Translate

Wednesday, September 19, 2012

በቁም እስር ላይ የነበሩ ሶስት ጄኔራሎች ተለቀቁ


ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ ዜናዊ መታመምን ተከትሎ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ መሞታቸው ከተረጋገጠና ከተገለጸ በኋላም የተባባሰ ደረጃ ላይ መድረሱ የኢህአዴግ የዜና ምንጮቻችን ገለጹ፡፡
በዚህ ክፍፍል ላይ እስካሁን ድረስ አቋማቸውን በግልጽ ካላሳዩት የሀገሪቱ ከፍተኛ ጄነራሎች ውስጥ የተወሰኑት እንደተቃወሙትም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ተቃውሟቸውን በይፋ ካሰሙት ውስጥ ሦስት ጀነራሎች ከሰኞ ጠዋት ጀምሮ በቢሯቸው የቁም እስረኛ ተደርገው ነበር ያሉን ታማኝ ምንጮቻችን ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከቁም እሥር መፈታታቸውን  ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሁለት የህወሓት እና አንድ የብአዴን ጀኔራሎች በቁም እሥር እንዲውሉ የተደረጉት በቅርቡ የተደረገውን የማዕረግ እድገት ይቃወማሉ በሚሉና ሌሎች ተጓዳኝ ምክንያት እንደሆነ የጠቆሙን ምንጮቻችን ለደህንነታቸው በመስጋት ሥማቸውን ለመግለጽ  ለጊዜው ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ህይወታቸው ማለፉ በመንግሥት ከተገለጸ በኋላ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከፍተኛ ጥርጣሬና ስጋት የተፈጠረ ሲሆን ይህንን ለማረጋጋት በሚመስል መልኩ የማዕረግ እድገት ለከፍተኛ የህወሓት መኮንኖች መሰጠቱ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም የሆኑት ጄነራል ሳሞራ የኑስ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው የተሰማ ሲሆን እንደ ምክንያትም ያቀረቡት በቃኝ ደከመኝ የሚል መሆኑን ታማኝ ምንጫችን አክለው ገልጠዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በኢህአዴግ ሊቃነ-መናብርት ምርጫ ድምጽ ማጣቱ፤ በድርጅቱ ውስጥ ተቃውሞ መፍጠሩ ተሰማ።
 ባለፈው ሳምንት ኢህአዴግ ባካሄደው የሊቃነ-መናብርት ምርጫ ኦህዴድ ያቀረባቸው ዕጩ ድምጽ ተነፍገው መውደቃቸው የድርጅቱን የተወሰኑ አባላት አስኮርፏል።
 በመሆኑም  የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ አባላት በ አስቸኳይ  በአዲስ አበባ በዝግ ስብሰባ እንዲቀመጡ መደረጋቸው ታውቋል።
 ሰንደቅ ሳምንታዊ ጋዜጣ እንዳለው፤ የኦህዴድ የስራ አስፈፃሚ አባላት ስብሰባ ከኢህአዴግ የም/ቤት ስብሰባ በኋላ ወዲያውኑ እንዲካሄድ መደረጉ፤ የተለያዩ ወገኖችን ትኩረት ስቧል።
ኢህአዴግ ፤ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ምትክ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝንና አቶ ደመቀ መኮንንን በሊቀመንበርነትና በምክትል ሊቀመንበርነት ከመረጠ በኋላ ነው የኦህዴድ የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ወዲያውኑ የተጀመረው።
 ስብሰባው  በተለይ ከኢህአዴግ የከፍተኛ አመራር መተካካት ጋር በተያያዘ በግንባሩ ውስጥ ኦህዴድ ተገቢውን ቦታ አላገኘም የሚሉ ብዥታዎችን ለማጥራት ነው ተብሏል።
ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳለው፦ኢህአዴግ የአመራር መተካካቱን ካከናወነ በኋላ፤ “ኦህዴድ በግንባሩ ውስጥ ተገቢውን ቦታ አላገኘም” በሚል የተሳሳቱ ስሜቶች መፈጠራቸው እንደማይቀር ታምኖበት በአስቸኳይ ሥራ አስፈፃሚው ስብሰባ እንዲቀመጥ ተደርጓል። 
የሰንደቅ ምንጮች አክለውም ይህ አስተሳሰብ በቀጣይ የድርጅቱን ጥንካሬና የክልሉን ልማት እንዳይጎዳ እንዲሁም  አሉባልታውን ለመስበር ታስቦ የተደረገ ስብሰባ መሆኑንም ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ቀደም ሲል የጤና መጓደል ቢገጥማቸውም፤ በአሁኑ ወቅት የጤናቸው ሁኔታ መሻሻል በማሳየቱ በ እርሳቸው ቦታ ሌላ ምደባ እንደማይኖር ተመልክቷል።
በሌላ በኩል ከጋዜጣው ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረጉት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትርና የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምዖን ፦”ህወሀት የታገለው የህወሀትን ስርወ-መንግስት ለመፍጠር አይደለም”ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ በረከት ይህን ያሉት በቃለ-ምልልሱ ፦” አሁን ከፊት እየመጣ ያለውን አመራር በማዬት ፤ቀደም ሲል የነበረው የህወሀት የበላይነት ቀንሷል የሚል ፍራቻ እየታዬ ነው ይባላል” በማለት  ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሢሰጡ ነው።
“ህወሀት የታገለው ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንጂ፤የህወሀትን ስርወ-መንግስት ለመፍጠር አይደለም”ነው ያሉት አቶ በረከት። 
ኢሳት በያዝነው ሳምንት መጨረሻ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን በይፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ለማድረግ እቅድ መውጣቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። አቶ በረከት ፓርላማው በመስከረም ወር መጨረሻ ተሰብስቦ ሹመቱን ያጸድቃል ብለው ከተናገሩ በሁዋላ ቃላቸውን አጥፈው የአስቸኳይ ስብሰባ  እንዲጠራ የጠየቁት በተለይ የምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትሩን ሹመት በተመለከተ ሊነሳ የሚችለውን ያልተጠበቀ ተቃውሞ በመፍራት መሆኑን ምንጫችን ገልጠዋል።  ምንም እንኳ እስካሁን ከኦህዴድና እና ከህወሀት ይፋ የወጣ ተቃውሞ ባይቀርቡም፣ ከ6 ወራት በሁዋላ በሚኖረው የኢህአዴግ ጉባኤ ህወሀት ቀድሞ የነበረውን ቦታ መልሶ ለመያዝ ፣ ኦህዴድ ደግሞ የደረሰበትን የፖለቲካ ኪሳራ ለማካካስ ከፍተኛ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ምንጫችን ገልጠዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ህወሀት ሊቀመንበር መምረጡን ዛሬ ይፋ አድርጓል:: አቶ አባይ ወልዱን አቶ  መለስ ዜናዊን በመተካካት ሊቀመንበር ሆነዋል:: የደህንነት ሹሙ አቶ  ደብረ ፅዬን ገ/ ሚካኤል ደግሞ  ምክትል ሊቀመንበር አድርጓ መርጦል::  ኢሳት ከቀናት በፊት አቶ  አባይ ወልዱን አቶ  መለስ ዜናዊን ተክተው መመረጣቸውን  የውስጥ ምንጮችን ጠቅሶ  መዘገቡ ይታወሳል::

No comments:

Post a Comment