Translate

Sunday, September 30, 2012

የጠመጠመ ሁሉ አይቀድስ፣ የጮኸ ሁሉ አይነክስ!


የኢትዮጵያዊነት መስተጋብር፣ ከነገድ፣ ከባህል፣ ከእምነትና ከቋንቋ ሳንዱቅ ተመዞ፣ ከጽርሐ አርያም በተለገሰ የጸጋ ልዕልና አብነት አሰተርእዮ የተቃኘ ስለመሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። ሀገርና ሕዝብን በአንድ ጠረፍ አባዝቶና አካቶ፣ በአንድ ዥረት አጣጥቶ፣ ሀረግ ስቦ፣ ሃረግ መዞ <<ሥር ሰዶ፣ ሥር አጋምዶ>> ወግና ልማድን ሾርቦ፣ በማህበረ-ሰባዊ የቁርኝት ሕግ እየተመራ ዘመናትን እየናደ እዚህ ስለመድረሱ ዋቢ መጥቀስ “ያላዋቂ ሳሚ….” አይነት እሳቤ ይመስለኛል። እንደውም የማንነታችን መገለጫ የሆነውን የስነ-ህልውና ማጀት እያተባ በህብረ-ሱታፌ እያገመ፣ ሁለንተናዊ ባህሪይ የተካነ አወንታዊ አትሮን ለመሆን በቃ እንጅ። ይህ ቁርኝት ማህበራዊና ኢኮኖሚአዊ ቅርፅ ይዞ አንደ ሰርዶ ባራቱ ማእዘን እየተንሰራፋ << የዘርና የጎሳን ካብ ንዶ፣ ሠላምና መቻቻልን አጋምዶ >> የልዩነት አግማስን አየሰነጠቀ፣ በእኛነት ያኖረን ፅኑ ማህበራዊ መሠረት መሆኑ ከቶ አይካድም።  እንዲያም ሲባል << የማንነታችን መባቻ፣ የህልውናችን ማቋቻ፣ ጥንተ-ሥሪት፣ ዝክረ-ምሪት፣ የሀበሻ ዘር ነዶ፣ የኢትዮጵያዊነት ህብረ-ተጋምዶ >> ጭምር ነው ማለት ይቻላል። ዛሬ፣ ዛሬ ድንበር እያበጀንለት ያለውን የዘር ድር ቁጢት ቋጠሮ፣ በዓይነ ህሊና ላፍታ የሗሊት ተጉዘን፣ ቅድመ ሆነ ድህረ ዓለም ብንፈትሽ፣ የማይነትብ << ተወራራሽ ሽል፣ ተደራሽ መድብል >> በመሆን፣ የአብሮነታችን ድጓ፣ የማንነታችን ጸጋ፣ << ነባር ቅርስ፣ እሴተ-ውርስ >> ያለን ሕዝቦች እንደሆንን ደግሞ ደጋግሞ ያረጋግጥልናል።

ስለሆነም ዛሬ አፋችንን ሞልተን፣ ኢትዮጵያዊነት ስንል፣ << የዘርን ሐረግ ስር በጥሶ፣ ሄይዋንን ካዳም ለውሶ፣ ስጋና ደም አልብሶ፣ ከዚህም ከዚያም ዘር አጣቅሶ፣ አፈር ልሶ ነፍስ አወራርሶ>> የተገነባ ነባራዊና ጭብጥ የሥርዓተ-ህዝብ፣ አኗኗር፣ ውህደት፣ ትስስርና እድገት ውርስ ውጤት ማውራታችን እንጅ፣ እንደው ለአፍ ወለምታ ያህል ነገር መጎሰም አምሮን አይደለም። ስለሆነም፣ ይኸም ሲባል አበው ሥሪት ግማደ ታሪካችን፣ በሰማያዊ እስትንፋስ፣ መለኮታዊ ሥሪት፣  አምሳያ አብቅሎ፣ ጸሊም ዘጸአዳ አዳቅሎ፣ ዘር ጎንቁሎ፣ ሥፍራ ደልድሎ፣ ሥርዓት አማክሎ፣ የማህበረ-ሰብን ሕግ ደልድሎ፣ በአውደ-ቅኝቱ የታሪክ መድብል እየ” ቋጠረ ያለማሰለስ እስከ ዛሬ ድረስ ያዘለቀን ጽኑ ማህበራዊ መሠረት መሆኑ ነው። ዛሬም ቢሆን ያለስጋት የሚያራምድ፣ የሚያሳርስ፣ የሚያስነግድ፣ ጥላቻን በፍቅር የሚያበርድ፣ ዝንተ ዓለም መፍቀሬ ኩሉ-ሰብ እሴታችን በመሆኑ ጭምር ነው። በሌላ አገላለጽ ይኸው ሀቅ በአንድ ወቅት በእቴጌ ጣይቱ አንደበት እንዲህ በተዋበ ቃል ተገልጾ ነበር። “ ኢትዮጵያ ማለት፦ አንደኛ፡ ክብርህ ናት! ሁለተኛ፡ እናትህ ናት !ሦሥተኛ፡ ሚስትህ ናት፣ አራተኛ፡ ልጅህ ናት! አምሥተኛ፡ መቃብርህ ናት! “
ይሁን እንጅ፣ ትውልድ እንደ ጅረት ውሃ ከአንድ ምእራፍ ወደሌላው ያለማቃረጥ እየፈሰሰ፣ የዘመናትን ህዳግ እየገሰሰ፣ በሥርዓተ-ሱታፌ እፁብ፣ ድንቅ፣ የተባለላቸውን ማህበራዊ ትውፊቶችና እሴቶችን በአብሮነታችን የመስተጋብር ገድል እያተባ፣ በመፈቃቀድ መስተፃምር ሥርዓታዊ ኩነቶች በሚፈጥሩት ስውር ሓይላት እየታገዘ ለዘመናት ቀደምት ትውልዳችንን ወደፊት ሲያወነጭፍ ኖሯል። በዚህ ታሪካዊ ጉዞ፣ ጣልቃ ገብ የሆኑ <<ልብን የሚተናነቁ፣ ወገብን የሚሰብቁ>> መሰናክሎች እንዲያም ሲል ጸያፍ ተግዳሮቶች አልተከሰቱበትም ለማለት ግን አይዳዳኝም። “የመከራ ለሊት እረዥም ነው “እንዲሉ፣ ሰውን ሰው እየገፋው፣ የክብር መንበሩን እየነሳው፣  <<ባንዱ ጫንቃ ሌላው ሲወደስ፣ ባንዱ ላንቃ የሌላው ክብሩ ሲገሰስ >> ተኑሯል። ያም ቢሆን ከማህበረ-ሰቡ ድጋፍ የተቸረው ከቶ አልነበረም።
