በፍሬው አበበ
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የቀድሞ የፓርላማ አባልና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) አማካሪ ምክርቤት ሰብሳቢ ናቸው። ከወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ፍሬው አበበ አነጋግሮአቸዋል።
ሰንደቅ፡- ከጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኃላ አስተዳደሩን ከተረከበው አዲስ አመራር ምን ይጠበቃል?
አቶ ቡልቻ፡- አዲስ አመራር አለን’ንዴ?ይህን ከአንተ ነው የምሰማው። አንተ አዲስ አመራር ትላለህ። እኛ ግን አዲስ አመራር እያየን አይደለም። ማንነው የሚመራን?
ይህ’ኮ የዘጠና ሚሊየን ሕዝብ ጉዳይ እኮ ነው። የዛሬ 30 እና 40 ዓመት የኢትዮጽያ ሕዝብ ቁጥሩ 50 ሚሊየን ገደማ ነበር። ዛሬ 90 ሚሊየን ደርሷል። ችግሩ ሰፍቷል፣ ፍላጎቱ አድጓል። የዚህ ትልቅ አገር፣ ትልቅ ሕዝብ አመራር እንዴት ተወሰነ? የኢትዮጽያ ፓርላማ የሚባል አለ።
ይህ’ኮ የዘጠና ሚሊየን ሕዝብ ጉዳይ እኮ ነው። የዛሬ 30 እና 40 ዓመት የኢትዮጽያ ሕዝብ ቁጥሩ 50 ሚሊየን ገደማ ነበር። ዛሬ 90 ሚሊየን ደርሷል። ችግሩ ሰፍቷል፣ ፍላጎቱ አድጓል። የዚህ ትልቅ አገር፣ ትልቅ ሕዝብ አመራር እንዴት ተወሰነ? የኢትዮጽያ ፓርላማ የሚባል አለ።
ፓርላማው በእንዲህ ዓይነት ትልቅ ጉዳይ አያገባውም’ንዴ?
ሰንደቅ፡- በአሁኑ ሰዓት በግልጽ የሚታወቅ አዲስ አመራር የለም ነው እያሉኝ ነው?
አቶ ቡልቻ፡- አዎን!…መሪው ማን እንደሆነ ሕዝብ የማወቅ መብት አለው።
ሰንደቅ፡- በቀጣይ ተተኪ ከሚሆነው አመራር ምን ይጠበቃል?
አቶ ቡልቻ፡- መጀመሪያ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአሁኑ ጊዜ አገሪትዋ ምን ዓይነት አመራር ያስፈልጋታል ብሎ መጠየቅ አለበት። እኔም እጠይቃለሁ። እስካሁን ድረስ አንድ ፓርቲ፣ ያውም ዝግት ያለ ፓርቲ… ሌላ ኀሳብ፣ አማራጭ የማይቀበል፣ የማያስተናግድ ፓርቲ ላለፉት 21 ዓመታት ሲመራን ቆይቷል። ከዛሬ 21 ዓመታት በፊት ይዞት የመጣውን የራሱን ኀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ይሞክራል። ኀሳብ አይለወጥም’ንዴ? ታላቁ የአሜሪካ መንግስት እንኳን በየአራት ዓመቱ አመራሩን ይለውጣል። ፖሊሲ ባይለውጥ እንኳን አመራሩ መለወጡ ጥሩ ነገር ነው። 21 ዓመታት ሙሉ በአንድ አመራር ብቻ፣ በአንድ ፍልስፍና ብቻ፣ በትግል ላይ ተገናኘን በሚሉ ጥቂት ሰዎች ብቻ ኢትዮጵያን ያህል አገር እንዴት ትመራለች? በቀጣይ በኢትዮጵያ የተሸለ ነገር የሚመጣው የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ተገናኝተው፣ በክብ ጠረጼዛ ዙሪያ ተመካክረው መፍትሔ ማምጣት የሚችሉበት ዕድል ሲፈጠር ብቻ ነው።
ሰንደቅ፡- የአቶ መለስ ህልፈተ ሕይወት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ነገር እንዲፈጠር ያደርጋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ቡልቻ፡- አዎ…ትልቅ ለውጥ መምጣት አለበት። ኢህአዴግ እና አቶ መለስ አገሪቷን የመሩበት አቅጣጫ ብዙ ኢትዮጽያዊያንን ያረካና በቂ አልነበረም። ብዙ ኢትዮጽያዊያን ደስተኞች አይደሉም። ይህ ሁሉ በአቶ መለስ ቀብር ላይ የተገኙ የውጪ አገር ሰዎች ንግግርና ምስክርነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰምቶ በቃ ጥያቄዬ መልስ አግኝቷል ብሎ ቤቱ አርፎ የሚቀመጥ ይመስልሃል? የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ለውጥ እየጠበቀ ነው።
ሰንደቅ፡- ሰሞኑን ሐዘኑን ለመግለጽ የወጣው ሕዝብ ለኢህአዴግ እግረመንገድ ድጋፉን ሰጥቷል እየተባለ ነው?
አቶ ቡልቻ፡- በእኔ ግምት ሐዘንን መግለጽ ድጋፍን አያሳይም። እርግጥ ነው፤ አቶ መለስ እንደማናችንም ዘመዶች አሏቸው፤ የሚወዷቸውም፣ የሚደግፏቸውም ሰዎች አሉዋቸው። ከዚህ አንጻር ለሐዘን ሰው መውጣቱ አያስገርምም። ግን ኢትዮጽያ ሕዝብ ወጥቶ አላለቀሰም። ለምን ብትል ብዙ ቁስል ያለበት ህዝብ አለ። የዛሬ አራት ዓመት በአንድ ቀን ከቀትር በኋላ ብቻ በኦሮሚያ 200 ሰዎች የተገደሉበት ሁኔታ ተረሳ? በ1997 ዓ.ም የወለጋ ሕዝብ ጦርነት ተከፈተበት፤ መዓት ሰዎች አለቁ፤ ማሳቸው ተቃጠለ፤ የተቀሩት ተሰደዱ፤ ይህ ይረሳስ ቢባል እንዴትይረሳል? ለአቶ መለስ የሚያለቅስላቸው ቢኖርም እጅግ የበዛው የማያለቅስላቸው፣ ያዘነባቸው ሕዝብ ነው። ባለፉት ዓመታት በዚህ ሥርዓት ብዙ ሰዎች ታስረዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተንገላተዋል፣ ተሰደዋል። ብዙ ቤተሰቦች ተበትነዋል። ይህንን እውነታ ማንም ሊክደው አይችልም። ሰዎች ለአቶ መለስ ስላለቀሱ፣ ስላዘኑ ብቻ ለኢህአዴግ ድጋፍ ሰጡ ማለት የማይቻለው ከዚህ አንጻር ነው። ለነገሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ለአቶ መለስ ቢያለቅስ እንኳን ለኢህአዴግ ድጋፍ ሰጠ ማለት አይቻልም።
ሰንደቅ፡- ተጠባባቂ ጠ/ሚኒስትሩ የአቶ መለስን ጅምሮች ይዘው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ይህ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?
አቶ ቡልቻ፡- አስቀድሜ ተናገርኩ እኮ!… ኢህአዴግ በሕግና በፖለቲካ ተደግፎ በሕዝብ ላይ ትልቅ ግፍ ሲሰራ ነበር። በዚህ መንገድ ሊቀጥል ነው? ይህን ዓይነት አካሄድማ ማንም ኢትዮጵያዊ አይደግፈውም። ለምንድነው ሰዎች ያለህግ የሚታሰሩት? ለምንድነው ሰዎች ከታሰሩ በኃላ በዘመዶቻቸውና በወዳጆቻቸው እንዳይጎበኙ የሚከለከሉት? ለምንድነው ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻ በመግለጻቸው፣ በመጻፋቸው የሚታሰሩት? ሕገመንግስቱ የኀሳብ ነጻነት አለ ይላል። ማንም ሰው ኀሳቡን በነጻነት መግለጽ ይችላል። የተሰጠውን ኀሳብ ሰዎች ሊቀበሉት ይችላሉ ወይም አይችሉም ሌላ ጉዳይ ነው። ለምን ተናገርክ፣ ለምን ጻፍክ ብሎ ማሰር፣ ፍርድቤት ማመላለስ ምን ዓይነት የህግ ሥርዓት ነው?እርግጥ ነው አባይ ይገደባል ሲባል በግሌ ደስ ይለኛል። ልማትን የሚጠላ የለምና። ግን ስንትና ስንት ጉድፎችን ተሸክሜ እሄዳለሁ ብሎ ማለት ምን ማለት ነው? በእኔ ግምት በቀድሞ አገዛዝ እቀጥላለሁ ማለት ሕዝብን ተስፋ ማስቆረጥ ነው።
No comments:
Post a Comment