የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። አርብ መስከረም 18 ቀን 2005 ዓም በአንዋር መስጊድ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን የተገመተ ሕዝብ ተገኝቶ ተቃውሞውን አሰምቷል። ከአዲስ አበባ ውጭም በተለያዩ ከተሞች ምዕመናን በከፍተኛ ቁጥር በመሰባሰብ ተቃውሞዓቸውን አሰምተዋል።
በአዲስ አበባው አንዋር መስጊድ ለአስር ደቂቃዎች ተቃውሞ ለማሰማት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ምዕመናኑ ከሠላሳ ደቂቃዎች በላይ የተደራጀ ተቃውሞ አሰምተዋል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ቁጣ ከሌላው ጊዜ ከፍቶ መታየቱም በቦታው የነበረ ዘጋቢያችን ከላከልን ሪፖርት መረዳት ተችሎአል።
ምዕመኑ ተቃውሞአቸውን በገለጹበት ስፍራ የወያኔው አገዛዝ በርካታ ፓሊሶችና ጆሮጠቢዎችን ያሰማራ ቢሆንም ሕዝቡን ለማስፈራራት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። እንዲያውም ፓሊሶች አራት ሴቶችንና ሶስት ወንዶችን ይዘው ለመሄድ ሲሞክሩ ምዕመናኑ ተረባርበው አስጥለዋቸዋል።
በትናንትናው ዕለት በታየው ተቃውሞ የሙስሊሙን ቁጣ ያባባሰው በእስር ላይ በሚገኙ የሙስሊም መሪዎች ላይ የሚደረገው ድብደባና ሰቆቃ እንዲሁም ከህዝበ ሙስሊሙ ፈቃድ ውጪ የ ሃይማኖት መሪዎችን በቀበሌ ለማስመረጥ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ካድሬዎችን ለቅስቀሳ በያንዳንዱ ቤት በመላክ ፈቃደኛ የማይሆኑትን ለማስፈራራት እየተደረገ ያለው ሙከራ እንደሆነ ታውቆአል።
አዲስ አበባ የሚገኘው የግንቦት 7 ዘጋቢ ያነጋገራቸው ወ/ሮ ሸምሲያ አህመድ የተባሉ የቤት እመቤት የቀበሌ ካድሬዎች እቤታቸው ድረስ ሂደው በቀበሌ ውስጥ በሚደረገው የማጭበርበሪያ የመጅሊስ ምርጫ ካልተሳተፍሽ የምትኖሪበት የቀበሌ ቤት ይወሰድብሻል መባላቸውን እሳቸው ግን ከነልጆቻቸው በረንዳ ላይ ቢጥሏቸውም እንኳ ምርጫው ላይ ለመሳተፍ ሲሉ ከቤታቸው እንደማይወጡ የእልህ ሲቃ እየተናነቃቸው ተናግረዋል።
ወጣት አህመድ ሲራጅ ደግሞ “እኛ ነፃነት የተነፈግን ዜጎች ነን። የምርጫው እለት ተቃውሞዓችን የምናሰማው በመስቀል አደባባይ ነው። ይህ ቀን በኢትዮጵያ አዲስ የትግል ምዕራፍ የሚጀመርበት ቀን ይሆናል። በኢትዮጵያዊነታችንም በሙስሊምነታችንም ድርብርብ በደሎች ይደርሱብናል። ይህንን በደል ከትካሻችን ማውረድ የኛ ተግባር ነው። በመስቀል አደባባይ ላይ በምናደርገው ተቃውሞ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ከጎናችን እንደሚሰለፉ እርግጠኞች ነን። እስካሁንም ከጎናችን ነበሩ። ወደፊትም እስከ ነፃነት አብረን እንዘልቃለን” ብሏል።
ወጣት ሃኒያ አህመድ ደግሞ “በአደባባይ በምናደርገው ተቃውሞ የሚመጣብንን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ነን። በበኩሌ ለዲኔ፣ ለእምነቴ፣ ለመብቴ ብሞት ደስተኛ ነኝ” ብላዋለች ለሪፓርተራችን።
በደሴ፣ በከሚሴ፣ በድሬዳዋና ሐረር፣ በአርሲ እና በሌሎችም የአገሪቱ ከተሞች የይስሙላ ምርጫ ይደረጋል በተባለበት የሚቀጥለው እሁድ ሙስሊሞች አቅራቢያቸው ወደሚገኘው አደባባይ ለተቃውሞ እንደሚያመሩ እየተነገረ ነው።
ዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ቢሞትም አንዳችም ለውጥ ሳይደረግ አገዛዙ የቀጠለ በመሆኑ ይህ ሥርዓት ካልተወገደ በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖትም ሆነ የዜጎች መብቶች ይከበራሉ ማለት ዘበት መሆኑን ብዙዎች የተስማሙበት ጉዳይ ሆኗል።
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ፍትሃዊ ጥያቄ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጥያቄዓቸው የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ በመሆኑ ነፃነትና መብት የጠማው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ እንዲቆም ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment