Translate

Saturday, September 22, 2012

“እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ማነው? ኃይለማሪያም አይደለምን…!?”



ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ወይ ጊዜ ድሮ ድሮ አረ የምን ድሮ ከሶስት እና ከአራት ወራት በፊት ብዙዎች መለስን ሲግለፁዋቸው ገዳዩ እና አምባገነኑ እያሉ ነበር። በእርግጥ እኔ እንደዛ ብያቸው አላውቅም። እኔ መለስን ገዳይ ካልኳቸው ግፋ ቢል በሳቅ ይገሉኛል ለማለት ይሆናል እንጂ በግልፅ ይፋ በሆኑ ሪፖርቶች ላይ እንደሚታየው በትንሹ የባድመውን የተሳሳተ ጦርነት ሳይጨምር የሶስት ሺህ ሰዎች ደም በእጃቸው ላይ እያለ ጨክኜ ገዳይ ብያቸው አላውቅም። (በሌላ ቅንፍ ቡቡ እኮ ነኝ!)) የሆነው ሆኖ ጊዜ ደጉ “ገዳይ” ሲባሉ የነበሩትን ሰውዬ “ሟች” እያልን እንድንጠራቸው አድርጎናል። ሞት አይቀርም ከቶ ምንም ታክቱ ምን ቢከተክቱ… ብለን በአዲስ መስመር እንቀጥል።
ሟቹ ጠቅላ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ… በህይወት ዘመናቸው 21 ዓመታት እንዲሁም በአስከሬናቸው ለሶስት ወራት አስተዳድረውን ሲያበቁ አሁን ደግሞ መንፈሳቸው በአዲሱ ሰውዬ ላይ ሆኖ ሊመራን የተዘጋጀ ይመስላል። ትላንት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባደረጉት ንግግር ለትህትና ይሁን የምራቸውን ይሁን እናጃ እንጂ “የኔ ስራ እንደ መለስ ዜናዊ ሆኖ መተወን ነው” አይነት ንግግር ሲናገሩ ሰምተናቸዋል። ይህንን ንግግራቸውን የሰማው የኢሳቱ ደረጄ ሀብተወልድ አንጀት ላይ ጠብ የሚል የአዋቂ ሰው ምክር መክሯቸዋል። ምን አላቸው….?
“ዳዊት ጎልያድን እንዲገጥም ሲላክ የንጉሥ ሳዖልን ካባና ሰይፍ ነበር ያለበሱት።ሆኖም ልኩ አልሆነም።ካባውም ሰፋው፣ሰይፉም መሬት ለመሬት ተጎተተ። በዚያመልኩ ወደ ጎልያድ ቢሄድ ኖሮ የሚጠብቀው ዕድል ሽንፈት ነበር።ዳዊት ግን-የንጉሥ ካባና ሰይፍ ስለሆነ ብቻ ፤ልኩ ያልሆነን ትጥቅ ታጥቆ ወደ ፍልሚያውመግባት አልፈለገም።ለዚህም ነው የሳዖልን ካባና ሰይፍ አውልቆ በመጣልወንጭፌን አምጡልኝ!”ያለው።እናም ወንጭፉን አነገተ፤ጠጠር በኮሮጆውጨመረ። በግ ጠባቂው ዳዊት ራሱን ሆነ። የሚያውቀውንና የተለማመደውንወንጭፍና ኮሮጆ አንግቶ ጎልያድን ገጠመ።አሸነፈም።”
ደሬ እንዳላቸው አቶ ሃይሌ ከመለስ ካባ እና ሰይፍ ይልቅ የራሳቸውን ወንጭፍ ይዘው ከፊታቸው የሚጠብቋቸውን በርካታ ጎልያዶች ቢሞክሯቸው ይሻላል።
አቶ ኃይለማሪያም ከፊት ለፊታቸው ብዙ ጎልያዶች አሉ። እርሳቸው እና ፓርቲያቸው እንደሚለው ድህነት አንዱ ጎልያድ ነው። የፍትህ ማጣት እንዴት ያለ ጎልያድ እንደሆነ ለማወቅ አንድ ጊዜ ቃሊቲ ወይም ቂሊጦ ኧረ ምን ሩቅ አስኬዳቸው እዝችው ማዕከላዊ ሄድ ብለው ማየት ይበቃቸዋል። ዛሬ በሀገራችን የማንበብ እና የመፃፍ ነፃነት በህገ መንግስቱ ላይ ብቻ ነው ያለው። ይሄም ትልቅ ጎልያድ ነው። መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለው የህገ መንግስት ቃል መከበሩን ለማረጋገጥም ወንጭፋቸውን ማሰናዳት አለባቸው። ሙስናም ቢሆን ዋዛ የሚባል ጎልያድ አይደለም።
ዘርዝረን የማንጨርሳቸው በርካታ ጎልያዶች አሉብን እነዚህን ለመፋለም የአቅማቸውን ወንጭፍ ካላዘጋጁ በስተቀር የአቶ መለስን ካባ ለብሰው በአቶ መለስ ሰይፍ ተፋልመው አይችሉትም። ራስዎን መሆን አለብዎ… “ራስን መሆን” የሚል መፅሀፍ ፒያሳ ወይም አራት ሎ አካባቢ አይጠፋም። ከጠፋ ከጠፋ ብሄራዊ እነ ጃፋር ዘንድ መጠየቅ ነው። እንጂ፤ መለስን ለመሆን መሞከር አያዋጣም። እኛም እንጠይቃለን… “እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ማነው ኃይለማሪያም አይደለምን!?”

No comments:

Post a Comment