Translate

Friday, September 21, 2012

ኃይለማርያም ደሳለኝ – እንደ ዳንኤል፤ እንደ አክሊሉ ወይስ እንደ መለስ?


አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አስር የሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አስተዳድረዋታል፡፡ ከእነዚህ መካከል በተለየ ሁኔታ ከሚወሱት አንዱ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ናቸው፡፡
በጣልያን ወረራ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ በአውሮጳ ያደረጉት ተጋድሎ እጅግ ከፍተኛ ለመሆኑ በተለያዩ ቦታዎች ሲጠቀስ የሚሰማ ነው፡፡ አርበኞቻችን በአገር ውስጥ የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ አክሊሉ ሃብተወልድ በአውሮጳ የከፈሉት መስዋዕትነትና ኢትዮጵያን ለማዳን የሠሩት ሥራ ተጽፎ የማያልቅ ታሪካቸው ነው፡፡ ያላንዳች ማጋነን የዲፕሎማሲውን ሥራ ያለመታከት ከግብ ያደረሱት አክሊሉ ነበሩ፡፡
በተለይ “የአክሊሉ ማስታወሻ” በተባለው የራሳቸው ታሪክ በከፊል የተወሳበት መጽሐፍ ላይ የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆር እና የፈረንሣዩ ጠ/ሚ/ር ላቫል ከኢትዮጵያ ክፍላተሃገራት አብዛኛው የሆነው ሐረር፣ ሲዳሞና ባሌን ጨምሮ ለጣሊያን እንዲሰጥ የተቀረው ጎጃም፣ ጎንደርና ትግራይ ለኢትዮጵያ እንዲሆን በምስጢር ያዘጋጁትን “የሆር-ላቫል” ስምምነት ሰነድ አክሊሉ በለንደን በጋዜጣ ላይ ይፋ እንዲወጣ በማስደረግና በእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ ሙግት በማስነሳት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆር እያለቀሰ ይቅርታ የጠየቀበትና ሰነዱም ውድቅ የተደረገበት ውሳኔ ጠ/ሚ/ር አክሊሉ ለአገራችን ከሰሩት ስፍር ቁጥር ከሌለው ውለታ አንዱ ነው፡፡

ከድል በኋላም አክሊሉ በውጭ ጉዳይ ቀጥሎም በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገራቸውን ባገለገሉባቸው ዓመታት ሁሉ ከሚጠቀሰት መካከል የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ በዲፕሎማሲው መድረክ ላይ ጣሊያን በከፈተችው ጦርነት ተባባሪ በመሆን ያስቸግሩ ለነበሩት የላቲን አሜሪካ አገሮች አክሊሉ የሰጡት ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ነበር፡፡ በመንግሥታቱ ማኅበር ፊት እንዲህ ነበር ያሉት፡-
“በዚህ አጋጣሚ ለባልደረቦቼ የላቲን አሜሪካ አገሮች ተወካዮች፣ በተለይም ለአርጀንቲናው ልዑክ እጅግ በጣም ከባድ ፋይዳ ስላለው ጉዳይ የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ። ዛሬ አገሬ ከግብጽ እና ከላይቤሪያ ጋር ሆና እናንተ ከጣልያን ጋር በማደም የአፍሪቃን ሕዝቦች ለመጨቆን የምትጫወቱትን ሚና በጥንቃቄ እየተመለከትን ነው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን እዚህ ያለነው ሦስት አፍሪቃውያን አገሮች በአስር እጥፍ በዝተን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተገቢ መቀመጫችንን እንይዛለን። ያን ጊዜ እኛ እንደናንተ ሳይሆን፣ ለዓለም ሰላም ድጋፍ እና ፍትሐዊ ፍርድ ድምጻችንን እንደምናሰማ ጥርጣሬ የለኝም።”
እንዳሉትም በርካታ የአፍሪካ አገራት በያኔው የመንግሥታ ማኅበር ውስጥ አባል በመሆን የኃይሉ ሚዛን ላይ ተጽዕኖ ማድረግ ጀመሩ፡፡
ከዘመነ አክሊሉ ወደእኛ ዘመን በፍጥነት ስንመጣ የምናገኘው ህወሓት/ኢህአዴግንና መለስን ነው፡፡ ባሳለፍናቸው 21ዓመታት መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ ስፋቱም ሆነ ጥልቀቱ ይህ ነው ተብሎ ሊዘረዘር የሚችል አይመስለንም፡፡ እርሳቸው ግን የቆፈሩትን ጉድጓድ ጥልቀቱንም ሆነ ስፋቱ ሳይናገሩ እንዴት እንደሚደፈን ለባልደረቦቻቸውም ሳያሳውቁ አልፈዋል፡፡ ዛሬ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ወንበር ላይ እንዲቀመጡ ተሰይመዋል፡፡ አቀማመጣቸው እንዴት ይሆን?
አቶ ኃይለማርያም “ምዕራፍ” ለተሰኘ መጽሔት “ሕዝብን እና አገርን በመልካም አስተዳደር የማገልገል” የጸጋ ስጦታ እንደተሰጣቸው በተናገሩት ቃለምልልስ ላይ የሚጸጸቱበትን ውሳኔ አስተላልፈው እንደሚያውቁ ለተጠየቁት ምላሽ “አንድ ጥፋት ሰው ላይ ከሚደርስ ብዙ ጊዜ ራሴን ብጎዳ እመርጣለሁ … እስካሁን ድረስ ጎድተኸኛል ብሎ የተናገረኝ ሰው የለም” በማለት ነበር የመለሱት፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስም የባቢሎን ጠ/ሚ/ር እንደነበረው “ዳንኤል መሆን መልካም እንደሆነ” ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ ባደረጓቸው ንግግሮች ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመለስን ራዕይ፣ ዓላማ፣ ሃሳብ … የጋራ አመራር … የሥራ መለያቸው እንደሆነ ነግረውናል፡፡
ዳንኤል በባቢሎን በሥልጣን በነበረበት ጊዜ “ስለኃጢአታችንና (በደላችን) የሩሳሌም (እስራኤል) እና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋል … ፊትህን አብራልን” በማለት ነበር በቅኝ ግዛት ሥር ስለወደቀችው አገሩ ነጻነት የማለደው፡፡
አክሊሉ ኢትዮጵያን ባገለገሉባቸው ዓመታት ከተናገሯቸው በርካታ ንግግሮች መካከል ተጠቃሽ የሆነው “የደረሰው ይድረስ ደካማ ሆኜ መታየት አልፈልግም፡፡የሀገሬን ጥቅምና መብት የሚነካ መስሎ ከታየኝ መናገሬን አልተውም” የሚለው አንዱ ነው፡፡ ይህም ከቃል አልፎ በሥራቸው ተተርጉሞ ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡
መለስ ላለፉት 21ዓመታት ሲነግሩን የነበሩትን “ስድብ ተኮር” ቃላት መድገም ባያስፈልግም “የአዝማሪ” ያሉትን የኢትዮጵያን ታሪክ እርሳቸውም በህይወታቸው “የሚሊኒየም፣ …” እያሉ ሲያዜሙት መስማት አሁን ማስታወሻችን ነው፡፡
ኃይለማሪያምስ? እንደ አክሊሉ፣ እንደ መለስ ወይስ እንደ ዳንኤል ይሆኑ? የእኛ ምክር መጀመሪያ እንደራሳቸው እንዲሆኑ፤ ቀጥሎም እንደፖለቲከኛ እንደ አክሊሉ እንደ ሃይማኖተኛ ደግሞ እንደ ዳንኤል እንዲሆኑ ነው፡፡ እርሳቸው ግን እንዴት እንደሚሆኑት ዛሬ ጀምረውታል፡፡ ሕዝብ ማስተዋል፤ ታሪክም መመዝገብ ጀምሯል፡፡

No comments:

Post a Comment