በስዬ አብረሃ
የአቶ መለስ ሕልፈተ ሕይወት ይፋ ሆኖ አስከሬኑ ቦሌ ደረሰ ሲባል የአዲስ አበባ ሕዝብ በድንጤና በሐዘን፣ የክረምቱ ዶፍ እየወረደበት አስከሬኑን ቤተ መንግሥቱ ድረስ አድርሶታል፡፡
አስከሬኑ ከገባ ከአሥራ ሁለት ቀን በኋላ ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብም እርሙን አውጥቷል፡፡ በአቶ መለስ ሕልፈተ ሞት የተሰማኝን ሐዘን ቀደም ብዬ የገለጽኩ ቢሆንም፣ አሁንም ለቤተሰቡ መጽናናትን እመኛለሁ፤ ፈጣሪ ነፍሱን በይቅርታ እንዲቀበለውም እመኝለታለሁ፡፡
እንግዲህ ከኢሕአዴግ መሪዎች የሚጠበቀው ላልተመለሱት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሕልፈቱን ምክንያት ግልጽ ማድረግ ይሆናል፡፡
እንግዲህ ከኢሕአዴግ መሪዎች የሚጠበቀው ላልተመለሱት ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሕልፈቱን ምክንያት ግልጽ ማድረግ ይሆናል፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት የገዛ መሪው መታመምን ይፋ ያደረገው በሁኔታዎች አስገዳጅነት የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ለአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ በመጡ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ከተናገሩ በኋላ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ያም ሆኖ ሕክምናው የሚሰጥበትን አገርና ሆስፒታል ሳይቀር አንገልጽም ማለታቸውን ያስታውሷል፡፡ እየተሻለው ነው በቅርብ ይመለሳል እየተባለ ለበርካታ ሳምንታት ሲነገር ቆይቶ በድንገት ለዚያውም በኢንፌክሽን አረፈ ተባለ፡፡
የአቶ መለስ ሕመም ምን መሆኑ አለመታወቁና ደህና ነው ሲባል አረፈ መባሉ ነገሩን ለብዙ መላምቶች ክፍት አድርጎታል፡፡ ለሕዝብ በግልጽ ባልተቀመጠ ሁኔታ የአንድ አገር መሪ አረፈ፣ ለዚያውም በሌላ አገር አረፈ ሲባል ብዙ ጥያቄዎች ሊያጭር እንደሚችል በመገንዘብ የኢሕአዴግ መሪዎች እውነታውን ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው የሕወሓት/ኢሕአዴግ ጉባዔ ለተተኪ አስረክቦ እርሱ ገለል ይላል ሲባል ነበር፡፡ እርሱ እለቃለሁ እያለ ቀሪዎቹ የኢሕአዴግ መሪዎች አይሆንም ብለው ጫና በመፍጠራቸው ምክንያት እንዲቆይ መገደዱ ተነግሮናል፡፡ አቶ መለስ መታመሙን ካወቀ ብዙ እንደቆየና ረጅም ዕረፍት እንደሚያስፈልገው ሰሞኑ ይሰጡ ከነበሩት መግለጫዎች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ መድከሙንና መታመሙን እያወቁ፣ አንተ እረፍ ከዚህ በኋላ ያለውን እኛ ማስቀጠል እንችላለን ማለት ባለመቻላቸው እስከመጨረሻ ሰዓት እንዲቆይ አድርገውታል፡፡
ይህ እየታወቀ የአቶ መለስን ሕልፈተ ሕይወት ተከትሎ ነገሮች በነበሩበት መልኩ ይቀጥላሉ የሚለወጥ ነገር አይኖርም ተብሏል፡፡ እርሱ በሕይወት እያለ የእርሱ ምክር ከጎናቸው እያለ ‹‹እኛ እንሞክረው›› ማለቱን ያልተቻላቸው ሰዎች አሁን እርሱ በሌለበት ነገሮችን እንደድሮው እናስቀጥላለን ማለታቸው ያስገርማል፡፡ ከጥንት ከጥዋቱ ጀምሮ ‹‹የራዕዩ አመንጪ››፣ ‹‹ቀያሹ ዋና አስፈጻሚው›› እሱ እንደነበረ ከገለጹልንና እውነቱ ይህ መሆኑን ካመኑ ዘንዳ እርሱ በሌለበት እኛ እንችለዋለን፣ ነገሮች በነበሩበት ይቀጥላሉ ማለታቸው ተዓማኒነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይልቁንስ የተጀመሩትን በጎ ጅማሮዎች አጎልብቶ ዳር ለማድረስ የሚያስችል፣ የጎደለቱን የሚያሟላና የኢትዮጵያን ሕዝብ ልቦና የሚዳብስ መንገድ መቀየስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያ እንኳን እንዳይሰማ የሚከለከለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ መሆኑን፣ የታላቅ ወግና ሥርዓት ባለቤት መሆኑን በአቶ መለስ ሕልፈተ ሕይወት አሳይቶአል፡፡ ይህን ያደረገው ለሕይወትና ለሕልፈተ ሕይወት ትልቅ ሥፍራ የመስጠትን፣ በሐዘን ወቅት በጎውን እንጂ መጥፎውን ማውሳት ያለመፈለግን የመሰለ ታላቅ ወግና ሥርዓት ያለው ሕዝብ ስለሆነ እንጂ፣ በኢሕአዴግና በአቶ መለስ አገዛዝ በደል ስላልተፈጸመበት ወይም ረስቶት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ቀሪዎቹ የኢሕአዴግ መሪዎች መፈክሮች እንዲወጡ በማድረግ፣ በየቀበሌው ድንኳን እንዲተከልና ሰው ጥቁር ልብስ እንዲለብስ መመርያ በማሰራጨት የሕዝቡን ሐዘን፣ ድንጋጤና ታላቁን የኢትዮጵያውያን ወግና ሥርዓት ወደ የተደራጀና የተራዘመ የፖለቲካ ዘመቻ ለመለወጥ ሞክረዋል፡፡
በአቶ መለስ ዜና ዕረፍት የታየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐዘንና ድንጋጤ ኢትዮጵያውያን በአደጋና በፈተና ጊዜ በአንድነት እንደሚቆሙ ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው፡፡ እስካሁን የተሠራውን በጎና ክፉው ሥራ እንደ የጋራ ታሪካችን ተቀብለንና ወደፊት በጋራ ቆመን የአገራችንን የዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ግንባታ እንድናጠናክር መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን ያመለክት እንደሆነ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንድ ፓርቲ አገዛዝ ይሁንታ እንደሰጠ ተደርጎ መተርጎም አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሕአዴግ ይግዛኝ ብሎ 99 በመቶ ድጋፍ አልሰጠም፡፡ ጋዜጠኞችና የኢሕአዴግን አገዛዝ የተቃወሙ ፖለቲከኞች በሽብርተኝነት እንዲታሰሩ ይሁንታ አልሰጠም፤ አይሰጥምም፡፡
የኢሕአዴግ መሪዎችን የኢትዮጵያውያንን ሐዘን በዚህ መተርጎማቸውና ነገሩን ለመጪው አገዛዛቸው ማጠናከርያ ለመጠቀም መሞከራቸው፣ ለዚህ ታላቅ ሕዝብ ያላቸው ሚዛን ምን እንደሚመስል ያመለክታል፡፡ ይህ ደግሞ ጤነኛ አመራርን አያመለክትም፡፡
የአቶ መለስ ማለፍ ሲታወቅ መወሰድ የነበረበት የመጀመርያ ዕርምጃ ተተኪውን ሰው መሰየምና ማስቀመጥ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የቀብሩን ዝግጅት አያስተጓጉልም፡፡ ማድረጉ ደግሞ የአገሬውን ሥነ ልቦና ያረጋጋል፡፡ ኢኮኖሚውን ያረጋጋል፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም መረጋጋትን ያመለክታል፡፡ ሆኖም አቶ መለስ ካለፈ ከሳምንታት በኋላም ይህንን ማድረግ አልተቻላቸውም፡፡ ይህም ጤነኛ አመራርን አያመለክትም፡፡
ነፍሱን ይማረውና ከእንግዲህ አቶ መለስ አርፏል፤ አልፏል፡፡ ከዚህ በኋላ ኢሕአዴግ የሚያቋቁመው መንግሥት የአቶ ኃይለ ማርያም ወይም ከሌሎቹ የአንዱ ሊሆን ይችላል፤ የአቶ መለስ ግን ሊሆን አይችልም፡፡ ኢሕአዴግ ማንንም ቢሾምም የአቶ መለስን ሥፍራ ሊተካ አይችልም፡፡ ለመለስ አገዛዝ የሠራው ለእነርሱም አይሠራም፡፡ ተወደደም ተጠላም የምናውቀው ኢሕአዴግ አይኖርም፡፡ ሁኔታ ተቀይሮአል፤ ‹‹ስታተስ ኮው›› ላይ አይደለንም፡፡ ለውጥ እንዳለና አንድምታው ግዙፍ እንደሆነ ኢሕአዴግ ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሃያ ዓመት ያገኘውን ተነፃፃሪ ሰላምና ይብዛም ይነስ በዚህ ወቅት ያፈራቸውን ቁሳዊ እሴቶች ሊያጣ አይፈልግም፡፡ በማያሻማ መልኩ ሁኔታዎች ለሰላማዊና ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲመቻቹለት ይፈልጋል፡፡
ለውጥ በመጣ ቁጠር ትርምስና መናጋትን አይቶአልና፡፡ አሁንስ ምን ይመጣብን ይሆን የሚል ሥጋት እንዳለበት መገንዘብ ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ ለዚህ ሁኔታ ከተለመደው የእኛ እናውቅልሃለን ፖለቲካ በተለየ መንገድ ማሰብ አለበት፡፡ የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎችም እውነታውን በጥሞና መመርመር ይገባቸዋል፡፡ አለ የሚሉትን የአቶ መለስን ‹‹ሌጋሲ›› መፈክርና ፎቶ በማንጠልጠል ወይም ዜማ በማዜም ሊያስጠብቁት አይቻላቸውም፡፡ ሁሉን እናስቀጥላለን ብሎ መሞከር ሁሉንም ማጣት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ነገሩ የቁጭትና የእልህ ሳይሆን የብልህነትና የአስተዋይነት ጉዳይ ነው፡፡ ለውጥ መኖሩን መገንዘብና ይህንን የተገነዘበ ሁሉንም የሚያሳትፍ መንገድ መቀየስ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡
እንደ አያያዛችን ይህ ሁኔታ መጥፎም ጥሩም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢሕአዴግ እርስ በርስ መስማማት አቅቶት ትርምስ ውስጥ ቢገባ ወይም ለአዲሱ ሁኔታ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ቢያቅተው፣ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ መጠቀምዋና መጠናከርዋ የሚያሰጋቸው ኃይሎች አጋጣሚው አገኘን ብለው በውስጣዊ ድክመቶቻችን ውስጥ መጫወት ቢጀምሩ፣ አገራችን ሕዝቡን እያሳሰበው ካለው ችግር ውስጥ ልትገባ እንደምትችል መገመትም ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መናጋት ከኢትዮጵያ ድንበር የዘለለ አካባቢውን በጠቅላላ ሊነካ እንደሚችልም መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህን ማስቀረት የሚቻለው ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር አስፈላጊ የሆኑትን ዕርምጃዎች በመውሰድ በአገራችን ውስጥ ሲጠራቀም የቆየውን ውጥረትን ማርገብ ሲቻል ብቻ ነው፡፡
ለውጡንና የአንድምታው ግዙፍነትን መገንዘብ ያለባቸው ተቃዋሚዎችና ዳያስፖራውም ጭምር ናቸው፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ብቅ ያለውን ለውጥ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ የተፈጠረ አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ለውጡን በዚህ እይታ እንቀበለው ካልን መንገዱ የይቅርታ፣ የመመካከር፣ የፍቅርና የአንድነት መንገድ ብቻ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ደጋፊና የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ፣ የዚህና የዚያ ብሔር ተወላጅ ወይም የዚያና የዚህ ሃይማኖት ተከታይ ሳንባባል ሁላችንም ለአገራችን ድል በጋራ መሥራትን ስንቀበል ነው፡፡
አንዳንድ ወገኖች ከታላቁ የሕዝባችንና የአገራችን ወግና ሥርዓት ወጣ ባለ ሁኔታ በሰው ሞት መደሰት ታይቶባቸዋል፡፡ የተፈጸሙ በደሎች እንዳሉ ሆነው ለውጡን የምንቀበለው በዚህ መንፈስ አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ጥቂት ቢሆኑም በኢትዮጵያውያን መካከል ሊፈጠር የሚችለውን የአንድነት፣ የእርቅና የፍቅር መንፈስ በመበረዝ ረገድ ከቁጥራቸው የገዘፈ አጥፊ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ የኢሕአዴግን ስህተቶች እንደምንተች ሁሉ እነዚህንም ስህተታቸውን ማሳየት የሁሉም ወገን ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡
ከዚህ አኳያ በተቃዋሚዎችና በዳያስፖራው በኩል ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ነጥቦችን ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡
1. አሁንም በውይይትና በምክክር ሁሉንም ወገን ሊያስማሙ የሚችሉ የጨዋታ ሜዳ ሕግጋት እንዲኖሩ ጠንክሮ መሥራት
ከኢሕአዴግ ጋር የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረንም እኛም የአገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በጠንካራ መደላድል ላይ እንዲቆምና ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡ የሃያ አንድ ዓመቱ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አገራችን በክፍለ አኅጉራችንና በአኅጉራችን ሰላም የምትጫወተው ገንቢ ሚና ቀጣይና አስተማማኝ እንዲሆን እንሻለን፡፡ አገራችን በተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቃሚ ትሆን ዘንድ የተጀመሩት ጅማሮዎች ቀጣይነትና ጥልቀት እንዲኖራቸውና ለዚሁ ስኬት ከአካባቢው አገሮች ጋር በምክክር መሥራትዋን እንድትቀጥልበት እንፈልጋለን፡፡
የፖለቲካ ልዩነት ጠላትነት እንዳልሆነ እናምናለን፤ በምንጋራቸው እምነቶች አብረን እየቆምን ልዩነቶቻችን በሠለጠነ መንገድ የሚስተናገዱበት ሥርዓት ሊመቻች ይገባል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን እንጠይቃለን፤ እንታገላለን፡፡ ይህንን ሰላማዊ መንገድ ዳር ማድረስ እንደሚቻልም እናምናለን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ይበልጥ የምትጠቀመው በውይይትና በምክክር፣ ሁሉንም ወገን ሊያስማሙ የሚችሉ የጨዋታ ሜዳ ሕግጋት ቢኖሩ እንደሆነ ካለን ፅኑ እምነት፣ ለዚህ እውን መሆን ከኢሕአዴግ ጋራ ለመወያየት ዝግጁነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡
2. የመደራጀት መብትን፣ ሐሳብን የመግለጽ መብትን፣ የመቃወምና የመተቸት መብትን፤ እንዲሁም ሥልጣን በነፃ ምርጫ የመያዝ መብትን የሚገድቡት ሕጎች እንዲነሱና እንዲስተካከሉ በእነዚህ ሕጎች የታሰሩት ወገኖቻችን እንዲፈቱ መጠየቅ
የአገራችን ሕገ መንግሥት ችግሮች እንዳሉበት እንገነዘባለን፤ ከአቶ መለስ ሕልፈት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ሁኔታ የዚሁ ክፍተት አንድ ማሳያ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌለ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የፕሬዚዳንቱ መኖር ወይም አለመኖር የሚፈጠረውን ክፍተት ከመሙላት አንፃር ምንም ሕገ መንግሥታዊ ፋይዳ እንደሌላቸው አሳይቶናል፡፡
ሕገ መንግሥታችን ጠንካራ ገጽታዎች አሉት፡፡ የመደራጀት መብትን፣ ሐሳብን የመግለጽ መብትን፣ የመቃወምና የመተቸት መብትን፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት፣ እንዲሁም ሥልጣን በነፃ ምርጫ የመያዝ መብትን ይደነግጋል፡፡ እነዚህ የማይነኩ የሕዝብ መብቶች መሆናቸውንና ይህ ታላቅ ሕዝብ ለዚህ ብቁ እንደሆነ እናምናለን፡፡
ይሁን እንጂ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነዚህ መብቶች ተጠቃሚነቱ ተገድቧል፡፡ እነዚህን መብቶች ትርጉም አልባ የሚያደርጉ በርካታ ሕጎችና በሕግ ያልሰፈሩ አሠራሮች ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱ ነፃነቱን በማጣቱ የሕዝብ ከበሬታን አጥቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ ወገኖቻችን ለሞት፣ ለእስር፣ ለስደትና ለኑሮ መመሰቃቀል እንደተዳረጉና እየተዳረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ የሕዝብ መብቶች ናቸው፡፡ ሉዓላዊነቱ የሚያረጋግጥባቸው፣ አገሩን የሚያለማባቸው፣ የአገሩን ሰላምና አንድነት የሚያስጠብቅባቸው ወሳኝ እሴቶቹ ናቸው፡፡ ሊመለሱለት ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ ለዚህ ሕዝብ አክብሮትና እምነት ማሳያ ጊዜው ከረፈደ ቆይቷል፡፡ ከገዛ አገሬው ጋር ለመተቃቀፍ ያለው የመጨረሻ ዕድል ይህ ሊሆን ይችላል፡፡
3. የከረሩ ጫፎችን በመተው ወደ አማካይ ሥፍራው መሰባሰብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈለግን መከተል
ጫፍ ላይ የቆመና የተካረረ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ሲያደማት ቆይቷል፡፡ ክስተቱ የስድሳዎቹ ክስተት ብቻ ሳይሆን አሁንም ያለ ችግራችን ነው፡፡ አሁንም በገዥው ፓርቲ፣ በተቃዋሚዎችና በዳያስፖራው መካከል የሚታይ ችግር ነው፡፡
የከረረ ቃል መጠቀምን፣ የጥላቻ፣ የጭካኔና የ‹‹እኛ እነሱ›› ቃላት የበለጠ ያስጨበጭባሉ፡፡ ነገሮችን ስለ ማለዘብ ስለፍቅር ስለእርቅና ስለሳለም መናገር እንደ ደካማነት ይቆጠራሉ፡፡ ስለዚህ በሚናገሩት ትችት መነጠል ስለሚያሰጋቸው አለማለቱን ይመርጣሉ፡፡ ከዚያም ባሻገር ከመድረክና ከፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን ያገላሉ፡፡
ይህ ችግር ትልቁን ሥዕል ለማየት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ብዙኅኑን የሚያሳትፍና የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያስተናግድ ፖለቲካና መድረክ መፍጠሩን ከባድ አድርጎታል፡፡
ከማንኛውም ወገን የሚመጡትን ለእርቅና ለመግባባት የማያመቹ ድርጊቶችና ንግግሮችን መቃወም፣ በዚያው ልክ ደግሞ ከማንኛውም ወገን ለሚመጡ ገንቢ ሐሳቦችንና ፍንጮችን ዋጋ መስጠትና አጸፋውን በገንቢ ተግባርና ቃላት እየስደገፉ የተፈጠረውን መራራቅ ለማጥበብ ጥረት ማድረግ፣ በዚሁ መንገድ በሕዝባችን የታየውን የአንድነትና የይቅርታ መንፈስ ማጠናከር ይጠበቃል፡፡
4. አገር ውስጥ ለሚሠራው ሥራ ድጋፍ መስጠት
በአገራችን ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ምኅዳር እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልና ደጋፊ መሆንን፣ ሐሳብን በነፃነት መግለጽና ተቺ ጋዜጠኛ መሆን እጅግ አደገኛ ሥራ ሆኗል፡፡ ይህ ብቻ በራሱ ወንጀል ሆኖ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ደጋፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ታስረው መከራ እያዩ ነው፡፡
አስቸጋሪና አደገኛ ቢሆንም በአገር ውስጥ መቆየትና ቦታውን አለመልቀቅ እጅግ አስፈላጊ የፖለቲካ ኢንቨስትመንት ነው ብለን እናምናለን፡፡
በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች አመራሮች አገር ውስጥ ባለው ሕዝባችን ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጭ ካለው ኢትዮጵያዊም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ለትግል የሚያስፈልገውን አቅም በአዝጋሚና አስቸጋሪ ሁኔታም ተሁኖ በሚገባ መገንባት ካልተቻለና ሁኔታዎች ለለውጥ ምቹ ቢሆኑም የተፈለገው ውጤት ላይ ለመድረስ አይቻልም፡፡
ከአራት ዓመታት ቀደም ብሎ በምክክር የተጀመረው የመድረክ ሥራ ከቅንጅት አልፎ ወደ ግንባር ተሸጋግሯል፡፡ እዚህ ለመድረስ የተሠራው ሥራ ቀላል አልነበረም፡፡ በአገራችን ሕዝብና በዳያስፖራው ለዚህ ፕሮጀክት የተሰጠው ድጋፍ የሚመሰገን ሆኖ፣ አሁን በተለይ በተጠናከረ መልኩ ድጋፉን በማስቀጠል በትግሉ ላይ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
5. ከፍተኛ ሕዝባዊ ዲፕሎማሲ
ሁለት ነገሮችን በምሳሌነት መጥቀስ ይህንን ጉዳይ የሚያብራራው ይመስለኛል፡፡ የአርመናውያንን የሕዝብ ዲፕሎማሲና ሰሞኑን ወ/ሮ ሱዛን ራይስ በአቶ መለስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ በአንዳንድ የዳያስፖራ ሚዲያ በኩል የተሰጠው ትችት፡፡ የመጀመርያው የሕዝባዊ ዲፕሎማሲ ስኬትን ያሳያል፤ ሁለተኛው ድክመትን ያመለክታል፡፡
አርሜንያ ትንሽ አገር ነች፡፡ ከአሜሪካ ስትራቴጂ አንፃር ይህ ነው ሊባል የሚችል ሥፍራም የላትም፡፡ የአርመናውያን ‹‹ሎቢ›› ግን በአሜሪካ ውስጥ እጅግ ውጤታማ ከሚባሉት ሦስት ሎቢዎች አንዱ ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አርሜንያን በሚጠቅም መልኩ እንዲቃኝ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡
ወ/ሮ ሱዛን ራይስ በአቶ መለስ ቀብር ላይ ሰውየውን በማድነቅ የሰጡት ዲስኩር የተጋነነ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ የነበረው ግን ከአቶ መለስ በኋላ ከሚኖረው መንግሥት ጋር አሜሪካ ሊኖራት የሚገባው ግንኙነትን አስመልክቶ ምን አሉ የሚለው መሆን ነበረበት፡፡ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና ነፃ ፕሬስ ላይ መሻሻል እንዲኖር አሜሪካ የምትጠብቅ መሆኑዋን ያመለከተ መልዕክታቸውን መዞ በማውጣትና በዚሁ አስታኮ መደረግ ያለበትን መጠቆም ላይ ማተኮር በተገባ ነበር፡፡ በአንዳንድ የዳያስፖራው ሚዲያ በኩል ይበልጥ የተተኮረበት ግን አቶ መለስን በማድነቅ የተናገሩት ላይ ነው፡፡ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ላይ ከማተኮር ይልቅ ዘለፋ አዘል አጸፋ መሰጠቱ ራስን ከማስገመት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
ዳያስፖራው መጀመርያ ከቤቱ ደጃፍ ያለውን ሥራ ማሳካት አለበት፡፡ ብዛቱን ወደሚቆጠር ድምፅና ወደሚሰማ ድምፅ መቀየር መቻል አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ መጀመርያ ዳያስፖራውን ራሱን ይጠቅመዋል፤ ቀጥሎም ኢትዮጵያን ይጠቅማል፡፡
አንዳንድ ወገኖች አጋጣሚውን እንጠቀምበት፣ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊት ለማድረግ መጣ የሚሉት ሌላ አጋጣሚ ሊያመልጠን አይገባም ይላሉ፡፡ አባባሉ ትክክል ነው፡፡
እንዳያመልጠን ማለት ግን እሽቅድድም አይደለም፡፡ ካለፉት ስህተቶች ተምሮ አካሄድን ማስተካከል እንጂ፡፡
6. የአገራችን የዲሞክራሲ እውን መሆን አይቀሬ ነው ለስኬቱ በፅናት፣ በኅብረትና በብቃት እንሥራ
አገራችን በታሪክም በአካባቢያችንም ታላቅ ሥፍራ ያላት፣ ተስፋዋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየለመለመ ያለች አገር ናት፡፡ ይህንን ሥፍራዋን ሳትለቅ በሰላማዊ መንገድ የዕድገትና የዲሞክራሲ መንገድዋን ይበልጥ ለማጠናከር የምንችልበት ሰፊ ዕድል አለ፡፡
ባለፉት ሰላሳና አርባ የፖለቲካ ዓመታት ታሪካችን ላይ የደረሱ ጉዳቶች ያደረሱብንን ጉዳይ በዚሁ ይብቃ ማለት ይኖርብናል፡፡ እነሱን እየመዘዝን በወደፊት የጋራ ጉዞአችን ላይ እንቅፋት እንዳይሆኑ ሁላችንም በኃላፊነት ከሠራን ተስፋውን ከተስፋ የዘለለ ተጨባጭ ነገር እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ብቃት ያለው ሕዝብ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ ይህንን ሕዝብ አክብረንና አምነን እርሱን የአገሩ ጉዳይ ባለቤት ይሆን ዘንድ በጋራ እንሥራ፡፡
ከአዘጋጁ፡- አቶ ስዬ አብረሃ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በአሜሪካ ሲያትል ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው፡፡ ለንባብ እንዲመች ለማድረግ ሲባል ብቻ መጠነኛ የሆነ አርትኦት ተደርጎበታል፡፡
No comments:
Post a Comment