Translate

Wednesday, September 19, 2012

አቶ አባይ ጸሀይ በአባ ወልደ ማርያም አማካኝነት ከዋልድባ መነኮሳት ጋር ተነጋገሩ


  • አቶ አባይ ፀሐይ በአባ ወልደ ማርያም (የጻድቃኔ ማርያም መነኮስ) አማይኝነት ከዋልድባ መነኮሳት ተገናኝተው   ነበር
  • የዋልድባ መነኩሳት በቤተክርስቲያናችን ድርድር የለንም፣ ሕይወታችንን ለመስጠት ዝግጁ ነን
  • እኛ ገዳሙ እንዲነካ አንፈልግም፣ ገዳሙ እንዲታረስ ልንፈቅድ አንችልም
  • መነኮሳቱ ግን እየተሰደዱብን ነው

ከትላንት በስቲያ በአባ ወልደ ማርያም (የጻድቃኔ መነኮስ) አማካኝነት አራት የዋልድባ መነኮሳት፣ አባ ወልደ ማርያም፣ እና አቶ አባይ ጸሐዬ ተሰብስበው እንደነበር ከታመኑ ምንጮቻችን ዘገባ ደርሶን ነበር።
በስብሰባውም ላይ አገናኙ አባት እኔ መነኮሳቱን አውቃለሁ የልማቱን ሥራ እንዲቀጥል መደረግ ይኖርበታል በማለት የዋልድባ መነኮሳት የቅዱስ ፖትርያርኩን ሞት ተከትሎ ለሥርዓተ ቀብሩ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ያወቁት እኝሁ አባት ከአቶ አባይ ጸሀይ ጋር መነኮሳቱን ለማገናኘት እላይ ታች በማለት ለማገናኘት ችለዋል።
በስብሰባውም ላይ ከዋልድባ የመጡት መነኮሳት በአሁን ሰዓት በርካታ መነኮሳት እየተሰደዱብን ነው፣ የአካባቢው ፖሊሶች እያስፈራሩን ነው፣ እየደበደቡን ነው፣ እኛ ገዳሙ እንዲነካብን አንፈልግም፣ ገዳሙንም ለማረስ ሳንፈቅድ ፈቀዳችሁ በማለት አሰወርታችኃል፣  በቤተክርስቲያናችን ህልውና ምንም ድርድር ልናደርግ አንችልም ሃሳባችን ይህው ነው በማለት እቅጩን ተናግረው ነበር።

አቶ አባይ ጸሐይም በበኩላችው የተሰደዱትንም መነኮሳት ወደ ገዳማችሁ ተመለሱ በሏቸው፣ ማንም ሊያሳድዳቸው አይችልም ወደ ገዳሙ ተመለሱ ብላችሁ ንገሯቸው እዛ ያሉትም የወረዳው አስተዳዳሪውም እስራቱን ማስፈራራቱን እንዲያቆም እናናግራቸዋለን፣ ነገር ግን በወጪ ሬድዮ የሚናገሩት አባቶችን በሙሉ በአደባባይ ይቅርታ የኢትዮጵያን መንግሥት ይቅርታ ይጠይቁ አለበለዚያ ግን ለእነሱ ይቅርታ እስካልጠየቁ ድረስ ወደ ገዳሙ መግባት እንደማይችሉ ነበር የተናገሩት።

በተለያየ ጊዜ በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ስለዋልድባ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ሲያስረዱ የቆዩትም አባት እንደሚያስረዱት: በመጀመሪያ ይቅርታ የምንጠይቀው ማንን ነው? ማን ይቅርታ ተጠያቂ? ማን ጠያቂ ሊሆን ነው? እንዴት ነገር የተገላቢጦሽ ይሆናል ነበር ያሉት። የሆነስ ሆነና ይቅርታስ የምንጠይቀው ምን ብለን ነው፣ ገዳማችንን አትንኩብን፣ የሃይማኖት መሰረታችን የሆነውን የቅዱሳን አጽም እንደ አሸዋ የፈሰሰበትን ቦታ አትረሱ ስላልን ነው ወይ ይቅርታ የምንጠይቀው። በመቀጠልም ገዳሙ አይነካብን ማለት የመነኮሳቱ ብቻ ጥያቄ መሆን እንደሌለበት አስረግጠው ነግረውናል፥ ይህ ታሪካዊ ገዳም የሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ የጳጳሳት፣ የመምህራን፣ የመነኮሳት፣ የዘማሪያን እንዲሁም የመላው ምዕመን ጥያቄ መሆን ነበረበት፣ ይህ ገዳም የሃይማኖታችን መገለጫ፣ የማንነታችን መኩሪያና ማሳያ፣ የታሪካችን አሻራ እንዲሁም የተለያዩ ቅዱሳን ገድል ያለባቸው በርካታ መጽሐፍት እና የተለያዩ የኢትዮጵያ ሀገራችን ቅርሶች ያሉበት ገዳም በመሆኑ ማንኛውንም የሃይማኖቱ ሰው ብቻ ሳይሆን ሃገር ወዳዱን ሕብረተሰብ ይመለከታል፤ በመሆኑም ይህንን ታሪካዊ እና ቅዱስ ቦታ የመጠበቅ ጠብቆም ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ያማድረግ ሃላፊነት የሁሉም ሃላፊነት መሆን እንዳለበት ነግረውናል።

እንደ እውነቱ ከሆነ የኛው አባቶች እሾም እሸለም ባዮች ወደ መንግሥት ነገሮችን እየወሰዱ የሚያመላልሱ ሰዎች እምኑ ላይ ይሆን የነሱ ለፈጣሪ ተገዥነታቸው? እውን እነዚህ ሰዎች ናቸው የወደፊቱ የቤተክርስቲያኒቱ ተረካቢዎች? መልሱን ለእነሱው እንተወው እና የኛ የምዕመናን ሃላፊነት እስከምን ድረስ ነው? እነዚህ እውነተኛ አባቶቻችን ለቤተክርስቲያናቸው ሕይወታቸን የተሰውላት፣ በፍጹም ቀናዒነት እና ተቆርቋሪነት ዱር ለዱር ፍርክታ ለፍርክታ ሲሳደዱ ማን ነው አለንላችሁ ሊላቸው የሚገባ፣ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ማንስ ነበር እንደነኚህ እውነተኛ አባቶች ባይሆን ኖሮ ዛሬ ዋልድባ ላይ የስኳር ፋብሪካው የገዳሙን ህልውና ሙሉለሙሉ በተቆጣጠረው ነበር። የገዛ ወገኖቻችን የቤተክርስቲያን ሰዎች ይልቁንም መነኩሳት እነኚህን አባቶች ለራሳቸው ተወዳጅነት ለማግኘት እንደ ማስያዣ ሲጫወቱባቸው፣ የቤተክርስቲያኒቱ የመጨረሻ የስልጣን እርከን ላይ ያሉት አባቶች ዝምታ፣ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚገኙ ካህናት እና መነኮሳት እኛን አይመለከትንም ብለው ፊታቸውን ሲያዞሩ ታዲያ ለነኝህ አባቶቻችን ተጠያቂው ማነው ስለሚደርስባቸውስ ድብደባ እና እንግልት ተጠያቂው ማነው? ስለምንስ ሁላችን በዝምታ ማየት መረጥን?

ነገ ታሪክን እና እውነተኛው ፈራጅ መድኅኒዓለም ክርስቶስ ፍርዱን ይሰጣል እውነተኛ አባቶቻችንን ሃይማኖታቸውን በመጠበቅ በፍጹም ተጋድሎአቸው ታሪክ ለዘለዓለም አይረሳቸውም፣ ነገር ግን መስሎ አዳሪዎችን፣ ታሪክ እና ትውልድ በማንነታቸው ያስታውሳቸዋል ብለን እናምናለን።
እግዚአብሔር አምላክ የእውነተኛ አባቶችን ጸሎት እና ልመና ሰምቶ ገዳመ ዋልድባን ከኢ-ዓማንዊያን ይታደግልን
ቅድስት ቤተክርስቲያንን በረደኤት ይጠብቅልን

No comments:

Post a Comment