Translate

Monday, September 17, 2012

መልካም አዲስ ዓመት ከብሩህ ራዕይ ጋር!!!


ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገረን ይላል። መጪው ዓመት ከወያኔ ዘረኛ ፓሊሲ ተላቀን ኢትዮጵያዊያን በአገራችን ጉዳይ ላይ ወሳኞች የምንሆንበት ዓመት እንዲሆን ይመኛል። በተጨማሪም አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊያን የወያኔ ባለሟሎች በዘረፋ መክበርን እየታዘቡ መቆጨታቸው የሚያበቃበት፤ ሕዝብ የአገሩም የሃብቱም ባለቤት የሚሆንበት ሥርዓት መሠረት የሚጣልበት ዓመት እንዲሆን ይመኛል።
ያለፈው 2004 ዓ. ም.  ግዙፍ የሆኑ አገራዊ ክስተቶች የሞሉት ዓመት ነበር። በፀረ ሽብርተኝነት ህግ ሽፋን በበርካታ ንፁሃን ዜጎች ላይ በደል ተፈጽሟል። የበደሉ ብዛት መምህር የኔሰው ገብሬን የመሳሰሉ ወጣቶች በገዛ ራሳቸው ሕይወት ላይ ሳይቀር እንዲፈርዱ አድርጓቸዋል። እጅግ የከፋ የኑሮ ውድነት  በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ስደት ገፍቷቸዋል። በጉራ ፈርዳ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ኦጋዴን፣ ወልቃይት ዋልድባ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ገጠሮች ኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች ሲያለቅሱና ሲያነቡ ነው ዓመቱን ያሳለፉት።

በ 2004 ሙስሊምም ክርስቲያንም ወገኖቻችን የእምነት መብታቸውን ለማስከበር ትግል ውስጥ የገቡበት ዓመት ነበር። ሙስሊሞች ወያኔ በሃይማኖታቸው ጣልቃ እንዳይገባ ለመጠየቅና መሪዎቻቸውን በነፃነት ለመምረጥ፤ ክርስቲያኖች ደግሞ ዋልድባን ከጥፋት ለማዳን  በሚያደርጉት ጥረት አብረው የቆሙበት ዓመት መሆኑ 2004 ዓ.ም. በበጎ የሚዘከርበት ሆኗል። ከሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በተጨማሪም የኢትዮጵያ መምህራን የኑሮ ውድነትን ያላገናዘበ የይስሙላ የደመወዝ ጭማሪ በመቃወም የሥራ ማቆም አድማ የመቱበት ዓመት መሆኑ የወያኔ የአገዛዝ እድሜ እያጠረ  መሆኑን ያመላከተ ዓመት ሆኖ አልፏል።
2004 ዓ. ም. የተጠናቀቀው በሁለቱ ዋና ዋና የሥርዓቱ ቁንጮዎች ማለትም በዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና በፓትሪያርኩ አቡነ ጳውሎስ ህልፈት ነው። ሁለቱም በተፈጥሮ  ምክንያቶች በአንድ ወቅት ማለፋቸው ቤተመንግሥትም ቤተክህነትም አዲሱን ዓመት ከብዙ ብዥታዎችና ስጋቶች ጋር እንዲቀበሉ አስገድዷቸዋል።
የሟቹ የመለስ ዜናዊ ተከታዮች መጪዎቹ ዓመታት የጌታቸው ራዕም ተግባራዊ የሚደረግባቸው ዓመታት ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ።  ለመሆኑ የመለስ ዜናዊ ራዕይ ምን ነበር?
የመለስ ዜናዊ ራዕይ ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ማዳከም፤ ዘረኝነትን ማንገስ፤ ሃብቷን መመዝበርና ማስመዝበር ነበር። ይህንን ራዕይ ለማሳካት ሲል ነው በቅድሚያ ህወሓትን ቀጥሎ በየቦታው አምሳያችን እና ኢህአዴግን ያደራጀው።
መለስ ዜናዊ በተወሰነ መጠን ራዕዩ ተሳክቶለት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ አዳክሟል፤ የራሱን ጠባብ ቡድን አባላትንና ምስለኔዎቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት እንዲያካብቱ ረድቷቸዋል። ዛሬ እነሱ ማመን በማይቻል መጠን ከብረዋል። ተከባብሮ ይኖር የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲናቆር ተደርጓል። የመለስ ዜናዊ ባለሟሎች እንዲቀጥል የሚፈልጉት ይህ ነው።
የመለስ ዜናዊ ራዕይ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መጥፊያ ነው። የመለስ ዜናዊ ራዕይ በዘራቸው የተመረጡ ጥቂት ሰዎች የተንቀባረረ ሕይወት ሲመሩ እያየ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በረሃብ እንዲያልቅ በችግር እየማቀቀ የምድር ሲኦል እንዲገፋ እየተደረገ ነው። የመለስ ዜናዊ ራዕይ ለም መሬታችን በሙሉ ለቻይና፣ ህንድና አረብ ቱጃሮች ተሰጥቶ ኢትዮጵያዊ ድሃ ገበሬ በስደት እንዲያልቅ፤ በገዛ ሀገሩ ባይትዋር እንዲሆን፤ የበይ ተመልካችና ተመጽዋች የሚያድርግ ነው። የመለስ ዜናዊ ራዕይ በቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌደራል መንግሥት ያሉት የመንግሥት ሥልጣኖች በሙሉ በእሱ ወገኖች እጅ ውስጥ ሆኖ የፈለጉትን እያስቀመጡ ያልፈለጉትን ደግሞ እያነሱ እድሜ ልካችንን እንዲገዙን ነው። የመለስ ዜናዊ ራዕይ የኢትዮጵያ ጠላት ራዕይ ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የመለስ ዜናዊ ተከታዮች የጌታቸውን ራዕይ የሚያሳኩበት እድል ሊሰጣቸው አይገባም።
በአንፃሩ የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ራዕይ የሚከተለው ነው።
 የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ራዕይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ የተከበረበት፤ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅበራዊ ፍትህ የሚገኝበት፤ የዜጎች ሕይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበረበት እና የሕዝቧ አንድነትና ትስስር የጠነከረበት ሃገር እንዲኖረው ማድረግ ነው።
 አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የግንቦት 7ን ራዕይ ይጋራል ብለን በጽኑ እናምናለን። የግንቦት 7 ራዕይ እውን እንዲሆን ግን የዚህ ራዕይ እንቅፋት የሆነው ወያኔ መገደድ አሊያም መወገድ ይኖርበታል።
አዲሱ 2005 ዓ. ም. ወያኔን አስገድደን ወይም አስወግደን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች  የተከበበሩባት፤ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅበራዊ ፍትህ የሚገኙባት፤ የዜጎች ሕይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበሩባት እና የሕዝቧ አንድነትና ትስስር የጠነከሩባት ሃገር መገንባት የምንጀምርበት ብርሃናዊ ዓመት እንዲሆንልን እንመኛለን።

መልካም አዲስ ዓመት!!!

No comments:

Post a Comment