቢፈፅሙም ህዝብ እንደ ህዝብ የሞት አፋፍ ላይ ላለው ዘረኛ  ሰርዓት መጠቀሚያ መሆን አልፈልግም፣  እምቢ፣  አሻፈረኝ ማለት አለመቻሉ ህዝባችን ምን ነካው፣ ወገኔን ምን ነካው ያሰብላል፡፡ ታማሚውን ከየሆስፒታሉ፣  የዚሁ ስርዓት  ውጤት የሆኑትን የጎዳና ተዳዳሪውን ከየ ታዛው ሰብስበው በህይወት ዘመኑ የጠላቸውን፣ እንደ ዜጋ ሳይታዩ ሜዳ የወደቁትን ምንዱባኖች  ነውር የማያውቁት እነበረከት ያለቃቸውን በድን እንዲሰናበቱ  በሚል ሰብስበው   ማስነባታቸው  ስርዓቱ አሁን ያለበትን የንቅዘት ደረጃ የሚያሳይ ነው፡፡
ህዝብ አርባውን ያወጣለት የመለስ  ሞት እንደ አዲስ ተሰምቶ  አስከሬኑ ለአንድ ወር ከምናምን ከተቀመተበት ማቀዝቀዢያ ወጥቶ አዲስ አበባ  በግባበት ወቅት የሟች ባለቤት አዜብ መስፍን ይታይባት  የነበረው መሪር አዘን  እና  የመንፍስ  ስብራት  የኢትዮጲያ ህዝብ  በዚህ ህኩይ ስርዓት ከደረሰበት  ከቃላት በላይ ከሆነው ግፍ እና ሰቆቃ   ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነው ፡፡
ይህ ስርዓት እና  የስርዓቱ ቁንጮ የሆነው መለስ  ከዘር  የወረሰውን  ኢትዮጲያን እና ኢትዮጲያዊነትን  የማጥፋት ህልሙን መፍታት  የመጀረው ገና በጠዋቱ ስለመሆኑን  ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ አንደኛውና  ዋንኛው ኤርትራን ሕጋዊና  ፍታዊ ባልሆነ መንገድ ማስገንጠሉ ሲሆን በተጨማሪም የባህር በር የማግኘት መብታችንን በፈቃዱ አሳልፎ በመሰጠት  አገራችንን  ካለባህር በር ማሰቀረቱ  መለስ  በአገርና በሕዝብ ላይ የፈፀመውን ክህደት ያሳያል፡፡ በመቀጠልም  ከሻቢያ ጋር  የነበረው ወዳጂነት  ወረቱ ሲያልቅ  መጀመሪያው አና መጨረሻው ላልታወቀ ለኢትዮ-ኤርትራ  ጦርነት በአስር ሺዎች  የሚቆጠሩ ወጣቶችን ለግል ቂም መወጫ  ጭዳ ያደረጋቸው  ይኸው  አንባገነን  መሪ  ነበር፡፡  ከዚህም በላይ  በሰብአዊ መብቶች  ጥሰትም ሆነ  የአገራዊ  ጥቅምን  ከማስከበር  አንፃር  ይህ  እንደ መጅገር  የተጣበቀብን  ዘረኛና ከፋፋይ  ቡድን እጅግ ብዙ ብዙ  ተነግሮ የማያልቅ  በደልና ግፍ  በአገር እና  በህዝብ ላይ  ፈፀሟል  እየፈፀመም ይገኛል፡፡
ዛሬ ወደ ተነሳሁበት  እርዕሰ ጉዳይ ላምራ፡፡ እንደሚታወቀው ገዢዎቻችን እንደ ወትሮው አዲስ አመትን በደስታ፣ በፈንጠዝያ ለመቀበል አልታደሉም  ወር ተራውን ጠብቆ  የህዝብ እንባ እና አዘን የበደል ፅዋውን ሞልቶ  እነሱም ቤት ዋይታ እና ጩኸት ሆኖ ማቅ  ለብሰዋል፡፡ የዘለኛው ስርዓት ሰወችም ሆኑ የስርኣቱ  አቀንቃኞች  በንፁሃን ደም የጨቀየ እጅ ያለውን እና አገር ሲሸጥ እና ሲመዘብር  ዘመኑን የጨረሰውን  አምባገነን  መሪያቸውን  ሞቶም ይፈሩታል መሰል  ጀግና፣ ባለህራዪ፣  አዘኝ  ምናምን እያል  ያቆለጳጵሱታል፡፡  ከህግና ከስርዓት  ውጪም በዛች ደሃ አገር ላይ አስራ ሶስት  ቤሄራዊ የሀዘን ቀን  አውጀው ደሃውን ለፍቶ አዳሪ  ኑሮውን ያከብዱበታል፡፡ ህዝቡንም በሀዘን ድባብ ሸብበው ውስጥ ውስጡን  እንዴት በባርነት ረግጠው  እንደሚገዙን እቅድ ይነድፋሉ፣ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በቴሌቪዥን  ለህዝቡ ሙሾ  እያሳዩ  እነሱ   በውስጣቸው የተፈጠረውን  ልዩነት  ለመቅረፍ ይገማገማሉ፡፡
እኛም በዚኛው ጎራ ያለን ዘመን በተለውጠ ቁጥር  የአቋም  መግለጫ ስናወጣ፣ በቃ ስንል፣ ገዬ ስንል፣ ስንቧደን  ስንለያይ  የጋራ ጠላታችን  ላይ በአንድነት መነሳት  ሲያቅተን እርስ በእርስ ስንጠላለፍ ፣ ደግሞ ሌላ ድርጅት መጣ (ተመሰረተ ሲባል) ሳናውቀው ለእሱ ስንዘምር፣ ስንመሰክር  ይህው ስናስር ስንፈታ  በገዢዎቻችን ጥንካሬ ብቻ  ሳይሆን  በኛ  ድክመት  ያልተፈታ  ህልም  ይዘን እዚህ  ደረስን፡፡የግፍ ቀንበር  የተሸከመው ህዝብ እከሌ የሚባል በዚህ ተነስቷል  ነፃ ያወጣኛል  ሲል፣ እገሌ በዚህ መጣ ሲል ነፃነት  እየናፈቀው፣ ነፃነት እያማረው በገዛ አገሩ በግዞት ይኖራል፡፡ ይህ የተገፋ ህብረተሰብ የሚመራው የሚያስነሳው  ድጋፍ፣ ዋልታ የሚሆነው  ሰለጠንኩ፣ ተማርኩ፣ አወኩ ከሚለው የህብረተሰብ ክፍል ይፈልጋል፡፡
ባለፉት አመታት በአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ስለበደላችን፣ በስርዓቱ ሰለሚደርስብን ግፍና ሰቆቃ፣ ስለችጋሩ፣  ሰለአገራችን ለባህዳን መሸጥ እና መቸብቸብ፣ ስለየዜጎች  ሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሰለምዝበራ ወ.ዘ.ተ. . . . በተለያዩ ሁኔታዎች  ለህዝባችንም ይሁን ለአለም አቀፉ  ህብረተሰብ  ስናሳውቅ ቆይትናል፡፡ ለዚህም  ነው  አብዛኛው  አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን  ሰውየው  ገና አፈር  ሳይገባ  ሰለ ጭካኔው መዘገብ የጀመሩት፡፡
ሁሉም ነገር በእኛ  ወገን ነው ያለው፡፡ጊዜ ሰጥተን እንዲደራጁ ልንፈቅድላቸው አይገባም፡፡  አሁን በተፈጠረው የወያኔ መፍረክረክ ተጠቅመን  ልዩነታችንን አቻችለን ለዚህ ህዝብ እና  ለዚች አገር ልንደርስ ይገባል፡፡ ከስብሰባ፣ ከሴሚናር፣ ከአቋም መግለጫ በዘለለ አሁን  በአይን የሚታይና  በተግባር የታገዘ  ትግል  የሚያስፈልግበት  ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ከዚህ በፊት ባመለጡን እድሎች  ከተቆጨን  አሁን ባገኘነው አጋጣሚ  መጠቀም  አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ተራራ  የሚያክል  እውነት  እያለን  ጠጠር የምታህል የትግል መንፈስ ካጣን  እውነታችን እውነት የሚሆነው ምኑ ላይ ነው፡፡
ወያኔ አሁን ካለብት ሁኔታ ሳያገግም  እና ሳይድራጅ አኛ ደርጅተን  በተባበረ የትግል መንፈስ  እርቃኑን የቀረውን አፋኝ  እና  ዘረኛ  ሰርዓት በአንድ ኢትዮጲያ ጥላ ስር  ሆነን ዘር እና ሃይማኖት ሳይለየን  በጋራ ለትግል እንነሳ፡፡
ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ ሞት ለወያኔ !!
ለአስተያየቶ፣ ftih_lewegen@yahoo.com

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/4132

No comments:

Post a Comment