Translate

Tuesday, September 25, 2012

በዋልድባ አምላከ ቅዱሳን ተዓምራቱን እያሳየ ነው


በዋልድባ አምላከ ቅዱሳን ተዓምራቱን እያሳየ ነው

የገዳማውያኑ የጸሎታቸው በረከት ይደርብን
  • ቅዱስ ራጉኤል በእለተ ቀኑ በዋልድባ ዛሬማ ወንዝ ላይ የተሰራውን ድልድይ በመብረቅ ተመቶ ጠራርጎ ወስዶታል
  • በአቲካ ወንዝ ላይ የተሰራው የሸንኮራ ማልማያ ግድብ እንዲሁ በዚሁ ቀን ፈራርሷል
  • የገዳማውያኑ እንግልት እንደቀጠለ ነው
  • ቤተክሕነት በዋልድባ ገዳም ለሚፈርሱት ቤተክርስቲያኖች ካሳ ጠይቋል ይባላል (የተረጋገጠ መልስ ማግኘት አልቻልንም)
ባለፉት ጥቂት ሳምትታት ውስጥ በዋልድባ ገዳም አካባቢ በሚሰራው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ የቻይናው ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ሥራውን ቀን ከሌሊት በመስራት ላይ እንደነበረ ከአካባቢው በደረሱን መረጃዎች ለመገንዘብ ችለናል። እንደሚታወቀው ከጥቂት ወራት በፊት በዋልድባ ገዳም አካባቢ ሊሰራ የታሰበውን ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ ሃላፊነቱን ወስዶ ሥራዎቹን ጀምሮ የነበረው የሱር ኮንስትራክሽን በተለያየ ጊዜ በአካባቢው በደረሰው ተአምራት ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል የዲሳይን ኢንጂነሩ በአጋጣሚ በመሞቱ፣ ጥቂት ሰራተኞች በአውሬ በመበላታቸው፣ የግድቡ ሥራ በጣም አዳጋች በሆነ መልኩ መስራት ባለመቻላቸው (ለግድብ ሥራ ጉድጓድ ቆፍረው በነጋታው ሲመለሱ ውሃ ሞልቶት ወይንም አፈር ተንዶ በመሞላቱ) ተደጋጋሚ ክስተቶች በመፈጸማቸው የሱር ኮንስትራክሽን ኮንትራቱን አፍርሶ መውጣቱ ይታወሳል። ኮንትራት አፍርሶ መውጣት (breach of contract) በብዙ ሚሊዮን ብር ቅጣት የሚያስቀጣ ቢሆንም ሱር ኮንስትራክሽን ባለቤቶቹም ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው የእግዚአብሔርን ተአምራት በዓይናቸው በማየታቸው ቅጣቱን ተቀጥተው ትተው ወጥተው ነበር።

ሱር ኮንስትራክሽን ጥሎ እንደወጣ ኢ-አማናውናኑን ጣዖት አምላኪዎቹን የቻይና ኮንስትራክሽን ካምፖኒዎችን በማስመጣት ሥራዎቹን እንዲቀጥሉ ማድረግ ተችሎ ነበር፤ በመጀመሪያው አካባቢ የአካባቢው ሰው በማንኛውም የቀን ሥራ ተቀጥሮ ለመስራት ፈቃደኛ ባለመገኘቱ፣ የአካባቢውም ነዋሪዎች በገዳሙ ላይ እንዲህ አይነት ሥራዎችን ሲሰሩ ከማየት ሞታችንን እንመርጣለን በማለት ከመንግሥት ወታደሮች ጋር ፍጥጫ መፈጠሩ የሚታወስ ነው፤ የመንግሥትም አካላት ምንም ዓይነት ግብግብ ከአካባቢው ነዋሪ ጋር እንዲፈጠር ባለመፈለግ፣ ቢፈጠር ሊመጣ የሚችለውን የከፋ አደጋ አስቀድሞ በመገመት በወቅቱ ሥራው ትንሽ ጋብ ለማድረግ ተችሎ ነበር። የአካባቢው ገበሬ መሐበራት ሥራቸውን እና ቤታቸውን ጥለው ወጥተው ስለነበር ለብዙ ጊዜ ያለሥራ መቆየት ባለመቻላቸው በመቀጠል የቻይናው ኮንስትራክሽን ሥራውን ላለፉት ጥቂት ወራት ሲሰራ ቆይቷል በዚህም በዛሬማ ወንዝ ላይ ትልቅ ድልድይ ወደ ገዳሙ ውስጥ logistics ሊያስገቡበት የሚችሉበት ድልድይ ተሰርቶ ነበር ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአቲካ ወንዝ አካባቢ መጠነኛ ግድብ ገድበው ለሸንኮራ ልማት ችግኝ ማፍያ የሚሆን ግድብ ተገድቦ ነበር በነዚህ ጥቂት ወራቶች ውስጥ ነገር ግን የፈጣሪ የአለም መድኃኒት ውጊያው ከባድ ነው ከፍጡራን ጋር ሰዎች ወይም መንግሥታት ጦርነት ገጥመው ወይንም ጎበዛዝት እርስ በርስ በጦር ገጎራዴ ሊጋጠሙ ይችላሉ በዚህም ጎበዝ የሆነው መንግሥት ወይም የጎበዝ አለቃ ያሸንፋል ተሸናፊውም መሸነፉን በጸጋ ተቀብሎ ይሄዳል። ነገር ግን የሀገራችን የኢትዮጵያ መንግሥት ወይንም የስኳር ልማት ሚኒስቴር በጉልበት ሰውን እንደሚያሸንፉ፣ በመሳሪያ ሃይል ሰውን እንደሚያስገድዱ፣ በወገናቸው ብዛት ወይም የስልጣናቸው መጠን እንደሚያሸንፉበት ሳይሆን ተግዳሮቱ ሰማይና ምድርን ከዘረጋው ከፈጣሪ ጋር መሆኑ እጅግ ከባድ ሊያደርገው እንደሚችል የተገነዘቡት አይመስለንም። በመጽሐፍ እንደተገለጸው ፈርዖን ልቡ ደንድኖ የፈጣሪን ትዕዛዝ ባለመቀበሉ 10 ተዓመራትን በግብጽ ምድር ላይ ሊታይ ችሏል ጓጉንቸር ከሰማይ ዘንቧል፣ ቅማል ምድሪቱን ወርሷታል፣ የደም ዶፍ ወርዶባቸዋል ያም አልበቃ ብሎ የግብጽን የበኩር ልጆች በመቅሰፍት ተመተዋል በመጨረሻ ግን የእግዚአብሔር ሃይል በልጦ እስራኤላውያን ወደ ተሰፋይቱ ምድር ለመሄድ በመሪያቸው በሙሴ አማካኝነት ከግብጽ 400 ዘመን ባርነት ወጥተው ነበር። ዛሬ በኛ ሀገር እንዴት እነዚህ በቅዱሳን መጽሐፍት የተጻፉ ታሪኮች እና የእግዚአብሔርን ሃያልነት የሚያስገነዝቡ ትምህርቶች ለመማር አለመቻላችን እስከ አሁን የሀገር መዋዕለ ንዋያት እና ሃብት ዝም ተብሎ ለጎርፍ እና ለመቅሰፍት መዳረጋቸው ያሳዝነናል።

ነገሩ እንዲህ ነው ባለፈው በጳጉሜ ፫ ቀን ፳፻፬ ዓ. ም. መብረቅ ቀላቅሎ የወረደው ዝናብ በዋልድባ ገዳም በቻይና ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ላለፉት ወራት ሲገነቡ የነበሩ ግንባታዎች በሙሉ ለታሪክ እንኳን ምንም ሳይቀር በመብረቅ እና የዝናም መዓት ተመተው ድራሻቸው መጥፋታቸው ለአምላከ ቅዱሳን መድኅኒዓለም ክርስቶስ ምን ይሳንሃል ያሰኘ ክስተት ነበር፤ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው ” . . .ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን የሰጣል ይላል . . .” ስለዚህ ዛሬም እግዚአብሔር ለተገፉት፣ ለተገረፉት፣ ለተደበደቡት ገዳማውያን አባቶቻችን ሃይሉን ሰጥቷቸው በጸሎታቸው ሃይል እንኪሁም በአምላካችን ቸርነት በዛሬማ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ በመብረቅ ለወሬ እንዳይመች ሆኖ በጥፋቱ በአቲካ ወንዝ ለሸንኮራ ማፍያ የተገደበው ግድብ እንዲሁ በጎርፍ ሙላት ሙሉ ለሙሉ ከነሸንኮራ ችግኝ ማፍሊያ እና የተለያዩ ከባድ እና ቀላል machinery በአንድነት በአንድ ጀምበር ድምጥማቱ መጥፋቱ “የአምላክ ሥራ መርቀቁ” የሚያስብል ሆኖ አልፏል ከዚህም ጊዜ ጀምሮ በምንም መልኩ የቻይናው የኢ-አማናውያኑ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ሊያንሰራራ ባለመቻሉ እስከ አሁኗ ቀን ድረስ ሥራው ሊጀመር አልቻለም ቢጀምሩም እንደገና ከዜሮ መጀመራቸው የማይቀር በመሆኑ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ይልቁንም አቶ አባይ ጸሐዬ በሚመሩት የሥኳር ልማት መስሪያ ቤት ውስጥ የተለያዩ ሃሳቦች እየተነሱና በዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎችም ሃሳባቸው እየተከፋፈለ መምጣኑን ሰምተናል።