እንደውም የእምነትና የባህሉ መስተጋብር አሀዳዊዉን የስነ-ህይወትም ሆነ ስነ-ምድር ምህዳር ቁርኝት ሽምቃቅ ይበልጥ ሲያጠብቀው እንጅ በአንጻሩ ሲያላላው የተስተዋለበት ጊዜ ከቶ የለም። ይበልጡንም ቢሆን ኢትዮጵያዊነት ስነ-ዜጋ ደጉሶ አያሌ ምዕተ ዓመታትን እያሻገረ ዛሬ ድረስ እነሆኝ አዝልቆናል። በማንኛውም ጊዜና ወቅት፣ በየትኛወም ሁኔታ፣ ከዚህ የአብሮነት መድብል ጭብጥ አፈንግጦ የወጣ የማህብረ-ሰብ አንጓ <<ጎራ ሲዘል፣ ስር ሲነቅል>> አልተስተዋለም። <<ፈር ቀዶ፣ ገደብ ንዶ>> የተጓዘ አለ ከተባለም ደግሞ እነሆ <<ውርደቷን እንደ ኩራቷ>> ከምትቆጥረው ግብዟ ኤርትራና አቀንቃኟ ወያኔ በስተቀር ሌላ አለ ማለት አይቻልም። የኤርትራ ትንግርታዊ ድራማም ቢሆን የተቋጨው “የዶሮ ቆለጥ በሆድ ይቀመጥ “ አይነት ትውስታ ጥሎብን ብቻ ነው።
እርግጥ ነው አንዳንድ መናፍቃን ለድርሰታቸው ትባት ይረዳቸው ዘንድ፣ በህብረ-ተሰቡ ልብ ውስጥ ለዘመናት፣ የተገነባውንና ዛሬም ቢሆን በጽናት ሁሉን እንደባህሪው አካቶና አቆራኝቶ ያኖረውን የመፈቃቀድና የመፈላለግ እውነታን ድሰው፣ የመፋለሚያ ጎራ ሲያደርጉት ይስተዋላል። ለወንበር መደራደሪያ፣ ይበጃቸው ዘንድ በየመድረኩ ስንኝ እየቋጠሩ በቀደምት አብሮነነታችንና ኢትዮጵያዊነታችን ላይ ያነጣጠረ ብርቱ ተግዳሮት ደቅነውብን ይታያል። በዚህ ረገድ ወያኔን ጨምሮ ሌሎች ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሀገር ለመናድ በሚያደርጉት ርብርቦሽ፣ ከወየበው የታሪክ ኩራታችን ፈልቅቀው ሊያወጡን እየታገሉን ያሉ ስለመሆናቸው አሌ የማይባል ሀቅ ብቻ ሳይሆን፣ እለት፣ ተለት በገሀድ የሚገዳደረን ዛሬም በአንድነታችን ላይ የመቅሰፍት ጥላወን ያጠላ የታሪክ ሸለፈት ነው።
<< ከማህሌት ዜማ፣ ቅኔ ዘርፎ፣ ከሶላት ፋቲሐ ኢማን ሸርፎ >> እድል የተነፈገውን የሀገር ልጅ እጣፈንታ በጋራ ለማስመር የተደረገውን ብርቱ ጥረት የመኖሩን ያህል፣ ለፍትህና ለመብት ሲደረግ የነበረው  የተጋድሎ መቅድም በየዘመናቱ እንደ “አንበር” በጨካኝ መሪዎች ሲዋጥ መኖሩ ይታወቃል። ይኸው ማብቂያ የሌለው ተግዳሮት እስከዛሬ ድረስ እልባት ያላገኘ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ፣ ሀገራችንን ለዘመናት ሲንጣት የኖረ የፖለቲካ አዙሪት (አባዜ) ያለከልካይ እስከ ዛሬ ድረስ ለመዝለቅ በቅቷል። ምንም እንኳ << እግዚኦ…. ለፈጣሪ ኩሉ !>> ባንዱ ጎራ << አዛንና ዱአ! >> በሌላኛው ጎራ፣ እንደዬ” በዓታቸው ለፈጣሪ ምልጃ በማድረስ ቢተጉም ድካማቸው <<ሰሚ ያጣ ጩኸት፣ ጥርስ ያወጣ ግጠት>> አይነት ሆኖ የመቅረቱ ጉዳይ የሁላችንም የመንፈስ ቁስል ነው።
ዝክረ-ታሪካችን በራሱ ምህዋር በሾረባቸው ቀደምት ዓመታትና ሁሉ፣ የትውልድን ጅረት ፍሰት አዲስ አቅጣጫ ለማስያዝ የተደረገው ብርቱ ተጋድሎ በሰመረ መልኩ ሊከናወን አለመቻሉ በራሱ፣ << ተዘርቶ ያላፈራ ሰብል፣ ተቆልቶ ያልገበረ ቀሊል፣ >> ሆኖ መቆየቱን ያመለክታል። ይህ ጉዳይ ዛሬም ድረስ፣ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። የብዙሀኑን እጣፈንታ ለመወሰን በተደረጉት እነዛ የማለዳ የፍትህና የአርነት ተጋድሎዎችም ይሁን፣ አሁን  ባለው የመረረ፣ የመብትና ነፃነት፣ ጥያቄ ላይ ጥላውን እንዳጠላም ይኖራል። ይህ ወርደ ጠባብ የፖለቲካ ሰርጥ በራሱ አቃቤ ርዕስ እየተከፈነ፣ በሁሉም ዘንድ የማይደፈርና የማይገሰስ የተቃርኖ መድብል ሆኖ የመኖሩን ያህል፣ በነፃነት ናፋቂው ጎራ፣ ለዓመታት ቅጥሩን ደርምሶ ወደፊት መራመድ ያልተቻለበት ጉዳይ በውል ተጢኗል ለማለት አያስደፍረኝም። ምክንያቱም ትግሉ እያደር ውሉ እንደጠፋበት ልቃቂት እየተወሳሰበ ሲሄድና ከርዝማኔው አንፃር፣ ወቅታዊና ነባራዊ ጭብብጡን በመቃኘት ማርከሻ መፍትሄ ለመተለም የተቻለ አይመስለኝም። እየተሠራ ያለውን የኑባሬ ሊቃውንት አብዮታዊ አስተርዕዮ ቅኝትም ቢሆን በውል ሲጤን በአመዛኙ “ ሞኝን እባብ ሁለት ጊዜ ይነድፈዋል፣ መጀመሪያ ሳያየው፣ ሁለተኛ የነደፈኝ እባብ ይዐኸ ነው ብሎ ለሌሎች ሲያሳይ” የሚለው ሀገረ-ሰብ ብሂል በውል ያልተጤነ መሆኑን በውል ያረጋግጥልናል።
ምንም እንኳ << ጥንተ-ነገር፣ ጥንተ ሀገር >> ማለት ለዚህ ዘመን ትውልድ በአመዛኙ << የጥርስ ማፋጫ፣ የጉረሮ ማስለጫ >> ሆኖ ቢታይም፣ ከኢትዮጵያዊነት ማዶ እየጠወለገ ያለው የአብሮነት ዛፍ ቅርንጫፎቹ በምንገደኞች እየተገነጠሉ ሲማገዱ ማየት የእለት ተእለት ተግባራችን ከሆነ እነሆ ውሎ አድሯል። በዚህ አጋጣሚ << በጥላው ሸሽጎ ያኖረን፣ በስሩ አጋምዶ ያሰረን፣ የህልውናችን ወጋግራ፣ የስብእናችን አዝመራ >> የሆነው ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ስለመሆናቸው የሚጠራጠር ትውልድ ለማየትም በቅተኛል።  የአብሮነት መልህቅ የሆነው << ኢትዮጵያዊነት >> ብሔራዊ ርእስ ሆኖ << ውሀ አያጣጡ፣ ስኒ አያማጠጡ >> እስከዛሬ ያቆዩን እነዛ ብርቅዬና ድንቅዬ፣ በማለዳ፣ በቅድመ በአባቶቻችን የተገነቡት የጋራ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶቻችን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዙ፣ እንደ አሮጌ ቅጥር እያዘመሙ፣ እንደ ከብት ቀንድ መንታ ምንቆሪያ እየተበጀላቸው እንዲወጉን የመደረጋቸው ምስጢር ዋቢ መጥቀስ አያሻኝም። ምክንያቱም፣ የዚህ ክስተት አስከፊ ገፅታ እለት፣ ተእለት እየገዘፈ መጥቶ እነሆኝ በብሄረ-ሰብ ሽፋን የከፋ አደጋ በሀገርና በሕዝብ ላይ ለመደቀን ችሏል።
<<ትላንትን ለዛሬ ባለእዳ፣ ነገንም በራሱ የምኞት ተራዳ>> ማድረግ የለብንም። በተውሶ ማንነት፣ የታሪክ እራፊ ከማውለብለባችንም በፊት፣ ዛሬን በዛሬነቱ <<የከረመ ቁጢት መቋጫ፣ የጥላቻን ማጀት መሟጠጫ፣ የምኞት ምናብ መሰልቀጫ>> ልናደርገው በተገባ ነበር። የሰው ልጅ ትልቁና አብይ የስብእናው ሚሥጢር፣ የህሊና ሚዛን መጠበቅ መቻሉ ነው። ያን በማድረጉ ረገድ ፈር ለቆ በሌጣው የሚጋልበውን መረን የወጣ የተስፈኞች ምኞት ገርቶ፣ ስለ ዛረው ብቻ ሳይሆን፣ የሁላችንንም መጻኢ እጣፈንታ ስለሚወስነው፣ ስለ ጭብጥ እውነታ <<የዘመናትን ህዳግ ዳሶ፣ የትውልዱን የፍትህና የእኩልነት ማህቶት ደርሶ>> ለሁሉም የሚበጅ አይነተኛ እልባት መስጠት ሀገራዊ ግዴታ፣ ታሪካዊ ሀላፊነትም ጭምር በሆነ ነበር።
የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት ስናስተውል ደግሞ፣ ዙሪያገባውን በቃላት ንዳድ እየታመሰ << ብስል ከቀሊል፣ ዳሩን ከመሀል፣ ግርዱን ከሰብል፣ >> መለየት አልተቻለም። ሐሰት << በነውጥ የተሞላች ብቻ ሳትሆን፣ ያለመሆን ፉጨት ጭምር ነች >>። ከዚህም የተነሳ በየ”ሥፍራው ደምቃ፣ ሞቃ በአጀብ ስትጓዝ ትስተዋላለች። ህልውናዋም በትላዋ ላይ የተሳለ ነው። እውነት ግን ስለ ህያው ነገር ከጥቂት ሀቀኛች ጋር ተቆራምዳ፣ እንደ ደረቀ ጭራሮ ከታሪክ ጠረፍ ዳር መንና፣ እጇን ለወዳጆቿ እንደዘረጋች ደርቃ ትኖራለች እንጅ ከቶ አትጠፋም። አንድ ሕብረተ-ሰብ ታሪካዊ እውነትን የመቀበልና የመከተል አቅሙ በዳበረ መጠን፣ የማንነቱና የምንነቱ መሥፈርት በዛውል ልክ ይደረጃል። የአብሮነት፣ የእኩልነት፣ የመከባበርና የመቻቻል ጥበብና ቀዳማይ እሴቱ ጭምር ከዚህ እየፈለቀ የሚቀዳ የጋራ መቅድም ድጉስ ነው የሚሆነው። በሌላ አንፃር <<የልዩነት ዋግምት፣ የሰላም ፈውስ፣ የእኛነት ማህደር>> ነው ማለት ነው።
ያም ሆነ ይህ፣ <<በገፈራ ግርግም ውሽጥ ውሻ የሚተኛው ገለባ ስለሚበላ ሳይሆን ሌሎች እንስሳት እንዳይበሉ በመመቅኘት ነው>> ኢትዮጵያም እንዲሁ ጥቅሟን ለማስከበር በየታሪኩ ምናብ መዳረሻ ባደረገቻቸው ሁለገብ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በውጭና በውስጥ አጥፊ ሃይላት ስትታመስ ኖራለች። ይ                ኸውም፣ በወቅቱ በውል በተጠና መንገድ እልባት ስላልተበጀለት፣ እነሆ ዛሬ እንደሰርዶ ሥር ሰዶ፣ አጎንቁሎ፣ ዛሬ የለየለት የፖለቲካ ሾተላይ በመሆን በሀገርና ህዝብ ላይ እያሰከተለ ያለው ጥፋት በቀላል የሚገመት አይደለም። ዛሬ ጉልበት አውጥቶ፣ አይኑን አፍጥጦ፣ ጥርሱን አግጦ ሊቧጥጠን ይስተዋላል። ይበልጥም እንደ ቁስል ነባር እዥ ሆኖ እያመረቀዘ የአንድነት፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የእኩልነት ተውሳክ በመሆን፣ የመንፈስ ነጋዴዎች መደራደሪያ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል። ከሁሉም በላይ ሊያሳስበን የሚገባው የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት ሆኖ እየገረፈን ያለ ያላሰብነውን እንድናስብ፣ ያልፈልግነውን እንድናደርግ፣ የማንመኘውን እንድናልም እያደረገን አለ ድውይ አመለካከት ነው።
ጎጠኝነት እንዲህ እንደዛሬው ቀንድ አውጥቶ በይፋ ሳይወጋን፣ ውስጥ ውስጡን እንደፍልፈል እየቆፈረ፣ ህሊናችንን የተፈታተነ፣ <ነፍሳችን ያስገበረ፣ ልባችንን ያሸበረ፣ ወኔያችንን ያዳወረ>> የብሶት ካንሰር እንደ ሆነ ማንም አይዘነጋውም። ጥንትም ሆነ ዛሬ <<ራሱን የማይችል አንገት>> አለ ብሎ መገመት ሞኝነት ነው። እንዲህ አይነት አይነበሲር አስተሳሰብ በራሱ የማይተማመን፣ ትውልዱን የሚያኮሰስ፣ የፍልስፍና ድህነት ማቀንቀን ነው የሚሆነው። ይኸውም በራሱ ምህዋር እየጦዘ፣ ውሎ አድሮ እራሱን በራሱ ጠልፎ የሚጥል አዙሪት የተቃኘ የድኩማን እሳቤ ከመሆን አይዘልም። ያም ቢሆን ጥሎት የሚሄደው ጠባሳ ቀላል ግምት ሊሰጠው አይገባም። ወትሮም ቢሆን “ ጸሐይና ምራት ፊት ያበላሻል “ እንደሚሉት ያለ ማለት ነው።
“የላሜ ቦራ” አይነቱ የኑፋቄ እስትንፋስ፣ ያሳየን ነገር ቢኖር፣ ታሪክን እንደ በረሀ ወተት በመንታ ዛፍ አንጠልጠሎ ከመናጥ ያለፈ፣ ነባራዊውን ሀቅ ተራምዶ አንዳች ነገር መፈየድ አለመቻሉን ነው። አንዳንዶቻችን << ህዝብን እንደ ሥልጣን ምህዋር፣ ሀገርንም እንደ ታሪክ መዘውር፣ የጋራ እሴቶቻችንንም እንደ ህልውናችን አውታር >> ማየትና መቀበል ለምን እንደሚተናነቀን አይገባኝም። ይህ እኛ ያመጣነው ወይም የፈጠርነው ሳይሆን፣ አባቶች በአብሮነታቸው በብዙ መውጣትና መውረድ <<በመቻቻላቸው ልማድ፣ በፍቅራቸው ማእድ፣ በእምነታቸው አእማድ፣ በመፈቃቀዳቸው ውሁድ>> ያወረሱን በረከትና ፀጋ እንጅ፣ ዛሬ በየ” አረዳው ሸንጎ እንደሚ” ፖተለከው፣ ለራስ ተመጥኖ በተሠፋ ሱሪ እንዲሁም የዓይን ቅድ ልኬት የሌላው ምናብ በመዳሰስ የተቸርነው ግንጥል ጌጥ አይደለም።
“እንኳን ዋሽተን በእውነትም እየጮህን እውር ነው የምንወልደው አለች ውሻ “እንዲሉ፣ እየ” ተስለመለመች ላለች እውነት የደም ደብዳቤ እያረቀቁ በቀቢፀ-ተስፋ የመንፈስ እንጉርጉሮ በማዜም፣ የትውልዱን የስሜት ህዋሳት በጎሳ ፖለቲካ መጨፍለቁ፣ ለሀገርም ለወገንም የሚበጅ ጉዳይ አለመሆኑ ከቶ የሚጠፋው ይኖራል ብየ አልታክትም። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከዚህ የከፋ <<ታሪካዊ ዝቅጠት፣ ህሊናዊ ንቅዘት>> ከቶ ሊኖርም አይችልም። ይሁን እንጅ አሁን እኛ በእውነተኛ ጎዳና ላይ ዛሬም፣ ነገም መራመድ እስከቻልን ድረስ፣ ስለ” ጉዞአችን ለሌሎች ለማስረዳት ረዥም ጊዜና ሃይል በከንቱ ማባከን የሚያስፈልገበት ጊዜ አይመስለኝም። “በሮቹን ንዳቸው አባራው ይነሳ፣…..ይከተል የለም ወይ ኮርማው እያገሳ “የሚለው የሀገሬ ገበሬ ቅኝቱ ዛሬ ቢሆን አልተለወጠም።
አላማችን ከማንነታችን በእጅጉ የላቀ ሊሆን ይገባል። ውድቀታችንም ይሁን ስኬቶቻችን ከብቃታችን በላይ  እንዳልሆኑ ሁሉ የመጀመሪያው እርምጃችንም በበኩሉ የጉዟችንን የወደፊት አቅጣጫ የሚወስን ይሆናል። ማድረግ ለውጤት ሲያበቃን፣ ለመሆን መጣር ደግሞ በራሱ ጊዜ መሆንን እንደሚያስከትል አሙን ነው። ችግሮቻችንን ለመፍታት የምናደርገው ጥረት ሁሉ በራሳቸው መድብል ፈጥረው፣ ተግዳሮቶቻችን በእኛ ላይ በተቃርኖ እያደረሱ ካሉት ጉዳት ይልቅ በእጅጉ የሚጠቅመን ነገር ሊያፈልቁ እንደሚችሉ ማሰብም  አስፈላጊ ይመስለኛል። “ውጤት ያለጥረት፣ ድል ያለመስዋዕትነት “አይገኝም ሲባልም ዝምብሎ አልነበረም።
በቀለጠው መንደር ማን በፀጥታ ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል? ይህ ወቅት ሁሉም መሰል ወገኑን አቧድኖ ጎራ ለይቶ በቃላት ቡጢ ሲናረት ውሎ የሚያድርበት፣ አለያም በፖለቲካ አዙሪት ናላቸውን እያጦዙ፣ በምኞት ሲሽቀዳደም የሚታዩበት፣ የለበጣና የሸፍጥ ሜዳ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል። ፖለቲከኞቹ ዱርቤቴ ያሉ እስኪመስላቸው ድረስ፣ ቤዬ” ቅጥሩ፣ እለት ተለት፣ ለሚፈለፈሉት የፖለቲካ ድርጅት ሰንበቴ፣ የክርስትና ስም እየሰየሙ በማስጨብጨብ በእጅጉ <<ትግሉን እየጎዳ፣ ህብረትን እያናጋ>> ያለ ምግባር ነው። ይህም <<የመደማመጥና የመቻቻልን ባህልን ያመከነ፣ የፖለቲካ ዋልጌነት ያሰፈነ፣ እኔነትን ያገነነ>> የፍልስፍና ድህነት ነው ማለት ይቻላል።  “ሰካራሙ ፖስታ” ይሏል ይኸ ነው። ከዚህ ባሻገር፣ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ቁምነገር ሲሠሩ <<ተስፋን አምጠው ሲወልዱ፣ ድልን አቅፎ ሲያለምዱ>>  አላስተዋልንም። በእንዲህ አይነቱ የፖለቲካ አዙሪት ሽምቃቅ ውስጥ ገብተው በሌጣው የሚጋልቡ ድርጅቶች እንኳን ወደፊት ሊራመዱ፣ ከተነሱበት ስፍራ እንኳ በወጉ ተመልው ስለመድረሳቸው እርግጠኛ መሆን አንችልም። ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎች ሩጫቸው ሁሉ በመንገድ ዋሎ እንደቀረ የታዘብነው ሀቅ ስለሆነ ጭምር ነው። “ የት” ይደርሳል ያሉት ጥጃ፣ ልካንዳ ቤት በራፍ ተገኘ “ እንዲሉ። በቀደሙት ጎራ ተርታ ተሰለፉትም ቢሆኑ   <<ወንዙን ከተሻገሩ በሁዋላ ስለምን አግር መጎተት እንዳስፈለጋቸው>> በውል ሊፈትሹት የሚገባ አቢይ ጉዳይ ይመስለኛል። ለአንድ ሀገር አራት አይነት ሰዎች ያስፈልጓታል የሚለው የአበው ፅኑ ምሳሌያዊ ምክር የግድ እስፈላጊያችን እንደሆነ እገነዘባለሁና ነው። ይኸውም “አንድ ቀዳሽ፣ አንድ ነጋሽ፣ አንድ አራሽና አንድ ተኳሽ “ናቸው። ችገገሩ ግን ማን….? “ማን ይሸከም ስልቻ፣ ሁሉ ሆነ ቃልቻ “ ሆኖብናል።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያላሸቀና ሲያጓትነው የኖረው የምሁር ፖለቲካ (Elite politics) ስለመሆኑ ሸንጎ መውጣት አያሻኝም። አቅል በሌለው፣ ያልሰከነ ስሜት፣ ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታዎን በውል ሳይገመግሙ፣ ታክቲክና እስትራቴጂ ሳይነደፍ፣ የሃይል አሰላለፍና ሚዛን ሳይለይ፣ ወዳጅና ጠላትን በውል ተለይቶ ሳይፈረጅ፣ ነባራዊና አንፃራዊ ሁኔታዎች ነጥረው ሳይወጡ፣ በድንግዝግዝ ህዝብን ባልተጠና እና ባልተደራጅ ትግል ማግዶ “ ልብ ያለው ሸተት” አይነት የቁጭበሉ ጨዋታ እንዳለፈው በህዝብ ሕይወት ሊጫወቱ የሚናፍቁ እንዳሉ ይሸተኛል። እነዚህ በምናብ የወይን ስካር << ያልተጨበጠ ድል የሚያውጁ፣ በደረቀ ወንዝ ድልድይ የሚያበጁ >> ናቸው። እንዲህ ያለው ቀቢፀ ተሰፋ አካሄድ በትግሉ ጎራ ከህልፈት ባሻገር፣ ያሳደረው የሞራል ድቀት  እውነተኛው ጥሪ ደርሶ እነሂኝ  << ሳንጃ ካፎቱ፣ ልብ ከግለቱ፣ ጣትም ከቃቱ >> ቢባል እንኳ፣ ከሰመመን እንዳይቀሰቀሱ የህሊና በራቸውን በችንካር ግጥም አርገው ዘግተን በቀዳዳ የሚያጮልቁ፣ በጨለማ የሚተኩሱ፣ << የስነ ልቦና ምርኮኞች >>  ያደረጋቸው ዜጎች ምን” ያህል  እንደሆኑ መገመት አያዳግትም።
እኔ አልሄድም ጅዳ አልሄድም እርቄ፣
አሜን እለዋለሁ እዚሁ ታጥቄ።…..አሰብላቸዋል።
የፖለቲካ ድርጅት የከበረ ነገር (እንቁ) እንደሚፈልግ ነጋዴ ማለት ነው። ጨቋኞች (ግፈኞች) የቀበሩትን ነፃነት የተሰኘ እንቁ የከበረ የህይወት ዋጋ ከፍሎ ይገዛዋል። ይህን በውል ማድረግ መቻል ደግሞ አስተዋይነት ነው። በፖለቲካው ዓለም የደራ ማህበራዊ ሳይንስ ገበያ ቢሆንም፣ መገበያየት የሚቻለው ግን መቻቻልና መደማመጥ ሲኖር ብቻ ነው። ለመግባባት ደግሞ የመደራደሪያ ነጥቦቻችን ባበዛን ቁጥር ይበልጥ ወደ መፍትሄዎች በእጅጉ እየቀረብን እንሄዳለን። አለበለዚያ “ የቁራ ገበያም ” አይነት ነው ሊሆን የሚችለው። በዚህ ሂደት ሊኖር የሚገባው የጫወታ ህግ ሙሉ ልምምድ አድርጎ ሙሉ ጨዋታ መጫወት መቻል ነው። በግማሽ ልምምድ ሙሉ ጫወታ ለመጫወት መሞከር፣ መሸነፍን እያወቁ እንደመጫዎት ማለት ነው። የመጫዎቻው ሜዳ ደግሞ የሰው ልጅ ህይወት፣ እወቀት፣ ተመክሮና በጽናት የተለበጠ ቆራጥነት በመሆኑ ብርቱ ጥንቃቄና ሃላፊነት ያሻዋል። ይህም ስንል ምናባዊ ቅኝት ሳይሆን  << ለማልማት ያልታደሉ፣ ለማጥፋት የተሳሉ >> ሞልተዋልና ነው። ገበሬ ባዝመራ ወቅት ማረስና መዝራት ብቻ ሳይሆን << ቡቃያውን ካራሙቻ፣ ፍሬውን ከግሪሳ ዘመቻ >> የመጠበቅ ሀላፊነትም አለበት። ስለሆነም፣ ድርጅቶች የነፍሰ-በላዎችና ቀራጮች መመሸጊያ እንዳይሆኑም በውል መጠንቀቅ የሚያሻ ይመስለኛል። << እወቁኝ ብሎ ደብቁኝ…. >> እንዳይመጣ ለማለት ያህል ነው። መቸም “ ድሀና ገበያ “ ሳይገኛኙ ይኖራሉ! ይህንንም ለማለት የዳዳኝ፣ እየተመለከትነው ያለው የመጠላለፍና የግርግር ጉዞ የሚያስገነዝበን የራሱ አይነተኛ ሀቅ ከፊታችን ተስሎ ስለምናየው ነው።
የፖለቲካ ድርጅቶች የየራሳቸው ምህዋር ፈጥረው ከመሻኮት ባለፈ፣ በትግሉ ጎራ ዙሪያ ተተኪ ትውልድ በማፍራት ረገድ << ሰንደቅ ላነገበው ዓላማ፣ ነፍጥ ለወደረው ኢላማ >> በማስጨበጥ እረገድ እየተሠራ ያለ ነገር ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ያሁኑ ወጣት በአመዛኙ የደርግ ሥርዓት ትሩፋትና፣ የወያኔ ፕሮፓ ጋንዳንዳ አዙሪት ናላውን ያጦዘው እንደመሆኑ መጠን። << እውነቱን የሚያስጨብጠው፣ ከአዙሪት የሚያስመልጠው >> ፋና ወጊና ብቃት ያለው ድርጅታዊ አመራርና ንቃት ከምንጊዝውም በበለጠ ያስፈልገዋል። በአንጻሩ ግን << ግራ በማጋባት የተካኑ፣ በጥላቻና ጽንፈኝነት የመነኑ >> የወንበር አብዮተኞች፣  በየአደባባዩና በየመጠለያው ወጣቱን ግራ ሲያጋቡት ማየት እለት ተእለት የህሊና ቁስል እየፈጠረብን ያለ ጉዳይ ነው። ትውልዱን ለአደራ ተረካቢነት ለማብቃት ተግቶ በመሥራትና በማነጽ ፈንታ፣ እንደበቅሎ ለጉሞ በዘልማድ ለመጎተትም የሚደረገው ሙከራም ቢሆን  ወጣቱን ይበልጥ “ ትግል እስከወረቀት” በተሰኘ ሰንካላ የስነልቦና ሾተል እያስወጋው አለ አሉታዊ ክንዋኔ ነው።
ታላቁ መጽሐፍ እንደሚያስገነዝበን። “….. አባቶች የላችሁም። ብዙ ሞግዚቶች ግን አሏችሁ….” የሚለው በእኛም እንደደረሰ ማጤን መልካም ይመስለኛል። አንዳንዱ ነገር “ ቢራቢሮ ቂጧን የምትሸፍነው የላት ምድር ታለብሳለች “ አይነት ሲሆን ሌላው ደግሞ “ ከእኛ ወዲያ ፉጨት አፍን ማሞጥሞጥ ነው “ ባይ ነው። በእንዲህ  አይነቱ የወግ አጥባቂዎች ውዥንብር ህልቆ መሳፍርቱ እየተለወስ በአመዛኙ << ከወዳጅነት ይልቅ ለጠላትነት የቀረበ፣ ከመገንባት ይልቅ በማፍረስ የቆረበ >> ሆኖ ይታያል። ይህን  መግታትና አፍራሽ ተልእኮውንም ማምከን የግድ ይላል። ያም ቢሆን አምና በታረሰው ዘንድሮ አይዘራምና አዲስ እዳሪ ለማውጣት፣ << ኮርማውን ከቀንጃ፣ ወላዱን ከጥጃ፣ ካህኑን ከምልጃ፣ ቃዲን ከመስገጃ፣ ሞፈር ከአራሹ ቋንጃ >> ማገናኘት ይጠበቅብናል። እንዲህም ሲባል እንደውትሮው ረዥም እርቀት መጓዝ የሚያስፈልገን ከቶ አይመስለኝም። ከጎናችን ያሉቱኑ ሀገርን በቀል ዛፎች (ልጆች) << የልብ እስትንፋስ ሽታ፣ የህሊናቸውን አውነታ >>  በውል ማድመጥ መቻል ብቻ በራሱ ብዙ ርቀት የመራመድ አህል ይመስለኛል። “ ሆድ ለባሰው……” ይባል የለ።
ጠቢቡ በምክሩ “….. ልጄ ሆይ ይህንንም አድርግ፡ እራስህን አድን ፣ በጎረቤት እጅ ወድቀሀልና፦ ፈጥነህም ጎረቤትህን ነዝንዘው፣ ለአይንህ እንቅልፍን፡ ለሽፋሽፍቶችህ እንጋጉልቻን፡ አትስጥ፣ እንደ ሚደቋ ከአዳኝ፣ እንደ ወፍ ከአጥማጅ እጅ ትድን ዘንድ….” (ምሣሌ፡ 6፦3-5) ይላል። እኛ ግን በውኑ እንደ ሀገር፣ እንደህዝብ፣ እንደዜጋ ይህን ለማድረግ የተቸገርን ስለምን ይሆን…? ሕይወትንስ የምንረዳውም ሆነ የምንመራው ባለን ትክክለኛ የሀሳብና የሕሊና ምሪት አይደለምን? ውጤታማ መሆን እየተቻለ ሳለ፣ ባዶነትስ የሚሰማን ስለምን ነው? ለመኖር ከምናባክነው አያሌ ድካም ይልቅ፣ ለሀገርና ለወገን አርነት ስንል የምንሰዋው ጥቂት ቁም ነገር በውኑ የከበረ አይደለምን?
