Translate

Tuesday, September 11, 2012

በኢትዮጵያ የታሰሩት ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች፤እንዲሁም ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና ሂሩት ክፍሌ ተፈቱ

ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያ ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፔርሰን ለተባሉት ሁለቱ ዊድናውያን ጋዜጠኞች ይቅርታ ማድረጓን አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን አስታወቁ።
ከስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች በተጨማሪ የ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ እና በነ ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ የተከሰሰች ሂሩት ክፍሌ በምህረት ተፈትተዋል።
አሶሲየትድ ፕሬስ ባለስልጣኑን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የተፈችዎቹ ይቅርታ የጸደቀው፤ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ መለስ ዜናዊ ነው ።
ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፐርሰን ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በኦጋዴ ክልል እየተፈጸመ ነው የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመቅረጽ ከኦጋዴ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር( ኦብነግ) ተዋጊዎች ጋር በመሆን ወደ ክልሉ ለመግባት ሲሞክሩ በኢትዮጵያ ወታደሮች መያዛቸው ይታወሳል።
ከዚያም የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው እያንዳንዳቸው በ11 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
ጋዜጠኞቹ መታሰራቸውን ተከትሎ ይቅርታ የጠየቁ ቢሆንም፤የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን፦” አንድ እስረኛ ይቅርታ ስለጠየቀ ብቻ፤ በህጉ መሰረት ለይቅርታ ማሟላት የሚገባውን ግዴታዎች ሳያሟላ እንዲሁ አይፈታም” በማለት ጥያቄያቸው በቶሎ ተቀባይነት እንደማያገኝ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል መናገራቸው ይታወሳል።
በመሆኑም ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ላለፈው አንድ ዓመት በቃሊቲ እስር ቤት አሳልፈዋል።
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬም በፃፋቸው ጽሁፎቹ፤ ሂሩት ክፍሌ ደግሞ ያለምንም ምክንያት የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸውና ተፈርዶባቸው ላለፈው ዓመት በእስር ቆይተዋል።
አዲስን ዓመት አስመልክቶ 1ሺህ 900 እስረኞች በምህረት እንደሚለቀቁ የተናገሩ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን፤ ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፔርሰን ፤እንዲሁም ውብሸት እና ሂሩት በምህረት ከሚፈቱት ውስጥ መካተታቸውን ገልጸዋል።
ተፈችዎቹ ምህረት ያገኙት፤ይቅርታ በመጠየቃቸው እንዲሁም በእስር ቤት ቆይታቸው መልካም ምግባር በማሳየታቸው ነው ብለዋል-ባለስልጣኑ።
በመሆኑም ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞችና እነ ውብሸት ፤አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ይቅርታ ከተደረገላቸው ሌሎች እስረኞች ጋር ዛሬ ከቀትር በሁዋላ ተፈተዋል።
ይሁንና ጋዜጣ እና ድረ-ገጽ ላይ በመፃፋቸው ብቻ በሽብርተኝነት ተወንጅለው በእስር ቤት ስለሚገኙት ሌሎች ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኞች ምንም የተባለ ነገር የለም።
ከነዚህም መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ይገኙበታል።
ምርጫ 97 ትን ተከትሎ አምስት የ አሜሪካ ድምጽ የ አማርኛ ፕሮግራም ጋዜጠኞችን ጨምሮ በ 20 ጋዜጠኞች ላይ “መንግስትን ለመገልበጥ የማሴር” ክስ መስርቶ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት፤ በ አሜሪካ መንግስት ተጽዕኖ የቪኦኤ ጋዜጠኞችን ክስ ወዲያው ውድቅ ሲያደርግ፤ ሌሎቹ ለሁለት ዓመታት በእስር መማቀቃቸው አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment