ህወሓት የድርጅቱን መሪዎች መምረጡን ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረት አቶ አባይ ወልዱ ሊቀመንበር፣ ዶ/ር ደብረጽዮን ወልደ ሚካኤል ምክትል አድርጎ ሰይሟል። ምርጫው የተከናወነው መቀሌ ሳይሆን አዲስ አበባ ነበር። ሴፕቴምበር 19 ይፋ የተደረገውን የህወሓት ምርጫ አስመልክቶ ህወሓት መግለጫ አሰራጭቷል።
ህወሓት በምርጫው ያልተገመቱና አዲስ አመራር ወደ ሃላፊነት አምጥቷል። እርሳቸውም ዶ/ር ደብረጽዮን ወልደ ሚካኤል ናቸው። በሚኒስትር ማዕረግ የኢንፎርሜሽንና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተርና የኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን በነባር ታጋዮች ዘንድ እይወደዱም።
ደብረጽዮን ወልደ ሚካኤል በደኅንነቱ የሚከናወኑ ከፍተኛ ጉዳዮችን የሚመሩ፣ ከፍተኛ ውሳኔዎችን የሚወስኑ፣ የአገሪቱን የደኅንነት መዋቅር ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ጎን ለጎን የሚመሩ መሆናቸውን በቅርብ የሚያውቁ ይገልጻሉ። ህወሓት የገነባውን የደህንነት መዋቅር በታማኝነት የሚቆጣጠሩት አዲሱ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ህወሓት ለሁለት በተከፈለበት ወቅት አቶ መለስ በአሸናፊነት እንዲወጡ ታላቅ ሚና መጫወታቸውን በብዙዎች ይፋ ያልወጣ ግለ ታሪካቸው ነው።
ለአቶ መለስ እጅግ ቅርብ የሆኑት ደብረጽዮን ህወሓትን ወክለው የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር እንዲሆኑ በህወሓት በኩል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ የጎልጉል የመረጃ ምንጮች አስታውቀዋል። በዘመነ ህንፍሽፍሽ ህወሓት ለሁለት መሰንጠቁ ይፋ ከመሆኑ በፊት ልዩነቱ ውስጥ ውስጡን በተጋጋመበት ወቅት አቶ ደብረጽዮን ከአቶ መለስ የተቀበሉትን ልዩ ተልዕኮ ለመተግበር ያስችላቸው ዘንድ የሽሬ ምክትል አስተዳዳሪ ተደርገው ተሹመው ነበር። አፈንጋጭ የተባለውን ቡድን ከሚመሩት መካከል ዋና ኃይል አላቸው ተብለው የሚፈሩት አቶ ስዬ አብርሃ በትውልድ መንደራቸው ተምቤን ውስጥ ያላቸውን ሰንሰለት ለመበጣጠስና ለማምከን ልዩ ተልዕኮ ይዘው ወደ ሽሬ ያመሩት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ሃላፊነታቸውን በመወጣት ለመለስ አሸናፊነት ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ምንጮቹ ጠቅሶ ጎልጉል ዘግቦ ነበር።
No comments:
Post a Comment