Translate

Tuesday, September 25, 2012

አቶ በረከት የኢቲቪና የፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጆችን አንስተው ታዛዦቻቸውን ሊሾሙ ነው ተባለ


ኢሳት ዜና:-የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን  የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥራ አስኪያጆችን በማንሳት ለእርሳቸው ታዛዥ የሆኑ ሰዎችን ለማስቀመጥ  እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተጠቆመ።
በዚህም መሰረት ከደቡብ ክልል ያስመጡትና በኢትዮጵያ ራዲዮ ውስጥ በምክትል ሥራ አስኪያጅነት ሢሰራ የቆየው ሰለሞን ተስፋዬ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሰይፈ ደርቤ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት  ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ ወስነው ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።
ሰይፈ ደርቤ የፍትህ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ላይ በምክትል ዋና አዘጋጅነት በሚሠራበት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተከታታይ በሚያወጣቸው  የፕሮፓጋንዳ ጽሁፎች፤ የሀሰት ክስ ሲደረድር መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ለ አዲስ ሹመት የታጩት ሁለቱም ሰዎች የ አቶ በረከት ታዛዦች መሆናቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል።
አቶ በረከት እነዚህን ሁለት ታዛዦቻቸውን ወደ ላይ ለማምጣት የፈለጉትም እንደተለመደው <ጠላቴ>የሚሏቸውን ለማጥቃት ይረዱኛል ብለው ነው-ብለዋል-ምንጮቹ።

የደቡብ ክልሉ ሰለሞን ተስፋዬ እና የብአዴኑ ሰይፈ ደርቤ በጓደኞቻቸውም ሆነ በመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ዘንድ የሚታወቁት አፍቃሬ በረከት በመሆናቸው እንደሆነም ተመልክቷል።
ምንጮቹ  እንደሚሉት አቶ በረከት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት፦ “የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ  ሆኖ እየሠራ ያለው ዘርአይ የትግሉ ውጤት በመሆኑ ለበረከት ጥሩ መሳሪያ ሊሆን ስላልቻለ ነው።”
አቶ ከፍያለው አዘዘን ተክቶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የነበረው ሰብስቤም እንዲወገድ የተፈለገው እንደታሰበው  ለአቶ በረከት መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል ባለመቻሉ ነው ተብሏል።
አቶ በረከት ብዙ ጊዜ ፦‹ሰብስቤ ደነዝ ከሚባሉ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ስራውን አያውቀውም፤ የሱ ስራ መጠጥ መጠጣትና ጫት መቃም ነው ›  በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
“አሁን በመለስ ሞት ምክንያት የተፈጠረውን አቅም በመጠቀም ዘርዓይንና ሰብስቤን  ገፍትሮ ለማስወጣት ዝግጅቱ ተጠናቋል ፡፡”ያሉት የዜናው ምንጮች፤ ሰሎሞን እና ሰይፈም አዲሶቹ ስራ አስኪያጆች ለመሆን በዝግጅት ላይ ናቸው”ብለዋል።
<<ለዚህም ዕቅዳቸው አቅጣጫ ለመስጠት፤ <ኢህአዴግ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር የልምድ ልውውጥ ያደርጋል> በሚል፤ አቶ በረከት ቀጣዮቹን የሚዲያዎቹን ሀላፊዎች ማለትም አቶ ሰለሞን ተስፋየን እና አቶ ሰይፈ ደርቤን  ቻይና ወስደው እያሰለጠኑ ነው ብለዋል።>>እነኚሁ በድርጅቶቹ ውስጥ ያሉ የኢሳት ምንጮች።
እንደ ዜናው ምንጮች መረጃ ፤የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ስላጠናቀቁ  መገፋት እየደረሰባቸው ነው።
በምርጫ 97 ማግስት የቅንጅት መሪዎችንና የጋዜጠኞችን የፍርድ ሂደት በፈቃደኝነት ግንባር ቀደም አቃቤ ህግ ሆነው የመሩት አቶ ሽመልስ ቀደም ሲልም በአቶ መለስ ፦<ሌቦች> ተብለው ተባርረው ከነበሩት ዳኞች አንዱ ናቸው።
ገለልተኛ አስተያዬት ሰጭዎች  በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ የተፈጠረውን ቅራኔ-  የህወሀትና ብአዴን ፍትጊያ ነጸብራቅ ነው ሲሉ አስተያዬታቸውን ይሰጣሉ።

No comments:

Post a Comment