Abe Tokchaw
ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ…
በቅጡ ካወጋን እኮ ዛሬ ወደ አራት ነው አምስት ቀን ሊሆነን ነው። ቢያንስ አራቱን ቀናት ታምሜ አበሳዬን ሳይ እንደነበር በፌስ ቡኬ ላይ ነግሬዎታለሁ! “እግዜር ይማርህ…” ላሉኝ እግዜር ይስጥልኝ፤እግዜር ይጨርስህ ላሉኝ ደግሞ እግዜር ይማርልኝ! አሁን በጣም በጥሩ ብቃት ላይ እገኛለሁ… ይኸው “ከአዲሱ አመት እጅግ ቀድሜ” እንኳን አደረሰን ብያለሁ! ይህንን ንግግር የት ነበር የማውቀው አሉ እንዴ…! ወዳጄ፤ አቶ በረከት ስምዖን ጥፍት አላሉብዎትም…!?
እኔ የምለው፤ አዲስ አመት በር ላይ ቆሞ አይደል እንዴ!? እንዴት ደስ ይላል! “የጎመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምንቸት ግባ” ብለን በአንድ ድምፅ መልካሙን የምንመኝበት ትክክልኛው ወቅት ላይ እኮ ነን።
በነገራችን ላይ እኔ እንዳመላከተኝ ከሆነ ዘንድሮ የጎመን ምንቸት ቀድሞ ወጥቷል። የገንፎ ምንቸት ግን ገና ደጃፍ ላይ ሆኖ ልግባ አልግባ እያለ ይገኛል።
የጎመን ምንቸት ግርግር ሳያበዛ ታህሪር አደባባይን ያኽል ሰው ይውጣልኝ ሳይል “ላጥ” ማለቱን በበኩሌ በጣም ተስፋ ሰጪ ነው ባይ ነኝ። የገንፎ ምንቸት ኩራት እና ጅንን ማለት ግን ደስ አላለኝም። ታድያ ለምን እንዲህ ብለን በግጥም አንጣራም? “ተገጥሞ ተሙቷል” ብሎ ማሽሟጠጥ ይፈቀዳል!
የገንፎ ምንቸት ቶሎ ግባ!
ጎሽ የጎመን ምንቸት
እንደዚህ ነው ደጉ
አፍነህ ይዘኸን
በፆም በፍስጉ
ውጣ… አትውጣ ብለን
ሳንከፍል ብዙ ዋጋ
ውልቅ በማለትህ
ብለናል “ሀይሎጋ!”
አንተ የገንፎ ምንቸት
የቆምከው ከበሩ
ባክህ ቶሎ ግባ
ይቅር መግደርደሩ
በጎምን የታሸን
ብዙ ነን በርካታ
ግባ ባክህ ገንፎ
ከውጭ አታመንታ
ያኛው ምንቸት ወጥቷል
ማንም የል ከቤቱ
ሳትሰጋ ሰተት በል
የአንተ ነው ሰዓቱ
በቃን ብዙ ፆምን
ከሃያ አመት በላይ
ገንፎ ምንቸት ግባ
አትቁም በር ላይ!
ስላነበባችሁልኝ አመሰግናለሁ። አዲሱ አመት የማንታፈንበት፣ የማንሰደድበት፣ የማንሰደብበት፣ የማንራብበት፣ እና የማንደፈርበት ይሁንልን። ይህ ይሆን ዘንድ አንድነት የግድ ያስፈልገናለንና አንድ ያድርገን!
አሜን!
No comments:
Post a Comment