ኢሳት ዜና:-ሰሞኑን በኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት በከፍተኛ ደረጃ የተሾሙትን አቶ ሀለማርያም ደሳለኝንና ምክትላቸውን አቶ ደመቀ መኮንንን ጠቅላይ ሚኒሰትር አድርጎ ለማሾም ሽርጉዱ መቀጠሉን የኢሳት ምንጮች ገልጠዋል።
አቶ በረከት ስምኦን ከፍተኛ ድል እንዳገኙ በተነገረበት በዚህ ሹመት፣ አቶ ሀይለማርያምን በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ወደ ፓርላማ አቅርቦ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በይፋ ለማሾም የሩጫ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል። የአገሪቱ ፓርላማ መደበኛ ስራውን መስከረም 25 የሚጀምር ቢሆንም፣ የአቶ በረከት ቡድን እስከዚያ ቀን ድረስ ለመታገስ ፍለጎት የሌለው መሆኑን ነው ምንጮች የሚገልጡት። የቃለመሀላ ስነስርአቱን ለማፋጠን የተፈለገውም ከህወሀት በኩል ሊደረስ የሚችለውን ያልተጠበቀ ተቃውሞ በመፍራት ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ይናገራሉ።
ህዝባዊ ወያን ሀርነት ትግራይ ቀድሞ የነበረውን ሀይሉን አሰባስቦ የጠቅላይ ሚኒሰትርነቱን ቦታ ለመያዝ ባልቻለበት በዚህ ሁኔታ፣ አቶ በረከት ስምኦን የኦህዴድ አባላትን አሳምነው አቶ ሀይለማርያም እንዲመረጡ፣ ከዚያም አልፎ ምክትላቸው እርሳቸው በፖለቲካ ኮትኩተው ያሳደጉዋቸው አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሆኑ ያደረጉት ጥረት እንደተሳካላቸው የቅርብ ሰዎች ይናገራሉ።
አቶ በረከት የፖለቲካ ጨዋታቸውን የጀመሩት የአቶ መለስ ራእይ አስፈጻሚ ሆነው በመቅረብ እንዲሁም የአቶ መለስን የለቅሶ ስነስርአት ሂደት በመቅረጽና ድርጅቱና አቶ መለስ የህዝብ ድጋፍ እንዳላቸው አድርጎ የፕሮፓጋንዳ ስራ በመስራታቸው ፣ ኦህአዴድንም ሆኑ ህወሀቶችን በተከላካይ ቦታ እንዳስቀመጡዋቸው ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ምንጮች ይገልጣሉ።
ምንም እንኳ አቶ መለስ ራሳቸው የመረጡዋቸው አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከሌሎች የኢህአዴግ ሰዎች የተሻሉ እንደሆኑ ቢነገርላቸውም፣ የአሿሿም ሂደቱ እርሳቸውን በአቶ በረከት ጫማ ስር የሚያስቀምጥ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ። አዲሶቹ መሪዎች የአቶ መለስና የአቶ በረከትን ያለፉት 21 አመታት የፖለቲካ ፕሮግራም እንዳለ ከመተግበር ውጭ ሌሎች ለውጦችን እንደማያደርጉ በይፋ መናገራቸው ይታወሳል።
አቶ በረከት ቀደም ብለው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒሰትር በመስከም ወር መጨረሻ እንደሚሾሙ ተናግረው ነበር። ይሁን እንጅ ሹመቱ ምናልባትም በያዝነው ሳምንት ውስጥ ሊሰጥ እንደሚችል ነው ምንጫችን የጠቆሙት።
99.6 በመቶው የሚሆነውን የፓርላማ ወንበር የተቆጣጠረው ኢህአዴግ ሹመቱን ለማጸደቅ የሚገደው ምንም ነገር የለም። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ብርሀነ ገብረክርስቶስን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በማድረግ ሊሾሙዋቸው ይችላሉ የሚሉ መረጃዎች አሉ።
No comments:
Post a Comment