መጽሀፍ፦” ድሀን የሚገዛ ጨካኝ መስፍን እንደሚያገሳ አንበሳ እንደተራበም ድብ ነው “ ይላል። እንዲህ ከሆነ ዘንዳ << በከንቱ ክርክር ስለምን እርስ በርስ እንፋለማለን፣ በጥላቻስ እስከመቼ፣ እየተገፋፋን እንዘልቃለን ! >> አይኖቻችን ከእንባ ይጠበቁ ዘንድ አይለንምን? ከጠረፍ ጥግ የመነነው ነፃነታችን ከምርኮ አስመልሰን  መንፈሳችን ይጠገን ዘንድ ከስነ-ልቦና ድህነት እረሳችንን መንጥቀን ማውጣት ተገቢ ይመስለኛል። “ ጉድ ሳይሰማ  መስከረም አይጠባም “ እንዲሉ፣ በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ማለቂያ የለሽ ግፍና በደል፣ ባንድ በኩል፣ ታሪክንና ኢትዮጵያዊትን ለማዛባት የሚደረገው ርብርቦሽ በሌላ በኩል፣ ተዳምረው የሀገራችንን የመከራ ገፈት አባብሶታል። ይህን ጣራ ጠቅቶ የሚገኝ ብሄራዊ ተግዳሮት ለማለዘብ ወያኔና ግብረ-በላዎቹ በሚያደርጉት የፕሮፓጋንዳና የስነልቦና ጦርነት፣ የብዙዎች ቀልብ እያማለለ የህሊንን ሚዛናቸውን እያዛባ መምጣቱ ሌላው የትግል አጣብቂኝ ሆኗል። ስለሆነም ወኔአችን ልባችንን ሽቅብ ነድሎት፣ የናላችንን ጣራ ፈንቅሎ በመውጣት <<የሽሽት ገመና ቢቋጭ፣ የግለት ገመና ቢረጭ >> “ ጸብያለሽ በዳቦ” የሚያሰኝ ከቶ ይሆናልን?
አላማችን ከማንነታችን በእጅጉ የላቀ ሊሆን ይገባል። ውድቀታችንም ይሁን ስኬቶቻችን ከብቃታችን በላይ  እንዳልሆኑ ሁሉ የመጀመሪያው እርምጃችንም በበኩሉ የጉዟችንን የወደፊት አቅጣጫ የሚወስን ይሆናል። ማድረግ ለውጤት ሲያበቃን፣ ለመሆን መጣር ደግሞ በራሱ ጊዜ መሆንን እንደሚያስከትል አሙን ነው። ስለሆነም፣ ችግሮቻችንን ለመፍታት የምናደርገው ጥረት ሁሉ በራሳቸው መድብል ፈጥረው፣ ተግዳሮቶቻችን በእኛ ላይ በተቃርኖ እያደረሱ ካሉት ጉዳት ይልቅ በእጅጉ የሚጠቅመንን ነገር ሊፈልቅ እንደሚችል ማሰብም  አስፈላጊ ይመስለኛል። “ ውጤት ያለጥረት፣ ድል ያለመስዋዕትነት “ አይገኝም ሲባልም ዝምብሎ አልነበረም።
የትላንትን ተስካር ለማውጣት ነገን መበደር ያለብን አይመስለኝም። ለነገም የቁም ተስካር ለመደገስ መራወጥ ሀላፊነት የጎደለው የኑፋቄ ሥራ ነው የሚሆነው። የእጃችንን የፖለቲካ ቁጢት ለመበጠስ ያቃተንም ሆንን፣ አዲስ የፖለቲካ መሀረብ ለማውለብለብ የምንማስን አሳዛኝወ ፖለቲከኞች ከመሆን እልፍ ያለ ተግባር ለመከወን አስብቶ ማሰብ ያሻል። በአዲስ እሳቤና ቅኝት፣ ለላቀ ለውጥ የላቀ እርምጃ ማሳየትም ተገቢ ነው እላለሁ። የሰውልጅ መታገስና መቆጣጠር የማይችለው ረሀቡን ሳይሆን ጥጋብን እራሱን ነው። በወያኔም ሠፈር እየተመለከትን ያለነው ነገር ቢኖር ይኸንኑ ጭብጥ ነው። ህዳጣን የፖለቲካ ምነደኞችም እሩጫ የሚቋጨው፣ እጣፈንታቸው የሚወሰነው በዚሁ ቅኝ ነው። ስለዚህም ነው << እንደ ሙሴ በምድረበዳ የሚመራ ትውልዱን አሻግሮ አራሱን ስለ ተሻጋሪው ትውልድ እጣፈንታ ሲል መስዋእት አድርጎ የሚያቀርብ መሪ ድርጅትና ከምንጊዜውም ይልቅ እጅግ አስፈላጊ የሆነው። በመኖር ብቻ ሳይሆን መስዋእት በመሆንም፣ የሽንፈትን ጣራ ነድሎ፣ የድል ፍሬ አብስሎ፣ በሞት ህያው ታሪክ ስሎ ዘለዓለማዊ ሆኖ መኖር ይቻላላ፡፡
ድርቡሾች በጎንደር ዳግም እንዳይደርሱ፣
መተማ ተቀምቷል ዮሐናስ እራሱ።…መባሉ ከቶ፣ ለተረት አይደለም።
የስጋቴ ምንጭ ደግሞ ብቃት ያለውና በውል የተደራጀ መሪ አካል በሌለበት፣ የህዝብ አመጽ << ፈር ለቆ፣ ጦር ሰብቆ >> አደባባይ ቢወጣ ሊታሰብበትና ዝግጅት ሊደረግበት የተገባ አቢይና ወቅታዊ ጉዳይ እንደሆነ ለማስገኝዘብ ጭምር ነው።  እየታየ ያለው የአምሥተኛ ረድፎች << የድል አጥቢጠያ አርበኝነት >> ግስጋሴ ልብ ይሏል። ዛሬም ሌላ << ዳግማዊ ደርግ፣ ዳግማዊ ወያኔ >> ላለማየት ምን ዋስትና አለን….? ሀገርን እርስ በርስ ለማተራመስ እየተደገሰ ላለው የጥፋት ዘመቻ እሽቅድምድምን ለመግታት በሚደረገው መከላከል ዋርድያ ለመቆም ስንቶቻችን በውን ተዘጋጅተናል? ስንቶቻችንስ የወቅቱ የፖለቲካ ውሽንፍር እያመሰን ነው? ምን ያህልስ << የወገንንስ ጭቆና መግቻ፣ ለእንባ ማቋቻ >> እልባት ለመፍጠር ተዘጋጅተናል…? በዚህ ከቀጠልን የዘረኞች ደባ አጎንቁሎ፣ አፍርቶና አሽቶ እንዲያም ሲል ጎምርቶ ሂሳብ የማወራረድ ሥራ እንዳንገባ ፅኑ ፍርሀቴ ነው። << የጠላትን ልቀቱ፣ የወዳጅን ስባቱ >> የሚፈተሸው ከወዲሁ የፖለቲካውን ጅረት መልካ ሳይሻገሩ ይመስለኛል። ወትሮም “ የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል “ የሚባለው ለወግ ያህል አልነበረም።
እኛ ማረፍ የምንችለው አሰቀድመን ልጆቻችንን የሚያሳርፍ ሥራ ስንሠራ ነው። በሸለብታ ድባብ የሚሠራ ስህተት “ ያንድ ቀን መዘዝ ያለ ዘጠኝ ወር አይመዘዝ “ አይነት መሆኑ ነው። ስለዚህ ካለፈው ተመክሮ ወስዶ ብርቱ ጥንቃቄ የተሞላበት ትግል ማካሄድ የግድ ይላል። ነገር በምሣሌ እንዲሉ፦ “ አንድ ስመጠር ጀግና ጠመንጃ ተኩሶ ያሰው ህይወት በማጥፋቱ፣ ለፍርድ ከዳግማዊ ምኒሊክ ዙፋን ችሎት ቀርቦ፣ በህገ-መንግስቱ መሠረት ሞት በቃ ይፈርዱበና እንዲገደል ትእዛዝ ይሰጣሉ። በወቅቱ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ (አባመላ) አብረው ስለነበሩ፣ ፍርዱን እኔ አስፈፅማለሁ እጁ ለኔ ይሰጠኝ ጌታዬ በማለት አስፈቅደው ወንጀለኛውን ወስደው በአንድ ሰዋራ ሥፍራ ሸሽገው ምግብና መጠጥ በስርዐት እንዲሰጠው አድርገው ያኖሩታል። ጥቂት ከረምረም ብሎ የተወሰኑ ጦረኞች ሸፍተው ከባድ ጦርነት በሀገር ውስጥ ያገረሽና በርካታ ህዝብና ሀገር ይታመስና አጼምኒሊክ የሚያደርጉት ግራይገባቸዋል። አንድ ቀን ፊታውራሪ ሀባተጊዮርጊስንና ሌሎች ባለማሎቻቸውን አስጠርተው በእልፍኛቸው የጦር ስልት ለመንደፍ ምክር ይጀምራሉ። በመሀል የዛ ሞት ፈረዱበትን ሰው ጀግንነትና የጦር ስልት አዋቂነት አስታውሰው በፀፀት፦
ጋረድ ለምን ሞተ፣ ለምን ተቀበረ፣
ክፉ ለክፉ ቀን፣ ይሆን የነበረ።….አሉ ይባላል።
እኔም ይህን ጉዳይ ማውሳቴ፣ << ያለክህነት ቅዳሴ፣ ያለ ወንድነት አንካሴ >> አይበጅምና ለዓላማችን የጨከን፣ ለእውነት የኖርን፣ በምግባራችን የተጋን፣ በታሪካችን የኮራን ልንሆን ይባናል ለማለት ያህል ነው።
በጥቅሉ፣ በፖለቲካ ትግል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚቻለው መሪዎችም ሆኑ ደጋፊዎች የተሻለ ማድረግ ሲችሉ ብቻ ነው። ያን ለማድረግ ደግሞ የድርጅት ፍቅር፣ የአላማ ፅናት፣ ከልብ መነሳሳት ያስፈልገዋል። የትግል ስሜታችን የሚነቃቃው ከልባችን እንዲሆን ከምንሻው ግብ ወይም አላማና ጠረፍ ነው። በዚያም ላይ አነጣጥረን በሚኖረን የትግል ቁርጠኝነት ሳቢያ ወደ ላቀ ብቃት እንሸጋገራለን። ከፊታችን አፍጠውና አግጠው ያሉትን ችግሮቻችንም ቢሆኑ፣ በአግባቡ መልኩ ማስተናገድ ከቻልን ቀውሶቻችንንም ለመመከት የተሻለ አቅም ለመፍጠር ያስችለናል። ድል ደግሞ የጥረትም የአጋጣሚም ውጤት መሆኑ ከቶ መዘንጋት የለበትም። በአሰተሳሰብ ተነሳሽነትና ልቀት እሸናፊ ሆነን እስካልወጣን ድረስ ህዝባችንን ከነገው ረሀብና እርዛት፣ ጉስቁልና፣ የመብት ረገጣና ጭቆና፣ እንዲሁም ስደትና ሞት ልንታደገው ፈፅሞ አይቻለንም። ይህን ብሄራዊ ሃላፊነት በብቃት መወጣት የምንችለው ደግሞ << አንጀት ከተቋደስን፣ አንገት ከተላላስን >> ብቻ ነው። ምክንያቱም እኛ የሁለት ታላላቅ ዛፎች ውጤት ነን፣ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት። ዘራችንም እየተበተነ ያለው በልባችን ውስጥ በሚነፍስ ማእበል ነው። ከምናወጣው ህግና የፍልስፍና ቀመር ባሻገር፣ ራሳችንን በእውነት ገርተን፣ አምናና ከርሞን አማትረን፣ በዛሬ የጊዜ ምህዋር ለራስም፣ ለወገንም የሚበጅ የትውፊት ቅሪት ጥለን ለትውልድ ለማለፍ ሲባል << ሁሉን መሸከም የሚችል ትከሻ፣ ጎባጣን የሚስለጥ ወጌሻ >> ሆነን ልንገኝ ይገባል። ያ ደግሞ በዜግነታችንም እንደግል ይሁን በተደራጀን መልኩ ህዝብ ከሚመራ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት አመራር ብቃት የሚወሰን ነው።
የዘንድሮው ነገር ይበልጡን አይመስል፣
የከረመው ያራል አዲሱን ሳማስል።
….እንዳይሆንም ጭምር ዜጋዊ ምክሬ ለመሰንዘር ያህል ነው፡። ተዳፍሬ ከሆነ እነሆኝ አፌን በዳቦ …? ብያለሁ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
የህዝብ ትግል ያሸንፋል!
ቸር ይግጠመን፦
አክሊሉ ሃይሉ (aklilu.h2@googlemail.com)
(ጀርመን፦ ሰፕቴምበር – 2012)

No comments:

Post a Comment