Translate

Monday, September 10, 2012

ጃንጥላው ተቀዶአል


   የወያኔ ስርአት በታሪኩ እንዲህ ያለ የተምታታ ሁኔታ ላይ የደረሰበት የታሪክ አጋጣሚ ነበር ለማለት አይቻልም። የባንክ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ፣ የኦነግ ከመሸጋገሪያው መውጣት፣ የኤርትራ ጦርነት፣ የህወሃት መከፋፈል፣ ምርጫ 97 የመሳሰሉ አጋጣሚዎች ለኢህአዴግ ፈታኝ የነበሩ መሆናቸው ይታወቃል።
ከፍተኛ ትርምስ የነበረባቸውም ናቸው። ቢሆንም በነዚያ ጊዜያት ድርጅቱ ድርጅታዊ አቅሙን ባለማጣቱ አንሰራርቶ መቀጠል ችሎአል። የመለስ ዜናዊን እረፍት ተከትሎ የመጣው ቀውስ ግን የድርጅቱን መሰረት እያናጋው ይገኛል።
        መለስን ተከትሎ አብሮ ለመሞት በጣም እየተጣደፈ ያለው ኦህዴድ ሆኖአል። ኦህዴድ መሪ የለውም። የህወሃት አንጋፋዎች የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም ኦህዴድን ከመሞት ለማዳን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው እየተሯሯጡ ይገኛሉ። መተካካት የሚለውን ነጠላ ዜማ ደምስሰው፣ ገራባ እየፈለጉ ነው። መገረብ ጀምረዋል። ኩማ ደመቅሳን የኦህዴድ ሊቀመንበር፣ አባ ዱላን በኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነት ለማስቀመጥ፣ በካድሬዎቻቸው በኩል ቅስቀሳ ይዘዋል። ይህ ሩጫ ጊዚያዊ ጥገና ይባላል። እንደ አሸዋ ግድብ ከነገ ወዲያ መልሶ ይፈርሳል።
“የሃይለማርያም ደሳለኝ ምክትል ማን ይሁን?” የሚለው እንዳከራከረ ሲሆን፣ በአንድ በኩል ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ለማስቀመጥ አሳብ ሲቀርብ፣ በሌላ በኩል የህወሃት እና የብአዴንን ፉክክር ለማስቀረት፣ ኩማ ደመቅሳን በምክትልነት ለማስቀመጥ መምረጣቸው ይሰማል። መፍትሄ አይሆንም። በዚህ አካሄድ ማንኛውም ነገር ወደሁዋላ በፍጥነት ይጓዛል።
ሁኔታዎች በፍጥነት ሲለዋወጡ ሰንብተዋል። ለዚህ ሲለዋወጥ ለሰነበተ ውዥንብር መቁዋጠሪያ ለማበጀት የኢህአዴግ ምክርቤት ከመስከረም 3 እስከ 5 ስብሰባ ጠርቶአል። ርግጥ ነው፣ ውዥንብሩን ለመቀነስ የሚረዳ፣ ከሃሜት የሚያድናቸውን አንድ ደካማ መዋቅር በመፍጠር፣ “ችግሩ ተፈትቶአል” ብለው ሊውጁ ይችላሉ።
ሊቀጥሉ ግን አይችሉም። ኢህአዴግ ማእከል አጥቶአል። ቀደም ሲል ኢህአዴግ አንድ መቋጠሪያ ነበረው። አንድ የሚፈሩት ሰው ነበራቸው። ሁሉም ልዩነቱን፣ ቅሬታውን ብሶቱን ይዞ የሚሮጥበት አንድ ቢሮ ነበር። አሁን ያ የለም። ጃንጥላው ተቀዶአል። ከጥቂት በላይ ምሰሶዎች በያቅጣጫው እየተተከሉ ነው። በራቸውን መክፈት ካልቻሉ፣ አፍጦ የመጣባቸውን እውነት ማየት ካልቻሉ እጣ ፈንታቸው ደጃፋቸው ላይ ከተቀመጠው መልአከ ውድቀት እጅ ላይ መውደቅ ይሆናል።

No comments:

Post a Comment