Translate

Monday, September 24, 2012

ዶላር አዘዋዋሪዎቹ ደላሎች!! ዳያስፖራው ወጋገን ባንክን እያደለበ ነው!


wegagan
ህወሓት የአጋር ፓርቲዎቹን የንግድ ተቋማትና ልማታዊ ባለሀብት እያለ የሚጠራቸውን አባላቱን በዋናነት አሰባስቦ ያቋቋመው የወጋገን ባንክ ውለታ ባስገባቸው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች አማካይነት በቀን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር የመሰብሰብ አቅም መገንባቱ ተጠቆመ።
የጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ባካሄደው ማጣራት ወጋገን ባንክ ከፖለቲካው አመራር ባለው ቀጥተኛ ድጋፍና ሽፋን በመታገዝ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፈውን የውጪ ምንዛሪ መቆጣጠር ያስቻለውን አቅም የገነባው በአስገዳጅ ደንብ ነው።
በሶማሌ ተወላጆችና በህወሓት ሰዎች አማካይነት በሽሪክነትና በተናጥል የተቋቋሙ የገንዘብ አዘዋዋሪ ተቋማት ስራውን መስራት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ሲያወጡ ከወጋገን ባንክ ጋር ብቻ ለመስራት አስቀድመው ውል እንደሚፈጽሙ ያስታወቀው ዘጋቢያችን፤ በዚሁ መሰረት ውል ከገቡት የገንዘብ አሰባሳቢ ድርጅቶች መካከል ዋንኞቹን በስም ዘርዝሯል።

ደሀብሺል/Dahabshiil፣ ካህ ኤክስፕሬስ/Kaah Express፣ ተወከል/Tawakal፣ ገረን ኤክስፕሬስ/Qaran Express፣ ኦሊምፒክ ኤክስ/Olimpic X፣ ሆዲን ግሎባል ኤክስፕሬስ/Hodin Global Express፣ አማነ/Amaana፣ ሰሃል/Sahal የመሳሰሉት በኢትዮጵያ ቢሮ ከፍተው በገንዘብ ዝውውር ስራ የሚሰሩትን ድርጅቶች የዘረዘረው የጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የአዲስ አበባ ዘጋቢ የገንዘብ ዝውውሩ እንዴት እንደሚከናወን አመልክቷል።
ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከአረብ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚላከውን የውጪ ምንዛሪ በማስተላለፍ ኮሚሽን የሚወስዱት ክፍሎች ራሱ ወጋገን ባንክ፣ ምንዛሪውን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ወጋገን ባንክ የሚያስተላልፉት የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችና እነዚህ ድርጅቶች ብር እየለቀሙ በወጋገን ባንክ በኩል እንዲላክ የሚያደርጉ ደላሎች ሲሆኑ ከሚተላለፈው ገንዘብ ሁሉም በጥቅሉ የሚካፈሉት የአምስት በመቶ (5%) ኮሚሽን አላቸው።
በዚሁ ስሌት መሰረት ወጋገን ባንክ ሁለት በመቶ (2%)፣ የገንዘብ አስተላላፊው ተቋም ሁለት በመቶ (2%)፣ ደላሎቹ ደግሞ አንድ በመቶ (1%) በዶላር ሂሳብ የሚታሰብና ባሉበት አገር ገንዘብ ተመንዝሮ የሚሰጣቸው ድርሻ አለቸው። ወጋገን ባንክ ዶላሩን በራሱ ሒሳብ (account) በታዋቂ አለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች አማካይነት ካስገባ በኋላ ከአምስት መቶኛው ድርሻውን ከመውሰዱ በተጨማሪ በያንዳንዱ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ውስጥ በገንዘብ ተቀባይነት (cashier) የሚሰሩ ሰራተኞችን በመመደብ ገንዘብ ለተላከላቸው ሰዎች በኢትዮጵያ ብር ክፍያ የሚያከናውነው ራሱ ነው።
“የሚላከው የውጪ ምንዛሪ በራሱ አካውንት ከገባለት የራሱን ገንዘብ ከፋይ ለምን ይመድባል?” በሚል ዘጋቢያችን ላነሳው ጥያቄ “ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶቹ ከዋናው ተልዕኳቸው ውጪ በማናቸውም የገንዘብ ማቀባበል ስራ እንዲሰማሩ አይፈለግም፤ አመኔታም የላቸውም። የሚላከው ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲቀየር በርካታ ስለሆነ ወጋገን ባንክ ከእስልምና ጉዳዮችና ከተለያዩ እንቅስቃሴዎች ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል የሚል ስጋት ስላለበትም ጭምር ተቀባዮችንም ለመቆጣጠር ጭምር ሲባል ነው…” ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው መልስ ሰጥተዋል።
አውሮፓ ተቀምጦ ገንዘብ በማሰባሰብ አንድ ከመቶ ኮሚሽን የሚወስድ አንድ የድለላ ሰራተኛ ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ሪፖርተር እንደተናገረው ስራ የለም ከተባለ እስከ ሃምሳ ሺህ ዶላር በቀን ወደ ወጋገን አካውንት የሚገባ የገንዘብ ሰነድ ለቀጠረው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅት እንደሚልክ አስታውቋል።
የገንዘብ አዘዋዋሪ ድርጅቶቹ የሶማሌ ተወላጆች ቢመስሉም ከጀርባቸው ተቆጣጣሪና ሽርካ እንዳላቸው የጠቆመው ይህ ደላላ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የሶማሌ ዜጎች ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በመላክ ወጋገን ባንክን እያደለቡት እንደሆነ አመልክቷል። ስሙ እንዳይገለጽበት የጠየቀው የሶማሌ ተወላጅ “የኢትዮጵያ መንግስት በኛ መስመር ብቻ በቀን እስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የውጪ ምንዛሪ ከአውሮፓ ብቻ ያገኛል” ሲል ከቅርብ አለቆቹ የተነገረው እንደሆነ  በመጥቀስ ተናግሯል። በየቦታው የተበተኑት ደላሎች እንዴትና ማን እንደመለመላቸው በራሱ አነጋጋሪ መሆኑንም አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የወጪ ምንዛሪ እጥረት ችግር አሳሳቢ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ባንኮች በተለየ መልኩ ሸሪኮቹን እንደሚያሰተናግድ በመግለጽ በርካታ ባለሃብቶችና ተገልጋዮች ምሬት የሚያቀርቡበት ወጋገን ባንክ፤ ከኤፈርት ቀጥሎ “ከፍተኛ ባለድርሻ” በሚል የያዛቸው የብአዴኑ ኢንዶውመንት – ጥረትና የኦህዴድ የንግድ ድርጅት – ቱምሳ ኢንዶውመንት እንኳን ሳይቀሩ በወጉ እንደማይስተናገዱ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ምንጮች ይጠቁማሉ።
በተለይም ቱምሳ ኢንዶውመንት ማዳበሪያ ንግድ ውስጥ በመግባት የኤፈርት አንድ አካል የሆነውን አምባሰልን ከፍተኛ ገቢ ስለተጋራው ሆን ተብሎ ብድር እንዲከለከል በማስደረግ እዳ ታቅፎ እንዲቀመጥ መደረጉን የሚጠቁሙት የጎልጉል ምንጮች፣ ኦህዴድ በክልሉ እንኳ ማዳበሪያ መሸጥ እንዳይችል መደረጉ ህወሓት አጋር ፓርቲዎችን በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በገንዘብ ተቋሙ በኩልም ምን ያህል ባሪያ እንዳደረጋቸው ማሳያ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
የህወሓት ንብረት በመሆኑ ብቻ በሚደረግለትና በሚመቻችለት የተለየ ጥቅም ከዋናው የአገሪቱ ባንክ ይልቅ “የኔ” ለሚላቸው ወዳጆቹና የስርዓቱ ደጋፊዎች ያለ ወረፋ የውጪ ምንዛሪ በማቅረቡ የባንኩ ደንበኛና የህወሓት አጋር ያልሆኑ አስመጪዎች እንቅስቃሴያቸው ሊፋዘዝ እንደቻለ የአዲስ አበባ የጎልጉል ዘጋቢ አመልክቷል። ባንኩ የሸፍጥ ንግድ ውስጥ መግባቱና የንግድ ውድድሩ እንዲዛባ ምክንያት ከመሆኑ ውጪ አገሪቱ ያጋጠማትን የውጪ ምንዛሪ እጥረት መቅረፍ የሚያስችል ሚና እንደሌለው ታዋቂ ነጋዴዎች አስተያየት መስጠታቸውን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተበተኑ ኢትዮጵያውያኖች ለፍተው ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩት የውጪ ምንዛሪ ተሰብስቦ በተለያዩ መንገዶች ህወሓት ጉያ ውስጥ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ቢገለጽም መንግስት ራሱ የሚያወጣቸው መረጃዎች ከዳያስፖራው የሚገኘው የመንግስት የውጪ ምንዛሬ ገቢ  ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሄዱን ነው። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤም ኤፍ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ድርቅ መመታቷን በቅርቡ ማስታወቁ አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment