Translate

Wednesday, September 19, 2012

በመጪው አርብ ለሚካሄደው የሙስሊሞች ተቃውሞ ወረቀቶች እየተበተኑ ነው


ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ መንግሥት የኢትዮጵያ ሙስሊም ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትንና የመስኪድ ኡላማዎችን የክስ ሂደት በመጪው ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም ፒያሳ በሚገኘው በአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለማድረግ ጊዜ ቀጠሮ መያዙ መታወቁን ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች  በመጪው የዓርብ /ጁምዓ/ ጸሎት በየመስኪዱ የተጠናከረ የተቃውሞ ትይንት ለማድረግ ዝግጅት ጀምረዋል።
ባለፈው ሳምንት ህዝበ ሙስሊሙ አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚገኝበትን ጊዮርጊስ አካባቢን በማጥለቅለቁ በመንግሥት ትዕዛዝ ችሎቱ እንዲቋረጥ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን በቀጣይ በዝግ ችሎት እንዲሆን መወሰኑን ዘጋቢያችን አረጋግጧል፡፡
ካለፈው ሣምንት ጀምሮ የኢህአዴግ መንግሥት ሙስሊም ካድሬዎች በየክፍለ ከተማው፣ በየወረዳው እና በእየ-ሙስሊም ቤት በመዞር በግዳጅ በወረዳ  የሚደረገው የመጅሊስ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ካርድ እንዲያወጡ እያስገደዱ ነው ሲሉ ለዘጋቢያችን የተናገሩት ሸህ አህመድ  እኔም ያለፍላጎቴ የምርጫ ካርድ አስወጥተውኛል ነገር ግን  አልመርጥም ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደሴ  ሙስሊም ወጣቶች  ከ 20 ሺህ በላይ የተቃውሞ ወረቀቶችን መበተናቸው ታውቋል።

-የአካባቢው ባለስልጣናት የተበተኑትን  ወረቀቶች ሌሊቱን በባትሪ እየፈለጉ ሲለቅሙ ማደራቸው ታውቋል።
በስፍራው የሚገኘው የኢሳት ወኪል እንዳጠናቀረው ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ሙስሊሞች ከጀመሩት መብት የማስከበር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የደሴ ሙስሊሙች፦” ዲናችንን ለመጠበቅና መብታችንን ለማስከበር እሰከመጨረሻው እንታገላለን” በሚል መርህ  መንቀሳቀስ ከጀመሩ ወራቶች ተቆጥረዋል።
በአሁኑ ጊዜ የብዙሀኑ ሙስሊም አስተባባሪ ኮሚቴዎች ቢታሰሩም በመላው ሀገሪቱ ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተባለው መሰረት የደሴ ሙስሊም ወጣቶችና ነዋሪዎች ከፍ ያለ የትግል እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው፡፡
በዚህ መሰረት ዛሬ ሌሊት ከተማውን በሙሉ በአራዳ፣በሻርፕ ተራ፤በዳውዶ፤በሮቢት፤በሰኞ ገበያ፤በቢለን፤ በቧንቧውሀ፤ በመናፈሻ፤በሸዋበር፤በአሬራ እና በሌሎች በርከታ የከተማዋ ሰፈሮች እንዲሁም  በአስፋልት እና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ ከ25 ሺ በላይ የትግል ጥሪ ወረቀቶችን  መበተናቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል።
ወጣቶቹ ከበተኗቸው ወረቀቶች ባሻገርም  በየኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እና በየግድግዳው ላይ  በርካታ ወረቀቶችን መለጠፋቸው ተመልክቷል።
በተበተኑትና በተለጠፉት ወረቀቶቹ ላይ ከተጻፉት ጹሁፎች መካከል፦“መብት መጠየቅ የሚያሳስር ከሆነ ፤አይደለም ለመታሰር ለመሰዋት ዝግጁ ነን!፣“ዲኔ ተደፍሮ ከምኖር ፤ እኔ ሞቼ ዲኔ ይኑርልኝ!፣የሚደርስብንን ህገወጥ ድብደባ እና እስራት ለመቀበል ዝግጁ ነን፣በቀበሌ፤ ካድሬ እንጂ የሀይማኖት መሪ አይመረጥም!፣መስከረም 27 ይካሄዳል በተባለው ህገወጥ ምርጫ ላይ አንሳተፍም!፤ ለምርጫው ካርድም አንወስድም!”የሚሉት ይገኙበታል።
ወረቀቱ የተበተነው ትናንት ማክሰኞ ከምሽቱ 2፡30 ጀምሮ ሲሆን፤ ወረቀቶቹን በመበተኑ እንቅስቃሴ እጅግ በርካታ የደሴ ወጣቶች መሳተፋቸው ታውቋል።
ወጣቶቹ በአንድ በኩል ወረቀቶችን  ሲበትኑ፤ በሌላ በኩል የተበተነውን ወረቀት የሚለቅሙ ካድሬዎችና ባለስልጣናት  መስተዋላቸውንም የዘጋቢያችን መረጃ ያመለክታል።
ወረቀቱን አጎንብሰው በባትሪ ሲለቅሙ ከነበሩት መካከል ፤የፖሊስ ዋና አዛዦች እና የከተማው መስተዳድር ባለስልጣናት እንደነበሩበት ወኪላችን ጠቁሟል።
“ህዝብን ለማገልገል ተግተው የማይሠሩ አምባገነኖች ሁሉ ዛሬ የህዝብን ድምጽ ለማፈን  ግን ሌሊቱን በባትሪ ወረቀት ሲለቅሙ አደሩ፤በከተማው በሙሉ የተበተነውን  ከ 25 ሺህ በላይ ወረቀት መልቀም ምን ያህል አድካሚ መሆኑን አስቡት። እነሱ ግን ሌሊቱን ሙሉ  አንድም ሳያስቀሩ ለቀሙት፤ ይህ ድምጻችንን ለማፈን ምን ያህል ቆርጠው እንደተነሱ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡” ብለዋል- የደሴ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያዬት።
“መንግሰት ድምጻችንን ለማፈን ይሄን ያህል ቢለፋም ፤ድካሙ “ከንቱ ልፋት” ከመሆን ውጭ ምንም የለውም”ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ሙስሊሙ ህበረተሰብ መብቱን ለማስከበር ወይም መስዕዋት  ለመሆን ቆርጦ መነሳቱን ሊያውቁ ይገባል”ብለዋል።
በደሴ ከተማ የሚገኙ በርካታ መስኪዶች አሁንም ድረስ በፖሊሶች ይጠበቃሉ። ህዝቡ በኢህአዴግ ላይ ያለው ጥላቻ እየጨመረ በመምጣቱም በመጪው አርብ ሙስሊሙ በእየመስኪዱ ጠንካራ ተቃውሞ እንደሚያሰማ ጉዳዩን በቅርበት የምትከታተለው ምንጫችን ገልጣለች::
መስከረም 27 ይካሄዳል በተባለው ህገ ወጥ ምርጫ ላይም እንደማይሳተፉ ለማሳወቅ የፊርማ ማሰባሰብ ሂደት መጀመራቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ የፊታችን አርብ (ጁምዓ)  በነቅስ ወጥተን ተቃውሟችንን  ለማሰማት ዕለቱን  በጉጉት እየጠበቅን ነው”ብለዋል።

No comments:

Post a Comment