Translate

Friday, September 14, 2012

የኢህአዴግ አድሏዊ ይቅርታና አሳፋሪው የነጭ አምልኮ

በዳዊት ከበደ (አውራምባ ታይምስ)
ባለፈው ሰኞ በኢትዮጵያ አዲስ አመት ዋዜማ፤ ሁለቱ ስዊድናዊያን ጋዜጠኞች ተፈቱ፡፡ ይህ በጎ እርምጃና መልካም ዜና ነው፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከአንድ አመት በፊት በጋዜጠኞቹ መታሰር አለም አቀፍ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው እንዲህ ሲሉ ነበር ምላሽ የሰጡት ‹‹እነዚህ ጋዜጠኞች ከአሸባሪው አልቃይዳ ጋር አንድ ላይ በመሆን በሜክሲኮ በኩል የአሜሪካን ድንበር ሲያቋርጡ ቢያዙ ኖሮ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት…
ተሟጋች ድርጅቶች አሁን እንደሚንጫጩት አይንጫጩም ነበር፡፡ የነጭም የጥቁርም ደም እኩል ነው›› ካሉ በኋላ ‹‹እንደውም እኛ ሆነን ነው እንጂ በሚሳይል መመታት ነበረባቸው›› አይነት አንድምታ ያለው ንግግር አደረጉ፡፡ ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ም/ኃላፊ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማልም በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፤ ‹‹የመንግስት አቃቤ ህግ በጋዜጠኞቹ ላይ ክሱን የመሰረተው ሽብርተኝነትን በሙያ በመደገፍና በማበረታታት፣ በሽብር ድርጊቶች ውስጥ በመግባትና በመሳተፍ፣ ብሎም በህገወጥ መንገድ ከፍቃድ ውጭ ወደአገር ውስጥ በመግባት ነው››። ብለው ነበር፡፡ በመርህ ደረጃ አቶ መለስም ሆኑ ሽመልስ የተናገሩት ልክ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሬት ላይ ያለው እውነት ግን ከዚህ በፍጹም የተለየ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞች ለሚያቀርቡት ትችት ትግስት የለውም፡፡ ጋዜጠኞቹ እንደውም ስዊድናዊያን ባይሆኑ ኖሮ ከአንድ ቀን በላይም አይታሰሩም ነበር፡፡ እኔ በግሌ እንደማውቀው ከዚህ በፊት የኒው ዮርክ ታይምሱ ጄፍሪይ ጄትልማን ከሁለት ባልደረቦቹ ጋር እንዲሁም የቪኦኤው ሄዘር ሙርዶክ በቦታው ላይ ሲገኙ አንድ ቀን ብቻ ታስረው ያለምንም ችግር ተለቀዋል፡፡ ነገር ግን የስዊድን መንግስት ከ2008 ጀምሮ (ከወ/ሪት ብርቱካን ዳግም እስር ጋር በተያያዘ) በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝና በፕሬስ ነጻነት ዙሪያ ልዩነቱን በይፋ ማንጸባረቁን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በኢምባሲ ደረጃ የነበረውን ግንኙነቱን ከሀምሌ 2002 ዓ.ም አንስቶ ወደ ቆንስላ ዝቅ ለማድረግ እንደተገደደ አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከስቶክሆልም ጋር በቆንስላ ብቻ የተገደበ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብትጀምርም ስዊድን ግን በአዲስ አበባ ያላት የዲፕሎማሲ እርከን ከፍ ባለ መልኩ በኤምባሲ ደረጃ ነው፡፡
ስዊድን በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ይህ አይነቱን ጥያቄ ስላነሳች የአቶ መለስ መንግስት ያን ያህል ለበቀል መነሳሳት አልነበረበትም፡፡ ምክንቱም በኢትዮጵያና በስዊድን መካከል ለዘመናት የዘለቀ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊና ታሪካዊ ግንኙነት ነበር፡፡ የመጀሪያዎቹ ክርስቲያን ሚሺነሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተከትሎ ስዊድናዊያን በእርዳታና በተለያዩ የገጠር ልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በዚህ በኩል SIDA የተሰኘው የስዊድን መንግስታዊ ተራድኦ ድርጅት ተጠቃሽ ነው፡
እነ ማርቲንን እንደመቀጣጫ
የአቶ መለስ መንግስት እነ ማርቲን ስቺቢን ለማሰር የተገደደው የአውሮፓ ህብረት በአቶ መለስ መንግስት ላይ ጫና እንዲያደርግ እጅግ ከፍተኛ ግፊት በማድረግ ላይ ለሚገኙት የስካንዲኒቪያ አገራት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ፖለቲካዊ መልእክት በማስተላለፍ ለማለሳለስ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ጋዜጠኞቹን ረጅም ጊዜ ለማሰር ሳይሆን በሦስተኛ ወገን አስማሚነት በኩል ለስዊድኖቹ ስውር ቅድመ-ሁኔታ በማስቀመጥ ሊቋጭ ይችላል የሚል ተስፋም ነበራቸው፡፡ የሆነውም እንደዛ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የእንግሊዝና የኖርዌይ ኤምባሲዎች በአቶ መለስና በስዊድናውያኑ መኃከል ስምምነት ለመፍጠር ብዙ ጥረት እንዳደረጉ ይታወቃል፡፡ በተለይ የኖርዌይ ባለስልጣናት ረቂቅ ዲፕሎማሲ (Subtle Diplomacy) የሚባለውንና ድንገተኛ ስብሰባ አመቻችቶ በተቃራኒ ፓርቲዎች መሃል ህዝባዊ ትኩረት የማይስቡ ድርድሮችን በማካሄድ የታወቁ ናቸው። ከስካንዲኒቪያን አገሮች ባሻገር የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ መንግስትም ለስዊዲናዊያኖቹ መፈታት ብዙ ጥረት እንዳደረጉ ታወቃል፡፡
ለኛስ ማን ይጩህልን
እነዚህ ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች ወደስፍራው ያቀኑት የሽብር ተልእኮ አንግበውና እውነትም ኢህአዴግ እንዳለው አዲስ አበባን ወደ ባግዳድ ለመቀየር ከሆነ፤ ከባልደረቦቼ ውብሸትና ርዕዮት ያነሰ ሳይሆን ከዛ በላይ ፍርድ ይገባቸው ነበር፡፡ ኢህአዴግ ግን እንደሚያወራው ሳይሆን ነጭ የሚያመልክ ስርዓት በመሆኑ ‹‹በቃ›› የሚልን ፖስተር ፎቶ አንስታችኋል ባላቸው ባልደረቦቼ ላይ የ14ዓመት ጽኑ እስራትና የ33ሺህ ብር ቅጣት ሲበይን የጦር መሳሪያ ይዘው በህገወጥ መንገድ ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ድንበር ጥሰው ገቡ በተባሉ ስዊድናዊያን ጋዜጠኞች ላይ የተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ግን 11 ዓመት ብቻ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ስዊድኖቹ ለምን ተፈቱ አሊያም ቅጣታቸው ለምን አነሰ የሚል መከራከሪያ እያቀረብኩ አይደለም፡፡ አንድ መንግስት ግን ከባዕድ ባልተናነሰ መልኩ (እንደውም በተሻለ) ዜጎቹን ማክበር አለበት፡፡ የአውሮፓ ህብረትና ስቴት ዲፓርትመንት ለስዊድን ጋዜጠኞች የተከራከረውን ያህል የእኛ መንግስት ለዜጎቹ ክብር እንደሌለው በዚህ የይቅርታ አዋጅ አፈጻጸም ብቻ በተጨባጭ አስመስክሯል፡፡
አዎ! እነ ውብሸት የስካንዲኒቪያን መንግስታት አሊያም የአውሮፓ ህብረት፣ የእንግሊዝና የኖርዌይ ዲፕሎማቶች አይከራከሩላቸውም፡፡ ሲኤን ኤንም ሆነ ዋሺንግተን ፖስት ሽፋን አይሰጣቸውም፡፡ የስዊድን መንግስት ለዜጎቹ የሚንሰፈሰፈው ያህልም መንግስታቸው አይጨነቅላቸውም፤ ሌላው ቀርቶ ከክሳቸው ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተቆራኘ ጉዳይ ያላቸው የኢትዮጵያ ድረገጾች እንኳን ለጉዳያቸው ይህነው የሚባል ሽፋን ሊሰጡ አልፈቀዱም፡፡ እናም ፈረንጆቹ ሲፈቱ ከፈረንጆቹ ቀድመው ይቅርታ የጠየቁት እነ ውብሸት እዛው ጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ ተወሰነባቸው፡፡ ይህ እንደዜጋ በጣም ያበሽቃል፡፡
እንደሚታወቀው ውብሸትና ርዕዮት የታሰሩት በሰኔ ወር 2003 መጀመሪያ ላይ ሲሆን ስዊድናዊያኑ ደግሞ ከአንድ ወር በኋላ በሀምሌ 2003 አጋማሽ ላይ ነው:: ሆኖም የነጮቹ የፍርድ ሂደት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ እንዲፋጠን ተደረገ፡፡ በዲሴምበር 27/2011ም ፍርድ ተሰጣቸው፡፡ የእነ ውብሸት ግን ወደኋላ እንዲጎተት ተደርጎ በጃንዋሪ 26/ 2012 ተጠናቀቀ፡፡ ከዛ በኋላ ከእስር ቤት ለመውጣት ብቸኛው አማራጭ ይቅርታ መፈረም ብቻ እንደሆነ የተረዱት እነዚህ ታሳሪ ጋዜጠኞች (ውብሸት ታዬ፣ ጆአን ፐርሰንና ማርቲን ሺቢዬ) ለመንግስት የይቅርታ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ እናም የነጭና የጥቁር ደም አንድ አይነት ነው የሚል እምነት የነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ‹‹አዲስ አመት ሲመጣ ፈረንጆቹን ጋዜጠኞች ብቻ ፍቱ›› የሚል የኑዛዜ ቃል በቤልጂየሙ ሆስፒታል ትተው ያለፉ ይመስል በይቅርታ አዋጅ ስነስርዓት መሰረት ይቅርታ ከጠየቁ ጋዜጠኞች መካከል ኢትዮጵያዊያኑ ብቻ ተለይተው እንዲቀሩ ተደረገ፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡
ሰሞኑን በአቶ መለስ ህለፈት ያተኮሩና ባለፉት 21 ዓመታት ያልሰማናቸው ብዙ ነገሮችን እየሰማን ነው፡፡ ከእነዚህ ፕሮፖጋንዳዎች መካከል ‹‹መለስ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው አይሰጡም›› የሚል ይገኝበታል፡፡ እኔ ግን አይመስለኝም፡፡ ለኢትዮጵዊያን የወጣ ህግ ከአገሬው ሰው የበለጠ የውጭ ዜጎችን ተጠቃሚ ሲያደርግ በተጨባጭ እያየን ነው፡፡ ቢያንስ የኢንቨስትመንት አዋጁና የይቅርታ አዋጁ እዚህ ላይ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አገሬን ጥዬ ከመሰደዴ ከስድስት ቀን በፊት በኖቬምበር 12/2011 ውብሸትን ቃሊቲ አግኝቼው ነበር፡፡ እውነት ለመናገር ውብሸት ከማንም ያነሰ ወኔና የትግል ተነሳሽነት ስላለው ሳይሆን ለህጻን ልጁ ለፍትህ ውብሸት ሲል ከፍርድ ውሳኔው በኋላ ይቅርታ ጠይቆ ሊወጣ እንደሚችል ነበር በወቅቱ የነገረኝ፡፡ አዎ! ባለቤቱ ስራ እንደሌላት አውቃለሁ፡፡ በእርግጥ ከአንድ አመት በፊት በውጭ የሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች (በጎ ፍቃደኞች) በቻሉት አቅም ባለቤቱን ይረዷት ነበር፡፡ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ግን አላውቅም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው መጠነ ሰፊ የኑሮ ውድነት ቤተሰቡ ምን እየሆነ እንደሆነ መረጃው የለኝም፡፡ ከተሰደድኩ በኋላ ግን ይቅርታ መጠየቁን ሰማሁ፡፡ ጳጉሜ 5 ቀን 2004 ዓ.ም በፍትህ ሚኒስቴር የሚገኙ ምንጮቼ የገለጹልኝም በአመት በአሉ ዋዜማ ከስዊድኖቹ ጋዜጠኞች ጋር አብሮ እንደሚለቀቅ ነው፡፡ ግን አልሆነም፡፡ የነጭና የጥቁር ደም እኩል አልሆነማ!
በተለያየ አጋጣሚ የማገኛቸው ጥቂት ግለሰቦች እንደነ እስክንድርና ውብሸት ስርአቱን ተጋፍጦ እስር ቤት መግባት እንጂ መፈርጠጥ አማራጭ እንዳልሆነ በመግለጽ በገደምዳሜ ይወቅሱኛል፡፡ ወቀሳ በጣም ቀላል ነው፡፡ እንዲህ አይነቱን ትችት ለሚሰነዝሩ ወገኖች በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ፡- ያልታሰረው እንዲታሰር የምንተጋውን ያህል ለታሰሩት ወገኖቻችን ምን አይነት እገዛ እያደረግን ነው? ለሚለውም ወሳኝ ጥያቄ መልስ ማዘጋጀት አለብን፡፡ አለበለዚያ ግን ጭካኔ ነው እጅግም ያስተዛዝባል፡፡
/ዳዊት ከበደ የአውራምባ ታይምስ ድረገጽ ማኔጂንግ ኤዲተር ነው

No comments:

Post a Comment