የዚህ ዝግጅት ክፍል እንደሚያምነው “ተግዳሮቱ ከፈጣሪ ጋር በመሆኑ ይቅር ባይ ነን፤ የፈርዖንን ልብ የያዘ ደግሞ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል በዓይናችን የምናየውን ማየት ከተሳነን” ምከረው ምከረው፤ አልመለስ ካለ መከራ ይምከረው የሚለውን የአባቶቻችንን አባባል እኛም ለመድገም እንገደዳለን።

ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ በዚሁ በዋልድባ ገዳም አካባቢ እግዚአብሔር መዓቱን አውርዶ እነዚህ ግድብ እና ድልድይ ከፈረሱ በኃላ የአካባቢው ጸጥታ ሰዎች በገዳሙ ውስጥ በመግባት አባቶችን ማወክ እና መደብደብ ጀምረው “የእናንተ መተት ነው” በማለት ሲያውኩ አንድ ስሙ ክንፈ ገብርኤል የተባለ መናኝ “የግድቡ እና የድልድዩ አይግረማችሁ፣ ይህንን ገዳም ለማፍረስ የተነሳ ሥራው ብቻ ሳይሆን እራሱ ይፈርሳል” በማለት በሃለቃል ለታጣቂዎቹ ነግሯቸው፣ ታጣቂዎቹም በአጸፋው መናኙን ክፉኛ ደብድበውት ክፉኛ በመቁሰሉ ማይገባ በሚባል ከገዳሙ የሰባት ሰዓት መንገድ የሆነ ጤና ጣቢያ ተወስዶ በህክምና ሲረዳ መቆየቱን እና በአሁን ሰዓት በማገገም ላይ እንደሚገኝ ከምንጮቻችን ለመረዳት ችለናል።
ዋልድባ ገዳም በመድኅኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የድንጋይ ቆብ ቀርጾ ባመነኮሳቸው መነኮሳት የተገደመ ገዳም እንደመሆኑ መጠን ችግሩ ምን ቢጸና፣ ምን ያህል አባቶቻችን መነኮሳት እና እናቶቻችን መነኮሳይት ቢንገላቱ እና ቢሰደዱ፣ በገዳሙ ውስጥ የሰው ዘር እንኳ ቢጠፋ በፍጹም ልንገነዘበው የሚገባን የገዳሙ መስራች እና የቤተክርስቲያናችን ጉልላቷ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ሊተዋት አይችልም መንግሥታት፣ ጎበዛዝት፣ ሃይለኞች ፣ በለጊዜዎች እና ባለመሣሪዎች በሙሉ ሰማይና ምድርም ሳይቀሩ ያልፋሉ ነገር ግን ቤተክርስቲያን እና የፈጣሪያችን ቃሉ ለዘልዓለም ህያው ሆነው እስከ ዓርያም ይኖራሉ። ዋልድባም ከነሙሉ ክብሩ በመድኅኒታችን ጠባቂነት እና ረደኤት ከትውልድ ትውልድ መተላለፉ ጥርጥር የሌለው እውነታ ነው።
መድኅኒዓለም ክርስቶስ ዘወትር በተዓምራቱ እና በቸርነቱ ያልተለየን የአባቶቻችን አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን
ቸር እንሰንብት

No comments:

Post a Comment