Translate

Saturday, September 15, 2012

ኢትዮጵያውያን እስረኞች በአስከፊ የስቃይ ሁኔታ እንደሚገኙ ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች አጋለጡ


መስከረም ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የታሰሩት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች በአስከፊ የስቃይ ሁኔታ እንደሚገኙ ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች አጋለጡ።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ወደ ኦጋዴ ክልል በመግባት በአካባቢው እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመቅረጽ ሲሞክሩ በታጣቂዎች ተይዘው ላለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ከታሰሩ በሁዋላ ሰሞኑን የተለቀቁት ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እስር ቤት በእስረኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስከፊ መሆኑን ገልጸዋል።

እነሱ  መፈታታቸው በታወቀ  ቀን  በእስር ላይ የሚገኙት  ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች  “እጆቻቸውን በካቴና የፊጥኝ እንደታሰሩ፦“ጆሀን!ማርቲን!” በማለት  በስሟቸው እንደጠሯቸው ያወሱት  ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች፤ ከዚያም ፦”አደራ አደራ ያያችሁትን ሁሉ ለቀሪው ዓለም ንገሩልን! አሉን” ብለዋል።
“እኛ ነፃ ጋዜጠኞች እስከሆንን ድረስ ያየነውን እንናገራለን።አደራም አለብን!” ያሉት ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ፤ “ኢትዮጵያውያኑ አደራውን ሲነግሩን፤ እጆቻቸውን በካቴና እንደታሰሩ ነው።መንግስታቸው ሰብዓዊ ርህራሔ የሌለው እጅግ ጨካኝ ነው”ሲሉ ተናግረዋል።
ማርቲን ሽብዬና ጆሀን ፔርሰን በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ዓለማቀፉ ህብረተሰብ ኢትዮጵያውኑን  ጋዜጠኞችና የፖለቲካ እስረኞች እንዲታደግ ተማጽነዋል።
ማርቲን ሺብየንና ጆሀን ፔርሰንን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሰሳካም፣  ጋዜጣዎ መግለጫውን የተከታተለው አቶ አህመድ አሊ ፣ መግለጫው ልብ የሚነካ እንደነበር ተናግሯል።

No comments:

Post a Comment