Translate

Monday, September 17, 2012

እኛ ህዝብ ስንል እና እነርሱ ህዝብ ሲሉ


በዓለማችን ላይ በህዝብ ስም ብዙ ክፉ እና ደግ ነገሮች ተሰርተው አይተናል። ሂትለር “እኛ ብቻ ወርቆች” ብሎ እርሱ ወርቅ ብሎ በሚጠራው ህዝብ ስም የሠራውን ሠርቶ አልፏል። በሌላ በኩል ማርቲን ሉተር ኪንግ ደግሞ ዘረኝነት የፈጠረውን ክፉ አስተሳሰብ ለመግደል ሲታገል ቆይቶ የመጨረሻውን መስዋእትነት ከፍሎ በክብር አልፏል።
ወዲህ ወደ አገራችን ስንመለስ ድምጻቸውን በጣም ከፍ አድርገው በህዝብ ስም የተገዘቱና የማሉ ገዥዎችን እናገኛለን።እጅግ በጣም ድምጹን ከፍ አድርጎ በተለየ መልኩ በህዝብ ስም የጮኸ ግን እንደ ህወሃት ያለ አልታየም። የጩኸቱን ያክል ደግሞ ህዝብን ያዋረድና ያንገላታት እንደ ህወሃት ያለም አልታየም። ከህወሃት በፊት የነበሩ አምባገነኖች ኢትዮጵያዊያን ሁነው ኢትዮጵያዊያንን የበደሉ ቢሆንም ህወሃት ግን ኢትዮጵያዊነት መንፍስ ሳይኖረው ኢትዮጵያዊያንን የበደለ ዘረኛ ድርጅት ነው።ከህወሃት በፊት የነበሩት ደርጎች ዘረኝነትን በቃልም በገቢሪም ሲገልጡ አልታዩም ህወሃት ግን ዘረኝነትን በቃልም በገቢሪም የገለጠ ድርጅት ነው።የዚህ ቡድን መሪ የነበረው መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ “መሪ” እኔ ነኝ ብሎ ሲያበቃ ህዝቡን ለሁለት ከፍሎ ተወለድኩበት የሚለውን ብሄር ለይቶ “ወርቅ” ብሎ መጥራቱ የሰውየውን ማን መሆን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ዓብይ ጉዳይ ሁኖ ይቆያል። ከዚህ ቀደም የነበሩ ገዥዎች “እንኳንም ከኢትዮጵያ ተወለድኩ” ይላሉ እንጂ ደምና አጥንታቸውን ቆጥረው ወደ መንደራቸው ወርደው “እንኳን ወርቅ ከሆነው ብሄር ተወለድኩ” ሲሉ አልተሰሙም።

