Translate

Monday, September 17, 2012

ኢህአዴግ ቀጣዩን ምርጫ ካሸነፈ አዲስ ተሿሚዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በስልጣናቸው ይቀጥላሉ ሢሉ አቶ በረከት ስምዖን ተናገሩ


ኢሳት ዜና:-የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ይህን ያሉት፤ የኢህአዴግ ምክር ቤት ቅዳሜ ዕለት ሊቀ-መንበሩን እና ምክትል ሊቀ-መንበሩን መምረጡን ተከትሎ ከኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሀላፊው ከአቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር በሂልተን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
ቀደም ሲል የህወሀቱን አቶ ስብሀት ነጋን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የሚመረጠው ሰው ሹመቱ የሚቆየው እስከ ቀጣዩ ምርጫ እንደሆነ እና ከዚያ ኢህአዴግ በምርጫው ካሸነፈ በፓርላማ ቋሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደሚሾም በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
አቶ በረከት በሂልተን በሰጡት መግለጫ ግን ኢህአዴግ ቀጣዩን ምርጫ ሲያሸንፍ አሁን የተመረጡት አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ እና አቶ ደመቀ መኮነን በያዙት ቦታቸው እንደሚቀጥሉ ነው ከወዲሁ የተናገሩት።
አቶ በረከት የአቶ መለስ ሞት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተነገረ በዚያኑ ቀን በፍጥነት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፦” አቶ ሀይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አቶ መለስን ተክተው ይሠራሉ” በማለት   መናገራቸው በህወሀት አባላት ዘንድ ከፍ ያለ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም።

ቅሬታው ባልበረደበት ሁኔታ ነው አቶ በረከት በአሁኑ መግለጫቸው፦”ኢህአዴግ ቀጣዩን ምርጫ ካሸነፈ አዲሶቹ የድርጅቱ ሊቃነ-መናብርት፤ ዋና እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሆነው ይቀጥላሉ” ያሉት።
የኢሳት ዘጋቢዎች ከአገር ቤት ያሰባሰቧቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ከቀናት በፊት በአመዛኙ ከህወሀት የሆኑ መኮንኖች በጀነራልነት የተሾሙ ቢሆንም፤ህወሀት ከ 21 ዓመታት በሁዋላ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ላይ ሙሉ በሙሉ መገለሉ ያልተዋጠላቸው ህወሀቶች፤ድርጅታቸው በብዙ ዘርፎች የደከመበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማውራት ጀምረዋል። ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተለው ዘጋቢያችን እንዳለው ደግሞ ህወሀት የቀድሞ ሀይሉን ይዞ ለመቀጠል ሊቸግረው ይችላል።
አቶ በረከት በሂልተኑ መግለጫቸው ህወሀት በአቶ መለስ ምትክ ሊቀ-መንበሩን ገና አልመረጠም ሲሉም ተናግረዋል።
ያለ ዋና ሊቀ-መንበር ከሁለት ወራት በላይ የቆየው ህወሀት እስካሁንም መሪውን መተካት ያልቻለው በውስጡ በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል።ኢሳት የውስጥ ምንጮችን በመጥቀስ እንደዘገበው አቶ አባይ ወልዱ የህወሀት ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡
አንጋፋው የህወሀት መስራች አቶ ስብሀት ነጋ በአቶ መለስ ሞት ማግስት፤-“መለስ ፤ህወሀትንም ጭምር ነው ገድሎት የሞተው” በማለት የቀድሞ የድርጅቱን ታጋዮች ሲቀሰቅሱ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment