Translate

Monday, September 24, 2012


ኢሳት ዜና:-የህወሀት መስራች የሆኑት አቶ ስብሀት ነጋ ይህን ያሉት ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።
ቀደም ሲል  የህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ-ህወሀት ሊቀ-መንበር ሆነው የተመረጡት አቶ አባይ ወልዱ ብሔራዊ እርቅ  የሚለው ጥያቄ  ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖረውና  ጥያቄውን የሚያነሱ ሀይሎችን  እንደሚታገሏቸው  መናገራቸው ያታወሳል።
የአቶ አባይ ወልዱ  አባባልም ሆነ፤ አቶ ስብሀት ለ አዲስ ጉዳይ መጽሔት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ያንጸባረቋቸው ሀቆች፤ ኢህአዴግ አዲስ ሊቀመንበርና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሾመ ቢያውጅም፤ ስለ አገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ ፤ከሁዋላ ብቻ ሳይሆን ከፊት ጭምር ሆነው እንደ መሪ እየተናገሩና እየሠሩ ያሉት የህወሀት ሰዎች መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ብለዋል-ቃለ ምልልሱን ያደረሱን አንባቢዎች።


በቃለ-ምልልሱ፦”ከአቶ መለስ መሰዋት በኋላ ድርጅቶቹ፤ ማለትም- ኢህአዴግና ህወሃት እንደነበሩ አሉ.”ያሉት አቶ ስብሀት..፤መለስ ስለሞቱ  በድርጅቱ ውስጥ ምንም ጉድለት  እንደሌለ እና ወደፊትም ጉድለት የሚባለው ቃል ራሱ ሊመጣ እንደማይችል ተናግረዋል።
አክለውም፦”…ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ ተማሪዎችም፣ አስተማሪዎችም ናቸው፤ባለን ልምድ ቀውጢ ነገር ሲፈጠር ድርብ ድርብርብ አቅም ነው የምንፈጥረው።…”ብለዋል-አቶ ስብሀት።
አቶ መለስ ሞተዋል ተብሎ በ ኢሳት ከተዘገበ ወዲህ ወደ መድረክ በመውጣት -በኢህአዴግ ውስጥ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበራቸውን ጉልህ ድርሻ ፦ሲያሳንሱ የቆዩት አቶ ስብሀት፤  አስፈላጊ መስሎ ሲታያቸው ደግሞ የአቶ መለስን የሀዘን ስነ-ሥርዓት እንደ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሲያደርጉት ተስተውለዋል።
የ አቶ መለስን ሞት ተከትሎ በነበረው የሀዘን ሥርዓት ህብረተሰቡ ያለፍላጎቱ ተደጓል ከሚባለው ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ፦<< .ሁላችንሞ እንደምናውቀው የሞቱ ዜና ከተሰማ በኋላ በየቤቱ ፎተግራፎች ተሰቅለው ተመልክተናል። ይህ የሚያመለክተን ህዝብ ለራሱ ለጥቅሙ አዋቂ መሆኑን ነው>>ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
አቶ ስብሀት አያይዘውም፦”ይሄ ሃሳብ ፀሐይ በምዕራብ ትወጣለች ዓይነት ነው። ይሔ ገበያ እኮ አይደለም። ይህንን ሰምቶ ያመነ ነው ጅል ማለት። ከይህንን ሰምቶ እውነት ሊሆን ይችላል ብሎ የሚያምንን እግዚአብሔር ይማረው። በአጠቃላይ ተቀስቅሶ ነው፥ ገንዘብ ተሰጥቶ ነው የሚሉትን ሁሉ ምህረት ያውርድላቸው። በአንድ ደቂቃ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ እንዴት ታዳርሳለህ? እንዴትስ ትቀሰቅሳለህ? ይህን ጥያቄ በማንሳትህ ብዙ አልቀየምህም።”
አብዛኛው ህዝብ ለለቅሶ በግድ እንዲወጣ መደረጉን ለኢሳት የደረሱ እጅግ በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ስለ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የወደፊት አሠራር ሲናገሩም፦<<እንዴት ይሠራል? የት ሆኖ ይሰራል? ከመለስ ጋር የነበሩ ምሁራን ይቀጥላሉ?ወይስ አይቀጥሉም  እነዚህ ታላላቅ ምሁራን ቢቀጥሉ ምንድን ነው ጉዳቱ?…”የሚለውን ለመገመት አልችልም>> ብለዋል።

የብሔራዊ እርቅና የጥምር መንግስት ጥያቄ ስለሚያቀርቡ ተቃዋሚዎች ጉዳይ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከት ብለው የሳቁት አቶ ስብሀት፤ አስከትለውም፦ <<የስልጣንም ይሁን የኢኮኖሚ ስስት ምን ያህል የሰው ልጅን እንደሚያዋርድ ከእነዚህ ሰዎች ተምረን መረዳት አለብን።…”ሲሉ ፓርቲዎቹን ዘልፈዋቸዋል።
አቶ ስብሀት ፓርቲዎቹን በመዝለፍ ብቻ አላቆሙም።<< እነዚህ ጥምር መንግስት የሚሉ ፓርቲዎች ሕጋዊ ፖለቲካዊ ድርጅቶች ሆነው ሊቀጥሉ ይገባቸዋል ወይ? የሚል ጥያቄ ለምርጫ ቦርድና ለሕግ ምሁራን አቀርባለሁ። አስፈላጊ እርምጃም መወሰድ አለበት።” ብለዋል።
አቶ ስብሀት  የጥምር መንግስት ጥያቄ በሚያቀርቡ ተቃዋሚዎች በህጋዊነት በመቀጠልና ባለመቀጠላቸው ዙሪያ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ የሚያቀርቡት በምን ካፓሲቲያቸው እንደሆነ አልገለጹም።
አቶ ስብሀት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ባልተሾሙበት ሁኔታ ስለ አዲሱ መንግስት የወደፊት አቅጣጫ፣ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህልውና እና ስለሌሎች አብይ ጉዳዮች በየ አደባባዩ እየተናገሯቸው ያሉት ነገሮች፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በነጻነት የሚሠሩበት መንገድ ጨርሶ የተዘጋ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው ሲሉ የመጽሔቱ አንባብያን ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment