Translate

Sunday, September 16, 2012

ተሸናፊው ሶፊያን አህመድ ነበር


by tesfaye g/abe
 የኢህአዴግ ምክርቤት ጉባኤ ተጠናቆአል። ምክርቤቱ ሃይለማርያምና ደመቀን ዋና እና ምክትል አድርጎ መርጦአል። በዚህ ምርጫ አነጋጋሪ የሆነው፣ ከምርጫው በፊት፣ “ታጋይ የነበረ ለምርጫ አይቀርብም” በሚል ማሳሰቢያ ከበረሃ የገቡ ታጋዮች ሁሉ ራሳቸውን ከምርጫ ማግለላቸው አንዱ ነበር።  በጥቆማው ወቅት ከህወሃት እጩ ሆኖ ለውድድር የቀረበ አለመኖሩ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው። ሶስት ሰዎች ተጠቆሙና ሁለቱ ተመረጡ።
ሶስተኛው ተወዳዳሪ ሶፊያን አህመድ ነበር። ሶፊያን አህመድን የጠቆመችው አዜብ ነበረች። እንዲመረጥላትም አስቸግራ ነበር። ችላ ሲሏት ተወችው። በረከት ስምኦን መግለጫ ሲሰጥ የሶፊያን አህመድን ስም ለምን መጥራት እንዳልፈለገ ግን አልገባኝም።“ሶስተኛውን ተወዳዳሪ ስም መጥቀስ አያስፈልግም” ሲል ዘለለው።መቼም እነዚህ ሰዎች ምስጢር ሲወዱ ጉድ ነው። እነሱ ቢደብቁት እኛ ምን ስራ አለን? እንገሸልጠዋለን። የእኛ የጋዜጠኞች ጆሮ እንኳን ሰምቶ፣ ሳይሰማም ቀዥቃዣ ነው። የሆነው ሆኖ፣ “ከበረሃ የመጡት ታጋይ ባለስልጣናት ከእንግዲህ ወደስልጣን አይመለሱም” ተብሎአል። እያማከሩ ቆይተው በዚያው ወደ ጡረታ ይሸኛሉ። ይህ ዜና መቼም “እፎይ” አሰኝቶኛል። እንዲህ ማሰብ መጀመራቸው ራሱ አንድ ፀጋ ነው። ህይወት ከንቱ መሆኗን ከመለስ ህይወት ተምረዋል። እንዲህ እንደጀመሩት፣ በነካ እጃቸው እስረኛ ቢፈቱ፣ በአካባቢያችን ላይም ሰላም እንዲሰፍን አንዳንድ እርምጃ ቢወስዱ፣ ነፍሳቸው ገነት ትገባለች።ከትናንቱ ምርጫ ጋር በተያያዘ መልከ ብዙ አስተያየቶች እየጎረፉ ነው። የህወሃት ሰዎች አካባቢ መደናገጥ ይታያል። በአንፃሩ በተቃዋሚዎች በኩል ግራ መጋባት ሰፍኖአል። “የምር ህወሃት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አካባቢ ተሰናበተ?” ገና ግልፅ አይደለም። “በጎ ምክር ለጓዶች” በሚል ርእስ ባቀረብኩት ፅሁፍ ላይ፣ (tgindex) ስዩም መስፍን አማካሪ ሆኖ ሃይለማርያምን እንዲመራ አሳብ አቅርቤ ነበር። ያደርጉታል ብዬ እገምታለሁ።በርግጥ ስዩም መስፍን ታሞአል። ቢሾሙትም በርትቶ ሊሰራ አይችልም። ስዩም ጤና የለውም። በጣም ታሞአል። ለነገሩ ማን ያልታመመ አለ? ስኳሩ፣ ደምግፊቱ፣ ሪህ፣ እንትን፣ ስምአይጠሬ፣ ኩላሊት፣ ጉበት፣ ልብ፣ ሳምባ፣ ካንሰር፣ ወፈፌነት፣ ምኑ ቅጡ… የኢህአዴግ አመራር ውስጥ የሚሰማው የበሽታ አይነት ሲመዘን፣ ሁሉንም የበሽታ ተዋፅኦ የጠበቀ ይመስላል። መቀለዴ አይደለም። በበሽታ ምን ይቀለዳል? 40 አመት ያለፈው አበሻ አንድ በሽታ አያጣውም። እኔ ራሴ ቮድካ ስቀምስ ልቤን ይከዳኝ ጀምሮአል።የሆነው ሆኖ “የህወሃት ዘመን አበቃለት” የሚሉ ወሬዎች አሉ። መቸኮል እንኳ አያስፈልግም። “ህወሃቶች ከጀርባ ሆነው አገር መምራታቸው አይቀርም” የሚሉትንም ማድመጥ ያስፈልጋል። ሁኔታዎች የተደበላለቁ ቢመስሉም በአንድ ነገር ግን መግባባት ይቻላል። የህወሃት ሰዎች አማራጭ ስላጡ ባልጠበቁት ፍጥነት ከቤተመንግስቱ ተገፍትረው ወጥተዋል። ተስፋ የሚያደርጉት ደህንነት እና መከላከያን በመያዛቸው ነው። ይሄ ግን ከንግዲህ አያስኬድም። ሃይለማርያምን እንዲዋሽ ማስገደድ ያስቸግራቸዋል። ሰውየው ጥብቅ ሃይማኖተኛ እንደመሆኑ፣ መግደልና መዋሸት ውስጥ ለመግባት ይቸገራል። ደህንነቱ ሰው ቢገድል የሚጠየቀው ሃይለማርያም እንደመሆኑ፣ ስራውን መልቀቅ ወይም ስለተፈፀመው ድርጊት ማብራራት ይኖርበታል። በመሆኑም ህወሃት ደህንነቱን ስለያዘ ሃገሪቱን ሙሉ በሙሉ ያሽከረክራል ማለት ላይሆን ይችላል። እና መቸኮል አይገባም። ነገም ሌላ ሰንበት አለ።የሃይለማርያም ሹመት በፓርላማ ከፀደቀ በሁዋላ፣ የራሱን አዲስ ካቢኔ እንደሚመሰርት ይጠበቃል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለኦህዴድ የታሰበ ቢሆንም፣ የህወሃት ሰዎች “ብርሃነ ገብረክርስቶስ መሆን አለበት” ሲሉ ቸክለዋል። ወርሃ ጥቅምት ላይ የሚሆነውን እናያለን። በአዲሱ ካቢኔ ደህንነት እና መከላከያ ያለምንም ጥያቄ በህወሃት እጅ የሚቆዩ ሲሆን፣ የሌሎች የሚኒስትር መስሪያ ቤት ስልጣናት እጣ ፈንታ ገና አልታወቀም።አዲስ አበቤ መቸም ቀልድ ይወዳል።ማምሻውን ቢራ ላይ  ቀልዶች ፈልተው ነበር አሉ። ከተፈጠሩት ቀልዶች አንዱ፣ “የህወሃት ሰዎች መለስን ከላይ አስቀምጠናል በሚል እምነት፣ ገንዘብ ሲያሳድዱ ተተኪ ባለማዘጋጀታቸው ስልጣኑ ከእጃቸው አመለጠ።” የሚለው ፉገራ አንዱ ነው።የህወሃት ሰዎች በበኩላቸው፣ “የዚህ ሁሉ ተንኮል ጠንሳሽ በረከት ስምኦን ነው” በሚል ጥርስ ነክሰውበታል። ይሄ ሰውዬ ምን ይሻለዋል? ጠላቱ በዛ። ጀግና ነው ግን። ታንክ የመሰለ ግንባሩን ደቅኖ ሁሉን ተቋቁሞ እዚህ ደርሶአል። በረከት – የስምኦን ልጅ።መለስና ጳጳሱ የተቃጠሩ ይመስል ተከታትለው ሄደው፣ ባልተጠበቀ ፍጥነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የኢህአዴግ ከፍተኛ ስልጣናት ከህወሃት እጅ መሹለካቸውን፣ “የእግዚአብሄር ተአምር” በሚል የሚገልፁም ተደምጠዋል። የፈረደበት እግዚአብሄር ያለፍላጎቱና ያለግብሩ ፖለቲካ ውስጥ እየተነከረ መከራውን ያያል። እግዜር ይርዳው!

No comments:

Post a Comment