ከህወሃት በፊት የነበሩ ገዥዎች ግዜውና ሁኔታው በፈቀደላቸው መጠን አስበው የራሳቸውን ትልቅ ኢትዮጵያ ለመፍጠር ሲሉ ህዝቡን በደሉት እንጂ እንደ ህወሃት ወሰን በሌለው ዝሪፊያ ውስጥ አልተዘፈቁም። ህወሃት ተብሎ የሚታወቀው ድርጅትና አባላቱ ግን የባእድ አገር የያዙ ይመስል እጅግ አሳፋሪ በሆነ ዝሪፊያ ውስጥ ስለመዘፈቃቸው ብዙ ማስረጃዎችን አቅርቦ ማሳየት ይቻላል። ህወሃት ለህዝብ ቆሜያለሁ እያለ ያንኑ ህዝብ ለመዘረፍ የዘረጋው የዝሪፊያ መረብ በየትኛውም አገር ታሪክ ታይቶ የሚያወቅ አይደለም። በመንግስት ስም ተደራጅቶ የገዛ አገሩን የዘርፈ፤የገዛ አገሩን ጥቅም ለባእድ አሳልፎ  የሰጠ  ቡድን እንደ ህወሃት ያለ በአገራችን ታሪክ አልታየም። አልተሰማም። ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ጉዞ ውስጥ ህወሃት የተባለው ዘረኛ ቡድን ለህዝብ ቆሜያለው የሚለው ውሸቱን መሆኑን በተግባር አሳይቶናል።ለህዝብ የቆመ ቡድን ከገዛ አገሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዘርፎ በባእዳን አገር አይደብቅም። ለህዝብ የቆመ ቡድን ከህዝብ የሚሠውረው ምንም ነገር አይኖረውም። ለህዝብ ቆሜያለው የሚል ቡድን ዛሬ የተናገረውን ነገ እያፈረሰው በአገር እና በህዝብ ላይ የወንበዴ ጨዋታ አይጫወትም።
ቀደም ብለው የነበሩ አምባገነኖች ያሉትን የሚያደርጉ በቃላቸው የሚገኙ ሲሆኑ ህወሃት ግን  በቃሉ የማይገኝ ውሸትን ባህሉ አድርጎ የተቀበለ ድርጅት ነው። የቀድሞው ገዥዎች እኛ ዲሞክራት ነን ውጡና የመሠላችሁን ፓሪት አቋቁሙ፤ምርጫም አካሂዱ፤ ጋዜጣም ፃፉ ብለው ሲያበቁ ዞር ብለው ደግሞ በዚሁ ምክንያት የፓሪት መሪዎችን አላሳሩም፤ መራጮችን አልገደሉም፤ ጋዜጠኞቹን አላሳደዱም። የቀድሞው ገዥዎች ፓሪትም ምርጫም ጋዜጣም የለም ብለው እንቅጩን ነግረውን ሲያበቁ በዚያው ፀንተዋል።ህወሃት ግን የዴሞክራሲን ዋጋ ሳያውቅ ስለደሞክራሲ የጮኸ ግን ደግሞ ከሁሉም የከፋ እኩይ አምባገነንና አፋኝ ቡድን ሆኖ የህዝቡን መከራ አብዝቶ ሃያ አንድ ዓመት ዘልቋል።
ይሄው ድርጅት ህዝብ የሚለው አንድም ራሱን ሲሆን አንድም ደግሞ ስብእናቸውን በምስር ወጥ የገዛቸውንና በራሱ አምሳያ ጠፍጥፎ የሠራቸውን የግለሰቦችን ስብስብ ነው። የለም እኛ እውነት የሌለበት ሠፈራችን አይደለም ስብእናችንንም ለከንቱ ነገር አሳልፈን አንሰጥም ያሉ ሰዎች ግን ለህወሃት ህዝብም ሰውም አይባሉም።እንዲህ ያሉት የሰው ልጆች እንደጠላት ተቆጥረው የመከራ እንጀራን እንዲበሉ የመከራ ጽዋንም እንዲጎነጩ ወደ ዘብጥያ ተጥለው ብልቶቻቸወን ተቀጥቅጠው ዘር እንዳይተኩ መደረጉን በዓይናችን አይተናል በጆሯችንም ሰምተናል። አገሪቷ ሰው አልባ እስክትሆንም ድረስ ህወሃቶች የመዘዙትን ሰይፍ ወደ ሰገባው ላለመለስ እጃቸውን በደም ወጪት ውስጥ ነክረው ተማምለው ቁመዋል። እነዚህ ቡድኖች ሰውም ህዝብም የሚሉት ስብእናቸውን በልፋጭ ሥጋ የገዟቸውን አልባሌ ግለሰቦችን እንጂ ለስብእናቸው ክብር ሰጥተው የለም “እኔ ሰው” ነኝ ብለው ከሃሰተኞችና ከነፍሰ ገዳዮች ጋር አንተባበርም ያሉትን አይደለም።የወሃት ህዝብና የእኛ ህዝብ በጣም ልዩነት አሏቸው።
እኛ ህዝብ የምንለው ጣኦቱ መለስ ዜናዊ ለደጅ ጥናትም ለሌላም ወደ ውጭ አገር ይሄዳል በተባለ ግዜ እርሱ በሚያልፍበት መንገድ ላይ የእለት ተግባሩን ለማከናወን ተፍ ተፍ ሲል ተገኝቶ እየተገፈተረ ወደ ጉድጓድም ወደ ጓዳም ገብቶ እንዲደበቅ የሚደረገው ያንን በእግሩ የሚኳትነውን ዜጋ ነው ህዝብ ብለን የምንጠራው። ህወሃቶች ግን ህዝብ ብለው የሚጠሩት ጣኦቱን አጅበው ሰፈሩንና መንደሩን አስወጥረው የሚያስጨንቁትን እነዚያ ጥቂቶችንና ከእነርሱ ጋር ለሆዳቸው ሲሉ ብቻ የተሳሰሩትን እንጂ ተገፈታትረው ወደ ጉድጓድም ወደ ጓዳም የሚወረወሩትን ብዙሃኑን አይደለም። መለስ በዚህ ያልፋል በተባለ ግዜ ስንቱ ጉሸማ ደርሶበታል፤ ስንቱ ከቀጠሮው ዘይግቷል፤ ስንቱስ በማይፈልገው ቤት ውስጥ ገብቶ እንዲደበቅ ተደርጓል። ግን ለምን መለስ ያልፍበታል በተባለ መንገድ ላይ የተገኘ ሁሉ እየተገፈተረ ገደል ይጨመራል  ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ህወሃቶች በህዝብ ስም ድምጻቸው ከፍ አድርገው ባዶ ጩኸት የሚጮሁ ግን ደግሞ ያንኑ ህዝብ የማያምኑ ቡድኖች በመሆናቸው ነው። መተማመን ከበጎ ሥራ የሚመነጭ ነው። ህወሃቶች በጎ ሥራ የሌላቸው መሆናቸውን ስለሚያውቁት ሠርቶ አደሩን ህዝብ አያምኑትም። ይህ ሠርቶ አደር ህዝብ የራሱን ማህበር አቋቁሞ የራሱን መሪ እንዲመርጥም አይፈቅዱም። ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ እንዳይኖረውም አግደውታል። እኛ ህዝብ የምንለው ይሄን ነጻነቱን የተነፈገውን ነው።
እኛ ህዝብ የምንለው በኢቲቪና በበረከት ስምኦን ፕሮፖጋንዳ ተወጥሮ “ዲፕረስድ” የሆነውን  ህዝብ እንጂ እነዚያ እነበረከት ስምዖንን ለመምሰል የሚኳትኑ ዘባተሎዎችን አይደለም።ዛሬ ጎሬቤታችን ኬኒያ ከአስር በላይ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያ አላት።ህዝቧም የፈለገውን ቻናል እየመረጠ ያያል ይሰማል። ይሄ በኢትዮጵያችን የተከለከለ ነው።ለምን ቢሉ ነጻ ሚዲያ ካለ ዘረኛው ህወሃት እስከ ዛሬ በህዝብ ሥም የፈጸመው ወንጀል ተነግሮ እውነተኛ ማንነቱ እንዳይገለጥ ስለሚፈራ ብቻ ነው።እንግዲህ እነርሱ ህዝብ ብለው የሚጠሩት  ከ30 ዓመት በላይ ወንጀል ሲፈጽም የኖረውንና ለዚህ ወንጀላቸውም መከደን የሚተባበሩትን እንጂ ለእውነት የቆሙትንና እውነቱ ይገለጥ የሚሉትን አይደለም።
እኛ ህዝብ ብለን የምንጠራውም የምንታገልለትም እንደ ጎሬቤቱ ኬኒያ አማራጭ ሳይኖረው በአንድ ቴሌቭዥን ብቻ በህወሃት ፕሮፖጋንዳ “ዲፕሬስድ” ሁኖ የሚኖረውን ብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ ነው እንጂ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት የነፈጉትን እና ለዚያ ተባባሪ የሆኑ ጥቂቶችን አይደለም።ባጠቃላይ ህወሃት/ኢሕአዴግ ሕዝብ ብሎ የሚጠራውና እኛ ህዝብ ብለን የምንጠራው በእጅጉ ይለያያል። እነርሱ ህዝብ የሚሉት ራሳቸውን እና ራሳቸውን ብቻ ነው።ከእነርሱ ውጪ ያለ ለህወሃት ሰውም ህዝብም አይባልም።
በመጨረሻም ህዝብ ጥቂት የመሰብሰብ እድል ባገኘ ጊዜ “ሳንፈልጋቸው ሃያ ዓመታቸው” ብሎ የሚፈልገውን ተናግሯል።አዎን ሳንፈልጋቸው ሃያ አንድ ዓመት ዘር እየቆጠሩ ዜጎችን ያሰቃዩ እነዚህ ዘረኞች ከህግ በታች እስኪሆኑ ድረስ የተጀመረው ትግል  በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በኢትዮጵያችን ፍትህ እስከሚነግስ ድረስ፤ ነጻነት ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ እስከሚናኝ ድረስ፤ እኩልነት የአገራችን ዋና መገለጫ እስከሚሆን ድረስ፤ የተደበቀው ተገልጦ እውነቱ እስከሚነገር ድረስ፤በህወሃት የተዘራው የጥላቻ ዘር ከሥሩ ተነቅሎ በምትኩ ፍቅር እና አንድነት እስኪያብብ ድረስ የጀመርነውን ትግል አናቆምም።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

No comments:

Post a Comment